ኢያሱ 23:1-16
23 ይሖዋ እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው+ ከብዙ ጊዜ በኋላ፣ ኢያሱም አርጅቶና ዕድሜው ገፍቶ ሳለ+
2 ኢያሱ እስራኤላውያንን በሙሉ፣ ሽማግሌዎቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ዳኞቻቸውንና አለቆቻቸውን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦+ “እንግዲህ እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቷል።
3 አምላካችሁ ይሖዋ ለእናንተ ሲል በእነዚህ ብሔራት ላይ ያደረገውን ሁሉ ራሳችሁ አይታችኋል፤ ምክንያቱም ለእናንተ እየተዋጋላችሁ የነበረው አምላካችሁ ይሖዋ ነው።+
4 እኔም ከዮርዳኖስ አንስቶ በስተ ምዕራብ* እስከሚገኘው እስከ ታላቁ ባሕር* ድረስ ያጠፋኋቸውን ብሔራት ሁሉ ምድር+ ጨምሮ የቀሩትን ብሔራት ምድር+ ለየነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆን በዕጣ አከፋፍዬ+ ሰጥቻችኋለሁ።
5 እነሱን ከፊታችሁ ያባረራቸው አምላካችሁ ይሖዋ ነው፤+ እሱም ለእናንተ ሲል አባረራቸው፤* እናንተም አምላካችሁ ይሖዋ በገባላችሁ ቃል መሠረት ምድራቸውን ወረሳችሁ።+
6 “እንግዲህ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ+ ውስጥ ከተጻፈው ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ፈጽሞ ዞር ሳትሉ+ ሕጉን ሁሉ ለመጠበቅና ለመፈጸም ደፋሮች ሁኑ፤
7 እንዲሁም በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ብሔራት ጋር አትቀላቀሉ።+ ሌላው ቀርቶ የአማልክታቸውን ስም አታንሱ፤+ በእነሱም አትማሉ፤ ፈጽሞ አታገልግሏቸው እንዲሁም አትስገዱላቸው።+
8 ከዚህ ይልቅ እስከዚህ ቀን ድረስ እንዳደረጋችሁት ሁሉ ከአምላካችሁ ከይሖዋ ጋር ተጣብቃችሁ ኑሩ።+
9 ይሖዋ ታላላቅና ኃያላን ብሔራትን ከፊታችሁ ያባርራቸዋል፤+ እስከዚህ ቀን ድረስ አንድም ሰው ሊቋቋማችሁ አልቻለም።+
10 አምላካችሁ ይሖዋ በገባላችሁ ቃል መሠረት+ ለእናንተ ስለሚዋጋላችሁ+ ከእናንተ አንዱ፣ ሺህ ሰው ያሳድዳል።+
11 ስለዚህ አምላካችሁን ይሖዋን በመውደድ+ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።*+
12 “ይሁንና ወደ ኋላ ዞር ብትሉና ከእነዚህ ብሔራት መካከል ተርፈው ከእናንተ ጋር ከቀሩት+ ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ብትመሠርቱ፣ በጋብቻ ብትዛመዱ+ እንዲሁም እናንተ ከእነሱ ጋር ብትወዳጁ፣ እነሱም ከእናንተ ጋር ወዳጅነት ቢመሠርቱ
13 አምላካችሁ ይሖዋ ከዚህ በኋላ ለእናንተ ሲል እነዚህን ብሔራት እንደማያባርራቸው* በእርግጥ እወቁ።+ እነሱም አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር ላይ እስክትጠፉ ድረስ ወጥመድ፣ አሽክላ፣ ለጀርባችሁ ጅራፍ እንዲሁም በዓይናችሁ ውስጥ እንዳለ እሾህ ይሆኑባችኋል።+
14 “እንግዲህ እኔ መሞቻዬ ተቃርቧል፤* አምላካችሁ ይሖዋ ከገባላችሁ መልካም ቃል ሁሉ አንዲቷም እንኳ ሳትፈጸም እንዳልቀረች በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ* ታውቃላችሁ። ሁሉም ተፈጽሞላችኋል። ከመካከላቸው ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም።+
15 ሆኖም አምላካችሁ ይሖዋ የገባላችሁ መልካም ቃል በሙሉ እንደተፈጸመላችሁ ሁሉ ይሖዋ አመጣባችኋለሁ ብሎ+ የተናገረውን ጥፋት ሁሉ* ያመጣባችኋል፤ አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድርም ያጠፋችኋል።+
16 አምላካችሁ ይሖዋ እንድትጠብቁት ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ካፈረሳችሁ እንዲሁም ሄዳችሁ ሌሎች አማልክትን ካገለገላችሁና ለእነሱ ከሰገዳችሁ የይሖዋ ቁጣ በእናንተ ላይ ይነድዳል፤+ ከሰጣችሁም መልካም ምድር ላይ በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በፀሐይ መግቢያ።”
^ ሜድትራንያንን ያመለክታል።
^ ወይም “አስለቀቃቸው።”
^ ወይም “ነፍሳችሁን በጥንቃቄ ጠብቁ።”
^ ወይም “እንደማያስለቅቃቸው።”
^ ቃል በቃል “ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ክፉ ቃል ሁሉ።”