ኢዮብ 24:1-25

  • ኢዮብ መልስ መስጠቱን ቀጠለ (1-25)

    • “አምላክ ለምን ጊዜ አልወሰነም?” (1)

    • አምላክ ክፋትን እንደሚፈቅድ ተናገረ (12)

    • ኃጢአተኞች ጨለማን ይወዳሉ (13-17)

24  “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ለምን ጊዜ አልወሰነም?+ እሱን የሚያውቁትስ ቀኑን* ለምን አያዩም?  2  ሰዎች የወሰን ምልክቶችን ይገፋሉ፤+ነጥቀው የወሰዱትን መንጋ በራሳቸው መስክ ላይ ያሰማራሉ።  3  አባት የሌላቸውን ልጆች አህያ እየነዱ ይወስዳሉ፤የመበለቲቱንም በሬ መያዣ አድርገው ይወስዳሉ።+  4  ድሃውን ከመንገድ ያስወጣሉ፤በዚህ ጊዜ የምድሪቱ ምስኪኖች ከእነሱ ለመሸሸግ ይገደዳሉ።+  5  ድሆች በምድረ በዳ እንዳሉ የዱር አህዮች፣+ ምግብ ፍለጋ ይራወጣሉ፤በበረሃ ለልጆቻቸው ምግብ ይፈልጋሉ።  6  ከሌላው ሰው እርሻ እህል* ለመሰብሰብ ይገደዳሉ፤ከክፉውም ሰው የወይን እርሻ ይቃርማሉ።  7  ያለልብስ ራቁታቸውን ያድራሉ፤+ብርድ የሚከላከሉበት ልብስ የላቸውም።  8  ከተራሮች በሚወርደው ዝናብ ይበሰብሳሉ፤መጠለያ ስለማያገኙ ዓለት ያቅፋሉ።  9  አባት የሌለው ልጅ ከእናቱ ጡት ላይ ተነጥቋል፤+የድሃውም ልብስ በመያዣነት ተወስዷል፤+ 10  ያለልብስ ራቁታቸውን ለመሄድ ይገደዳሉ፤ተርበው እያሉም ነዶ ተሸክመው ይሄዳሉ። 11  በቀትር ሐሩር በእርከኖቹ መካከል ይለፋሉ፤*የወይን መጭመቂያውን እየረገጡ እነሱ ግን ይጠማሉ።+ 12  በሞት አፋፍ ላይ ያሉት በከተማዋ ውስጥ ያጣጥራሉ፤ክፉኛም የቆሰሉት ሰዎች* እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ፤+አምላክ ግን ይህን በቸልታ ያልፋል።* 13  በብርሃን ላይ የሚያምፁ አሉ፤+የብርሃኑን መንገድ አላወቁም፤ጎዳናውንም አልተከተሉም። 14  ነፍሰ ገዳዩ ጎህ ሲቀድ ይነሳል፤ምስኪኑንና ድሃውን ይገድላል፤+በሌሊትም ይሰርቃል። 15  የአመንዝራ ዓይን ድንግዝግዝታን ይጠባበቃል፤+‘ማንም አያየኝም!’ ይላል፤+ ፊቱንም ይሸፍናል። 16  በጨለማ ቤት ሰብረው* ይገባሉ፤ቀን ላይ ተሸሽገው ይውላሉ። ለብርሃን እንግዳ ናቸው።+ 17  ለእነሱ ንጋት እንደ ድቅድቅ ጨለማ ነውና፤ድቅድቅ ጨለማ የሚያስከትለውን ሽብር ያውቁታል። 18  ይሁንና ውኃ በፍጥነት ጠርጎ ይወስዳቸዋል።* ርስታቸውም የተረገመ ይሆናል።+ ወደ ወይን እርሻቸው አይመለሱም። 19  ድርቁና ሐሩሩ የቀለጠውን በረዶ እንደሚያስወግደው፣መቃብር* ኃጢአተኞችን ይነጥቃል!+ 20  እናቱ* ትረሳዋለች፤ ትልም ትመጠምጠዋለች። ዳግመኛ አይታወስም።+ ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል። 21  በመሃኒቱ ላይ ያደባል፤መበለቲቱንም ይበድላል። 22  አምላክ* ኃይሉን ተጠቅሞ ብርቱ ሰዎችን ያጠፋል፤ከፍ ከፍ ቢሉም ሕይወታቸው ዋስትና የለውም። 23  አምላክ* የመተማመን ስሜት እንዲያድርባቸውና ደህንነት እንዲሰማቸው ይፈቅዳል፤+ይሁንና ዓይኑ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ* ላይ ነው።+ 24  ለጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ከዚያም ደብዛቸው ይጠፋል።+ ዝቅ ዝቅ ይደረጋሉ፤+ ደግሞም እንደ ማንኛውም ሰው ይሰበሰባሉ፤እንደ እህል ዛላ ይቆረጣሉ። 25  እንግዲህ አሁን እኔን ውሸታም ሊያደርገኝ፣ወይም ቃሌን ሊያስተባብል የሚችል ማን ነው?”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ይህ ቃል የፍርድ ቀኑን ያመለክታል።
“መኖ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“በእርከኖቹ መካከል ዘይት ይጨምቃሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የቆሰሉት ነፍሳት።”
“አምላክ ግን ማንንም ተጠያቂ አያደርግም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ሰርስረው።”
ቃል በቃል “እሱ በውኃ ላይ ፈጣን ነው።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ማህፀን።”
ቃል በቃል “እሱ።”
ቃል በቃል “እሱ።”
ቃል በቃል “በመንገዶቻቸው።”