ኢያሱ 14:1-15

  • ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያለውን ምድር መከፋፈል (1-5)

  • ኬብሮን ለካሌብ በርስትነት ተሰጠች (6-15)

14  እንግዲህ እስራኤላውያን በከነአን ምድር ርስት አድርገው የወረሱት ይኸውም ካህኑ አልዓዛር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል ነገዶች የአባቶች ቤት መሪዎች ያወረሷቸው ምድር ይህ ነው።+  ይሖዋ ዘጠኙን ነገድና ግማሹን ነገድ+ አስመልክቶ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ርስታቸው የተከፋፈለው በዕጣ ነበር።+  ሙሴ ለሌሎቹ ሁለት ነገዶችና ለሌላኛው ግማሽ ነገድ ከዮርዳኖስ ማዶ* ርስት ሰጥቷቸው ነበር፤+ ለሌዋውያኑ ግን በእነሱ መካከል ርስት አልሰጣቸውም።+  የዮሴፍ ዘሮች እንደ ሁለት ነገድ ተደርገው ይቆጠሩ+ የነበረ ሲሆን እነሱም ምናሴና ኤፍሬም ናቸው፤+ ለሌዋውያኑም ከሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም ለከብቶቻቸውና ለንብረቶቻቸው ከሚሆን መሬት በስተቀር በምድሪቱ ውስጥ ድርሻ አልሰጧቸውም።+  በመሆኑም እስራኤላውያን ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ምድሪቱን ተከፋፈሉ።  ከዚያም የይሁዳ ሰዎች በጊልጋል+ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ የቀኒዛዊው የየፎኒ ልጅ ካሌብም+ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ በቃዴስበርኔ+ ስለ እኔና ስለ አንተ ለእውነተኛው አምላክ ሰው ለሙሴ+ ምን እንዳለው በሚገባ ታውቃለህ።+  የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስበርኔ ሲልከኝ የ40 ዓመት ሰው ነበርኩ፤+ እኔም ትክክለኛውን መረጃ* ይዤ መጣሁ።+  አብረውኝ የወጡት ወንድሞቼ የሕዝቡ ልብ እንዲቀልጥ ቢያደርጉም እኔ ግን አምላኬን ይሖዋን በሙሉ ልቤ ተከተልኩት።+  ሙሴም በዚያ ዕለት ‘አምላኬን ይሖዋን በሙሉ ልብህ ስለተከተልከው እግርህ የረገጣት ምድር ለዘለቄታው የአንተና የልጆችህ ርስት ትሆናለች’ ብሎ ማለ።+ 10  እስራኤል በምድረ በዳ እየተጓዘ ሳለ+ ይሖዋ ለሙሴ ይህን ቃል ከገባለት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ በገባው ቃል መሠረት+ እነዚህን 45 ዓመታት በሕይወት አቆይቶኛል፤+ ይኸው ዛሬ 85 ዓመት ሆኖኛል። 11  ደግሞም ሙሴ በላከኝ ጊዜ የነበረኝ ብርታት ዛሬም አለኝ። ልክ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ አሁንም ወደ ጦርነት ለመሄድም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችል ጥንካሬ አለኝ። 12  ስለዚህ ይሖዋ በዚያ ዕለት ቃል የገባውን ይህን ተራራማ አካባቢ ስጠኝ። የተመሸጉ ታላላቅ ከተሞች+ ያሏቸው ኤናቃውያን+ በአካባቢው እንደሚኖሩ በዚያ ቀን ሰምተህ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ከእኔ ጋር እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤+ ይሖዋም በገባው ቃል መሠረት ድል አድርጌ አባርራቸዋለሁ።”+ 13  በመሆኑም ኢያሱ ባረከው፤ ኬብሮንንም ለየፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርጎ ሰጠው።+ 14  ኬብሮን ለቀኒዛዊው ለየፎኒ ልጅ ለካሌብ እስከ ዛሬ ድረስ ርስት የሆነችው ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም እሱ የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን በሙሉ ልቡ ተከትሏል።+ 15  ኬብሮን ከዚያ በፊት ቂርያትአርባ+ ተብላ ትጠራ ነበር (አርባ በኤናቃውያን መካከል ታላቅ ሰው ነበር)። ምድሪቱም ከጦርነት አረፈች።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ከልቤ ጋር ያለውን ቃል።”