ኢዮብ 21:1-34

  • ኢዮብ የሰጠው መልስ (1-34)

    • ‘ክፉዎች የሚሳካላቸው ለምንድን ነው?’ (7-13)

    • “የአጽናኞቹን” ክፋት አጋለጠ (27-34)

21  ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦  2  “የምናገረውን በጥሞና አዳምጡ፤የምታጽናኑኝ በዚህ ይሁን።  3  በምናገርበት ጊዜ በትዕግሥት አዳምጡኝ፤ከተናገርኩ በኋላ ልትሳለቁብኝ ትችላላችሁ።+  4  ቅሬታዬ በሰው ላይ ነው? ቢሆንማ ኖሮ የእኔ* ትዕግሥት አያልቅም ነበር?  5  እዩኝ፤ በመገረምም ተመልከቱኝ፤እጃችሁን በአፋችሁ ላይ አድርጉ።  6  ስለዚህ ነገር ሳስብ እረበሻለሁ፤መላ ሰውነቴም ይንቀጠቀጣል።  7  ክፉዎች በሕይወት የሚኖሩት፣+ለእርጅና የሚበቁትና ባለጸጋ* የሚሆኑት ለምንድን ነው?+  8  ልጆቻቸው ሁልጊዜ አብረዋቸው ይኖራሉ፤ዘሮቻቸውንም ያያሉ።  9  ቤታቸው ሰላም የሰፈነበት ነው፤ የሚያሰጋቸውም ነገር የለም፤+አምላክም በበትሩ አይቀጣቸውም። 10  ኮርማዎቻቸው ዘር ያፈራሉ፤ላሞቻቸው ይወልዳሉ፤ ደግሞም አይጨነግፉም። 11  ወንዶች ልጆቻቸው እንደ መንጋ በደጅ ይሯሯጣሉ፤ልጆቻቸውም ይቦርቃሉ። 12  በአታሞና በበገና ታጅበው ይዘፍናሉ፤በዋሽንትም ድምፅ* ደስ ይሰኛሉ።+ 13  ዕድሜያቸውን በደስታ ያሳልፋሉ፤በሰላምም* ወደ መቃብር* ይወርዳሉ። 14  ይሁንና እውነተኛውን አምላክ እንዲህ ይሉታል፦ ‘አትድረስብን! መንገዶችህን ማወቅ አንፈልግም።+ 15  እናገለግለው ዘንድ ሁሉን ቻይ አምላክ ማን ነው?+ ከእሱ ጋር መተዋወቃችን ምን ይጠቅመናል?’+ 16  ሆኖም ብልጽግናቸው በእነሱ ቁጥጥር ሥር እንዳልሆነ አውቃለሁ።+ የክፉዎች ሐሳብ* ከእኔ የራቀች ናት።+ 17  የክፉዎች መብራት የጠፋው ስንት ጊዜ ነው?+ መዓት የደረሰባቸውስ ስንት ጊዜ ነው? አምላክ ተቆጥቶ ጥፋት የላከባቸው ስንት ጊዜ ነው? 18  ለመሆኑ በነፋስ ፊት እንዳለ ገለባ፣አውሎ ነፋስም እንደሚወስደው እብቅ ሆነው ያውቃሉ? 19  አምላክ አንድ ሰው የሚደርስበትን ቅጣት ለገዛ ልጆቹ ያከማቻል። ይሁንና ሰውየው ያውቀው ዘንድ አምላክ ብድራቱን ይክፈለው።+ 20  የገዛ ዓይኖቹ የሚደርስበትን ጥፋት ይዩ፤ደግሞም ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ቁጣ ይጠጣ።+ 21  የወራቱ ቁጥር ቢያጥር፣*+እሱ ከሄደ በኋላ በቤቱ ላይ ስለሚደርሰው ነገር ምን ግድ ይሰጠዋል? 22  ከፍ ባሉት ላይ እንኳ የሚፈርደው አምላክ ሆኖ ሳለ፣+ለእሱ እውቀት ሊሰጠው* የሚችል ይኖራል?+ 23  አንድ ሰው ሙሉ ብርታት እያለው፣ተረጋግቶና ያላንዳች ጭንቀት እየኖረ ሳለ ይሞታል፤+ 24  ጭኑ በስብ ተሞልቶ፣አጥንቶቹም ጠንካራ ሆነው* እያለ በሞት ይለያል። 25  ሌላው ሰው ግን አንዳች ጥሩ ነገር ሳይቀምስ፣በጭንቀት እንደተዋጠ* ይሞታል። 26  ሁለቱም በአንድነት አፈር ውስጥ ይጋደማሉ፤+ትሎችም ይሸፍኗቸዋል።+ 27  እነሆ፣ እናንተ የምታስቡትን፣እኔንም ለመጉዳት* የጠነሰሳችሁትን ሴራ በሚገባ አውቃለሁ።+ 28  እናንተ ‘የተከበረው ሰው ቤት የት አለ?ክፉው ሰው የኖረበት ድንኳንስ የት አለ?’ ትላላችሁና።+ 29  መንገደኞችን አልጠየቃችሁም? እነሱ የሰጧቸውን አስተያየቶችስ* በሚገባ አልመረመራችሁም? 30  ክፉ ሰው በጥፋት ቀን ይተርፍ የለ?በቁጣስ ቀን ይድን የለ? 31  ተግባሩን ፊት ለፊት የሚነግረው ማን ነው?ለሠራውስ ነገር ብድራቱን የሚከፍለው ማን ነው? 32  እሱ ወደ መቃብር ቦታ ሲወሰድ፣መቃብሩ ጥበቃ ይደረግለታል። 33  የሸለቆ* ጓል ይጣፍጠዋል፤+ደግሞም ከእሱ በፊት እንደነበሩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ሁሉ፣የሰው ዘር በሙሉ ይከተለዋል።*+ 34  ታዲያ ትርጉም የለሽ ማጽናኛ የምትሰጡኝ ለምንድን ነው?+ የምትሰጡት መልስ ሁሉ ማታለያ ነው!”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የመንፈሴ።”
ወይም “ኃያል።”
ወይም “በእምቢልታም ድምፅ።”
ወይም “በቅጽበትም።” ያለምንም ሥቃይ ወዲያው መሞታቸውን ያመለክታል።
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ምክር፤ ዕቅድ።”
ወይም “ለሁለት ቢከፈል።”
ወይም “እሱን አንዳች ነገር ሊያስተምረው።”
ቃል በቃል “የአጥንቶቹ መቅኒም እርጥብ (ሆኖ)።”
ወይም “ነፍሱ እንደተመረረች።”
“በእኔ ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ምልክቶችስ።”
ወይም “የደረቅ ወንዝ።”
ቃል በቃል “የሰውን ዘር ሁሉ ከኋላው ይጎትታል።”