ኢዩኤል 1:1-20
1 ወደ ፐቱኤል ልጅ፣ ወደ ኢዩኤል* የመጣው የይሖዋ ቃል ይህ ነው፦
2 “እናንተ ሽማግሌዎች ይህን ስሙ፤የአገሪቱም* ነዋሪዎች ሁሉ ልብ በሉ።
በእናንተም ዘመን ይሁን በአባቶቻችሁ ዘመንእንዲህ ያለ ነገር ተከስቶ ያውቃል?+
3 ይህን ለልጆቻችሁ ተናገሩ፤ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፣የእነሱ ልጆች ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ይናገሩ።
4 ከአውዳሚ አንበጣ የተረፈውን የአንበጣ መንጋ በላው፤+ከአንበጣ መንጋ የተረፈውንም ኩብኩባ በላው፤ከኩብኩባ የተረፈውን ደግሞ የማይጠግብ አንበጣ በላው።+
5 እናንተ ሰካራሞች ንቁ፤+ ደግሞም አልቅሱ!
እናንተ የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉጣፋጩ የወይን ጠጅ ከአፋችሁ ላይ ስለተወሰደ ዋይ ዋይ በሉ።+
6 ኃያል የሆነና የሕዝቡ ብዛት ስፍር ቁጥር የሌለው ብሔር ምድሬን ወሮታልና።+
ጥርሶቹ የአንበሳ ጥርሶች ናቸው፤+ መንገጭላውም የአንበሳ መንገጭላ ነው።
7 የወይን ተክሌን አጠፋው፤ የበለስ ዛፌንም ጉቶ አደረገው፤ቅርፊታቸውን ሙልጭ አድርጎ ልጦ ወዲያ ጣላቸው፤በቅርንጫፎቻቸው ላይ አንድም ልጥ አልቀረም።
8 ማቅ ለብሳ ለልጅነት ሙሽራዋ* እንደምታለቅስ ድንግል*ዋይ ዋይ በዪ።
9 የእህል መባና+ የመጠጥ መባ+ ከይሖዋ ቤት ተቋርጧል፤የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑት ካህናቱም ሐዘን ላይ ናቸው።
10 እርሻው ወድሟል፤ ምድሪቱ አዝናለች፤+እህሉ ወድሟልና፤ አዲሱ የወይን ጠጅ ደርቋል፤ ዘይቱም ተሟጧል።+
11 ገበሬዎች አፍረዋል፤ የወይን አትክልት ሠራተኞች ዋይ ዋይ ይላሉ፤ይህም የሆነው ከስንዴውና ከገብሱ የተነሳ ነው፤የእርሻው መከር ጠፍቷልና።
12 ወይኑ ደርቋል፤የበለስ ዛፉም ጠውልጓል።
ሮማኑ፣ ዘንባባው፣ ፖሙናበሜዳው ላይ ያለው ዛፍ ሁሉ ደርቋል፤+በሕዝቡ መካከል የነበረው ደስታ ወደ ኀፍረት ተለውጧልና።
13 እናንተ ካህናት ማቅ ልበሱ፤* ደግሞም ሐዘን ተቀመጡ፤*እናንተ በመሠዊያው ፊት የምታገለግሉ+ ዋይ ዋይ በሉ።
እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች ኑ፣ ማቅ ለብሳችሁ እደሩ፤ከአምላካችሁ ቤት የእህል መባና+ የመጠጥ መባ+ ተቋርጧልና።
14 ጾም አውጁ!* የተቀደሰ ጉባኤ ጥሩ።+
ሽማግሌዎቹንና የምድሪቱን ነዋሪዎች ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ ይሖዋ ቤት ሰብስቡ፤+እርዳታም ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጩኹ።
15 ከቀኑ የተነሳ ወዮላችሁ!
የይሖዋ ቀን ቀርቧልና፤+ሁሉን ከሚችለው አምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል!
16 ምግብ ከዓይናችን ፊት፣ሐሴትና ደስታም ከአምላካችን ቤት ጠፍቶ የለም?
17 ዘሮቹ* ከአካፋዎቻቸው ሥር ጠውልገዋል።
ጎተራዎቹም ተራቁተዋል።
ጎታዎቹ* ፈራርሰዋል፤ እህሉ ደርቋልና።
18 መንጎቹ እንኳ ሳይቀሩ ያቃስታሉ!
ከብቶቹ ግራ ተጋብተው ይቅበዘበዛሉ፤ መሰማሪያ የላቸውምና!
የበጎቹም መንጋ ቅጣቱን ይቀበላል።
19 ይሖዋ ሆይ፣ ወደ አንተ እጣራለሁ፤+በምድረ በዳ ያለውን የግጦሽ መሬት እሳት በልቶታልና፤በሜዳ ያሉትንም ዛፎች ሁሉ ነበልባል አቃጥሏቸዋል።
20 የዱር አራዊትም እንኳ አንተን በጉጉት ይጠባበቃሉ፤ምክንያቱም የውኃ ጅረቶቹ ደርቀዋል፤በምድረ በዳ ያለውን የግጦሽ መሬትም እሳት በልቶታል።”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “ይሖዋ አምላክ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
^ ወይም “የምድሪቱም።”
^ ወይም “ባሏ።”
^ ወይም “ወጣት ሴት።”
^ ቃል በቃል “ታጠቁ።”
^ ወይም “ደረታችሁን ምቱ።”
^ ቃል በቃል “ጾምን ቀድሱ።”
^ “የደረቁት በለሶች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ከጎተራ አነስ ያለ የእህል ማስቀመጫ።