ኢሳይያስ 43:1-28
43 አሁን ግን፣ ያዕቆብ ሆይ ፈጣሪህ፣እስራኤልም ሆይ የሠራህ ይሖዋ+ እንዲህ ይላል፦
“እኔ ተቤዥቼሃለሁና+ አትፍራ።
በስምህ ጠርቼሃለሁ።
አንተ የእኔ ነህ።
2 በውኃዎች መካከል ስታልፍ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤+በወንዞችም መካከል ስትሻገር አያሰምጡህም።+
በእሳት መካከል ስትሄድ አትቃጠልም፤ነበልባሉም አይፈጅህም።
3 እኔ ይሖዋ አምላክህ፣የእስራኤል ቅዱስ፣ አዳኝህ ነኝና።
ግብፅን ለአንተ ቤዛ አድርጌ ሰጥቻለሁ፤ኢትዮጵያንና ሴባን በአንተ ምትክ ሰጥቻለሁ።
4 አንተ በዓይኔ ፊት ውድ ሆነሃልና፤+የተከበርክም ነህ፤ እኔም ወድጄሃለሁ።+
ስለዚህ በአንተ ምትክ ሰዎችን፣በሕይወትህም* ምትክ ብሔራትን እሰጣለሁ።
5 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ።+
ዘርህን ከምሥራቅ አመጣለሁ፤ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ።+
6 ሰሜንን ‘ልቀቃቸው!’ እለዋለሁ፤+
ደቡብንም እንዲህ እለዋለሁ፦ ‘አታግታቸው።
ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ አምጣ፤+
7 በስሜ የተጠራውን፣+ለክብሬም የፈጠርኩትን፣የሠራሁትንና ያበጀሁትን ሁሉ አምጣ።’+
8 ዓይን ቢኖራቸውም ዕውር የሆኑትን፣ጆሮ ቢኖራቸውም ደንቆሮ የሆኑትን ሰዎች አውጣ።+
9 ብሔራት ሁሉ አንድ ቦታ ይሰብሰቡ፤ሕዝቦችም በአንድነት ይሰብሰቡ።+
ከመካከላቸው ይህን ሊናገር የሚችል ማን አለ?
ወይስ የመጀመሪያዎቹን ነገሮች ሊነግሩን ይችላሉ?*+
ትክክል መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ምሥክሮቻቸውን ያቅርቡ፤ወይም ሰምተው ‘ይህ እውነት ነው!’ ይበሉ።”+
10 “እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ”+ ይላል ይሖዋ፤“አዎ፣ የመረጥኩት አገልጋዬ ናችሁ፤+ይህም ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ*ደግሞም እኔ ምንጊዜም ያው እንደሆንኩ ታስተውሉ ዘንድ ነው።+
ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ከእኔም በኋላ የለም።+
11 እኔ፣ አዎ እኔ ይሖዋ ነኝ፤+ ከእኔ በቀር አዳኝ የለም።”+
12 “በመካከላችሁ ባዕድ አምላክ ባልነበረበት ጊዜየተናገርኩት፣ ያዳንኩትና ያሳወቅኩት እኔ ነኝ።+
ስለዚህ እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ” ይላል ይሖዋ፤ “እኔም አምላክ ነኝ።+
13 ደግሞም እኔ ምንጊዜም ያው ነኝ፤+ከእጄም አንዳች ነገር ሊነጥቅ የሚችል የለም።+
እርምጃ በምወስድበት ጊዜ ሊያግድ የሚችል ማን ነው?”+
14 እናንተን የሚቤዠው+ የእስራኤል ቅዱስ ይሖዋ+ እንዲህ ይላል፦
“ለእናንተ ስል ወደ ባቢሎን እሰዳለሁ፤ የበሮቹንም መቀርቀርያዎች ሁሉ እጥላለሁ፤+በመርከቦቻቸው ላይ ያሉት ከለዳውያንም በጭንቀት ይጮኻሉ።+
15 እኔ ይሖዋ የእናንተ ቅዱስ፣+ የእስራኤል ፈጣሪ፣+ ንጉሣችሁ ነኝ።”+
16 ይሖዋ ይኸውምበባሕር መካከል መንገድ የሚያበጀው፣በሚናወጡ ውኃዎችም መካከል ጎዳና የሚዘረጋው፣+
17 የጦር ሠረገላውንና ፈረሱን፣+ሠራዊቱንና ኃያላን ተዋጊዎቹን በአንድነት የሚያወጣው አምላክ እንዲህ ይላል፦
“ይተኛሉ፤ አይነሱምም።+
እንደሚነድ የጧፍ ክር ተዳፍነው ይጠፋሉ።”
18 “የቀድሞዎቹን ነገሮች አታስታውሱ፤ያለፈውንም ነገር አታውጠንጥኑ።
19 እነሆ፣ አዲስ ነገር አደርጋለሁ፤+አሁንም እንኳ መከናወን ጀምሯል።
ይህን አታስተውሉም?
በምድረ በዳ መንገድ አዘጋጃለሁ፤+በበረሃም ወንዞችን አፈልቃለሁ።+
20 የዱር አውሬ፣ ቀበሮዎችናሰጎኖች ያከብሩኛል፤በምድረ በዳ ውኃ፣በበረሃም ወንዞችን እሰጣለሁና፤+ይህን የማደርገው የመረጥኩት ሕዝቤ+ እንዲጠጣ፣
21 ለራሴ የሠራሁትም ሕዝብ እንዲጎነጭ ነው፤ሕዝቤ ውዳሴዬን እንዲያውጅ ይህን አደርጋለሁ።+
22 እስራኤል ሆይ፣ አንተ ግን የእኔ ነገር ስለታከተህ፣+ያዕቆብ ሆይ፣ አልጠራኸኝም።+
23 ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ ለማቅረብ በግ አላመጣህልኝም፤ወይም መሥዋዕቶች በማቅረብ አላከበርከኝም።
ስጦታ እንድታመጣልኝ አላስገደድኩህም፤ነጭ ዕጣን አቅርብልኝ ብዬም አላሰለቸሁህም።+
24 በገንዘብህ ጠጅ ሣር* አልገዛህልኝም፤በመሥዋዕቶችህም ስብ አላጠገብከኝም።+
ከዚህ ይልቅ ኃጢአትህን አሸክመኸኛል፤በምትፈጽማቸውም በደሎች አሰልችተኸኛል።+
25 ስለ ራሴ ስል+ በደልህን* እኔ ራሴ እደመስሰዋለሁ፤+ኃጢአትህንም አላስታውስም።+
26 እስቲ አስታውሰኝ፤ ጉዳያችንን አቅርበን እንሟገት፤ትክክለኛ መሆንህን ለማረጋገጥ በበኩልህ ጉዳይህን ተናገር።
27 የመጀመሪያው አባትህ ኃጢአት ሠርቷል፤የገዛ ቃል አቀባዮችህም* በእኔ ላይ ዓምፀዋል።+
28 ስለዚህ በቅዱሱ ስፍራ የሚገኙትን መኳንንት አረክሳለሁ፤ያዕቆብንም ለጥፋት አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤እስራኤልንም ለስድብ እዳርገዋለሁ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በነፍስህም።”
^ ወደፊት የሚመጡትን የመጀመሪያዎቹን ነገሮች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ትታመኑብኝ ዘንድ።”
^ እዚህ ላይ የተጠቀሰው የዕብራይስጥ ቃል ጥሩ መዓዛ ያለውን ተክል ያመለክታል። ሆኖም የተክሉ ምንነት በእርግጠኝነት አይታወቅም።
^ ወይም “የዓመፅ ድርጊትህን።”
^ የሕጉን አስተማሪዎች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።