ኢዮብ 18:1-21

  • የበልዳዶስ ሁለተኛ ዙር ንግግር (1-21)

    • የኃጢአተኞችን ዕጣ ፋንታ ገለጸ (5-20)

    • ኢዮብ አምላክን እንደማያውቅ ጠቆመ (21)

18  ሹሃዊው በልዳዶስ+ እንዲህ ሲል መለሰ፦  2  “እንዲህ ያለ ንግግር መናገራችሁን* የምትቀጥሉት እስከ መቼ ነው? በተወሰነ መጠን ልታስተውሉ ይገባል፤ ያን ጊዜ እኛ እንናገራለን።  3  ለምን እንደ እንስሳ እንቆጠራለን?+በፊታችሁስ ለምን እንደ ደነዝ* እንታያለን?  4  አንተ በቁጣ ራስህን* ብትቦጫጭቅ፣ለአንተ ሲባል ምድር ባዶ ትቀራለች?ወይስ ዓለት ከስፍራው ተነቅሎ ይወሰዳል?  5  አዎ፣ የክፉዎች ብርሃን ይጠፋል፤የእሳቱም ነበልባል አይበራም።+  6  በድንኳኑ ውስጥ ያለው ብርሃን በእርግጥ ይጨልማል፤በላዩ ያለው መብራትም ይጠፋል።  7  ብርታት የተሞላበት እርምጃው ያጥራል፤የገዛ ዕቅዱም ይጥለዋል።+  8  እግሩ ወደ መረብ ይመራዋልና፤በመረቡም ገመድ ይተበተባል።  9  ወጥመድ ተረከዙን ይይዘዋል፤ወስፈንጥርም ያጠምደዋል።+ 10  በመሬት ላይ ሸምቀቆ በስውር ይቀመጥለታል፤ወጥመድም በመንገዱ ላይ ይጠብቀዋል። 11  ሽብር ከሁሉም አቅጣጫ ፍርሃት ይለቅበታል፤+እግር በእግርም ያሳድደዋል። 12  ጉልበቱ ይከዳዋል፤አደጋም+ያንገዳግደዋል።* 13  ቆዳው ተበልቷል፤እጅግ ቀሳፊ የሆነ በሽታ* እጆቹንና እግሮቹን ይበላል። 14  ተማምኖ ከሚኖርበት ድንኳኑ ይወገዳል፤+ወደ ሽብር ንጉሥም* ይወሰዳል። 15  እንግዶች በድንኳኑ ውስጥ ይኖራሉ፤*በቤቱም ላይ ድኝ ይበተናል።+ 16  ሥሮቹ ከእሱ በታች ይደርቃሉ፤ቅርንጫፎቹ ደግሞ ከእሱ በላይ ይጠወልጋሉ። 17  መታሰቢያው ከምድር ላይ ይጠፋል፤በጎዳናም ላይ ስሙ አይታወቅም።* 18  ከብርሃን ወደ ጨለማ ይወሰዳል፤ፍሬያማ ከሆነችውም ምድር ይባረራል። 19  በሕዝቡ መካከል ልጆችም ሆኑ ዘሮች አይኖሩትም፤በሚኖርበት ስፍራም* የሚተርፍ ሰው አይኖረውም። 20  የሚጠፋበት ቀን ሲደርስ በምዕራብ ያሉ ሰዎች ይደነግጣሉ፤በምሥራቅ ያሉ ሰዎችም በፍርሃት ይዋጣሉ። 21  የክፉ አድራጊ ድንኳኖች፣አምላክን የማያውቁ ሰዎች ስፍራም እንዲህ ያለ ነገር ይደርስባቸዋል።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ኢዮብንና እንደ እሱ ያሉትን ወይም ለእሱ አዘኔታ የሚያሳዩ ሰዎችን ሊያመለክት ይችላል።
“ርኩስ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ያስነክሰዋል።”
ቃል በቃል “የሞት የበኩር ልጅ።”
ወይም “አስከፊ ወደሆነ ሞትም።”
ቃል በቃል “የእሱ ያልሆነ ነገር በድንኳኑ ውስጥ ይኖራል።”
ቃል በቃል “ስም አይኖረውም።”
ወይም “ለጊዜው በሚኖርበት ስፍራም።”