ኢያሱ 4:1-24

  • ለመታሰቢያነት የሚያገለግሉ ድንጋዮች (1-24)

4  መላው ብሔር ዮርዳኖስን እንደተሻገረ ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ 2  “ከሕዝቡ መካከል 12 ሰዎችን ይኸውም ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው ምረጥ፤+ 3  እነሱንም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ ‘ከዮርዳኖስ ወንዝ መሃል ይኸውም የካህናቱ እግር ከቆመበት ስፍራ+ 12 ድንጋዮችን ውሰዱ፤ ድንጋዮቹንም ይዛችሁ በመሄድ በምታድሩበት ስፍራ አስቀምጧቸው።’”+ 4  በመሆኑም ኢያሱ ከእስራኤላውያን መካከል የሾማቸውን 12 ሰዎች ይኸውም ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው ጠራ፤ 5  ኢያሱም እንዲህ አላቸው፦ “የአምላካችሁን የይሖዋን ታቦት ቀድማችሁ ወደ ዮርዳኖስ መሃል ሂዱ፤ እያንዳንዳችሁም በእስራኤላውያን ነገዶች ቁጥር ልክ አንድ አንድ ድንጋይ አንስታችሁ በትከሻችሁ ተሸከሙ፤ 6  ይህም በመካከላችሁ እንደ ምልክት ሆኖ ያገለግላል። ምናልባት ወደፊት ልጆቻችሁ* ‘እነዚህን ድንጋዮች እዚህ ያስቀመጣችኋቸው ለምንድን ነው?’ ብለው ቢጠይቋችሁ+ 7  እንዲህ በሏቸው፦ ‘የዮርዳኖስ ውኃ በይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ተቋርጦ ስለነበር ነው።+ ታቦቱ ዮርዳኖስን ሲሻገር የዮርዳኖስ ውኃ ተቋረጠ። እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤላውያን በዘላቂነት እንደ መታሰቢያ* ሆነው ያገለግላሉ።’”+ 8  እስራኤላውያንም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እነሱም ይሖዋ ኢያሱን ባዘዘው መሠረት ከዮርዳኖስ መሃል በእስራኤላውያን ነገዶች ቁጥር ልክ 12 ድንጋዮችን አነሱ። ከዚያም ወደሚያድሩበት ስፍራ ይዘዋቸው በመሄድ እዚያ አስቀመጧቸው። 9  በተጨማሪም ኢያሱ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት እግር ቆሞበት በነበረው በዮርዳኖስ መሃል ባለው ቦታ+ ላይ 12 ድንጋዮችን አስቀምጦ ነበር፤ እነዚህም ድንጋዮች እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይገኛሉ። 10  ሙሴ ለኢያሱ በሰጠው መመሪያ መሠረት ይሖዋ፣ ኢያሱ ለሕዝቡ እንዲናገር ያዘዘው ነገር በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት በዮርዳኖስ መሃል ቆመው ነበር። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ፈጥኖ ተሻገረ። 11  ሕዝቡ ሁሉ ተሻግሮ እንዳበቃ የይሖዋ ታቦትና ካህናቱ ሕዝቡ እያያቸው ተሻገሩ።+ 12  ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ሙሴ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት+ የጦርነት አሰላለፍ ተከትለው+ ሌሎቹን እስራኤላውያን ቀድመው ተሻገሩ። 13  ወደ 40,000 የሚሆኑ ለጦርነት የታጠቁ ሰዎች ወደ ኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ በይሖዋ ፊት ተሻገሩ። 14  በዚያ ዕለት ይሖዋ ኢያሱን በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደረገው፤+ እነሱም ሙሴን በጥልቅ ያከብሩት እንደነበር ሁሉ እሱንም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በጥልቅ አከበሩት።*+ 15  ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ 16  “የምሥክሩን ታቦት+ የተሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ እንዲወጡ እዘዛቸው።” 17  በመሆኑም ኢያሱ ካህናቱን “ከዮርዳኖስ ውጡ” በማለት አዘዛቸው። 18  የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት+ ከዮርዳኖስ መሃል ሲወጡና የካህናቱ እግር ከውኃው ወጥቶ ደረቁን መሬት ሲረግጥ የዮርዳኖስ ውኃ እንደቀድሞው መፍሰሱንና ዳርቻውን ሁሉ ማጥለቅለቁን ቀጠለ።+ 19  ሕዝቡም በመጀመሪያው ወር በአሥረኛው ቀን ላይ ከዮርዳኖስ ወጥቶ በኢያሪኮ ምሥራቃዊ ወሰን ላይ በምትገኘው በጊልጋል ሰፈረ።+ 20  ኢያሱም ከዮርዳኖስ ያወጧቸውን 12 ድንጋዮች በጊልጋል አቆማቸው።+ 21  ከዚያም እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “ወደፊት ልጆቻችሁ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው በሚጠይቋችሁ ጊዜ+ 22  ልጆቻችሁን እንዲህ በሏቸው፦ ‘እስራኤል ዮርዳኖስን በደረቅ ምድር ተሻገረ፤+ 23  ይህም የሆነው አምላካችሁ ይሖዋ ቀይ ባሕርን እስኪሻገሩ ድረስ ባሕሩን በፊታቸው እንዳደረቀው ሁሉ እኛም ዮርዳኖስን እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ ይሖዋ የዮርዳኖስን ውኃ በፊታችን ስላደረቀው ነው።+ 24  ይህን ያደረገው የምድር ሕዝቦች ሁሉ የይሖዋ ክንድ ምን ያህል ኃያል መሆኑን እንዲያውቁና+ እናንተም አምላካችሁን ይሖዋን ሁልጊዜ እንድትፈሩ ነው።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ወንዶች ልጆቻችሁ።”
ወይም “ማስታወሻ።”
ቃል በቃል “ፈሩት።”