ኢዮብ 31:1-40

  • ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን እንዳላጎደፈ በመግለጽ ተሟገተ (1-40)

    • “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ” (1)

    • አምላክ እንዲመዝነው ጠየቀ (6)

    • አመንዝራ አልነበረም (9-12)

    • የገንዘብ ፍቅር አልነበረውም (24, 25)

    • ጣዖት አምላኪ አልነበረም (26-28)

31  “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ።+ ታዲያ ለድንግሊቱ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት እንዴት እሰጣለሁ?+  2  ለመሆኑ ከላይ ከአምላክ የማገኘው ድርሻ ምንድን ነው?ከፍ ባለ ስፍራ ከሚኖረው ሁሉን ቻይ አምላክ የማገኘውስ ውርሻ ምንድን ነው?  3  በደለኛ ሰው ጥፋት፣ክፉ ነገር የሚያደርጉስ መቅሰፍት አይደርስባቸውም?+  4  እሱ መንገዴን ሁሉ አያይም?+እርምጃዬንስ ሁሉ አይቆጥርም?  5  በውሸት ጎዳና ተመላልሼ* አውቃለሁ? እግሬ ለማታለል ተጣድፎ ያውቃል?+  6  አምላክ በትክክለኛ ሚዛን ይመዝነኝ፤+ያን ጊዜ ንጹሕ አቋም* እንዳለኝ ይገነዘባል።+  7  እርምጃዬ ከመንገዱ ወጣ ብሎ፣+ወይም ልቤ ዓይኔን ተከትሎ፣+አሊያም እጄ ረክሶ ከሆነ፣  8  የዘራሁትን ዘር ሌላ ይብላው፤+የተከልኩትም ይነቀል።*  9  ልቤ ሌላ ሴት ከጅሎ፣+በባልንጀራዬም ደጃፍ ላይ አድብቼ ከሆነ፣+ 10  ሚስቴ ለሌላ ሰው እህል ትፍጭ፤ሌሎች ወንዶችም ከእሷ ጋር ይተኙ።*+ 11  ይህ አሳፋሪ ምግባር፣ደግሞም በዳኞች ሊያስቀጣ የሚገባ በደል በሆነ ነበርና።+ 12  ይህ የሚያጠፋና የሚደመስስ፣*የፍሬዬንም ሥር ሁሉ የሚፈጅ* እሳት በሆነ ነበር።+ 13  ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ በእኔ ላይ አቤቱታ* ባቀረቡ ጊዜፍትሕ ነፍጌ ከሆነ፣ 14  አምላክ ሲከራከረኝ* ምን ማድረግ እችላለሁ? ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ?+ 15  እኔን በማህፀን ውስጥ የሠራኝ እነሱንስ አልሠራም?+ ከመወለዳችን በፊት* የሠራን እሱ ራሱ አይደለም?+ 16  ድሃ የሆኑ ሰዎች የፈለጉትን ነገር ነፍጌ፣+ወይም የመበለቲቱ ዓይን እንዲያዝን* አድርጌ ከሆነ፣+ 17  ወላጅ አልባ ለሆኑ ልጆች ሳላካፍል፣የራሴን ምግብ ብቻዬን በልቼ ከሆነ፣+ 18  (ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅ* ከወጣትነቴ ጀምሮ እንደ አባት ሆኜ አሳድጌዋለሁና፤ከልጅነቴም* አንስቶ መበለቲቱን* ስመራት ቆይቻለሁ።) 19  ሰው የሚለብሰው አጥቶ በብርድ ሲያልቅ፣ወይም ድሃው ሲታረዝ አይቼ ከሆነ፣+ 20  ከጠቦቶቼ የተሸለተውን ፀጉር ለብሶ በሞቀው ጊዜ፣ሳይባርከኝ ቀርቶ ከሆነ፣+ 21  በከተማዋ በር+ ላይ የእኔን እርዳታ በሚፈልግ ወላጅ አልባ ልጅ ላይ*እጄን በዛቻ አወዛውዤ ከሆነ፣+ 22  ክንዴ* ከትከሻዬ ይውለቅ፤ክንዴም ከክርኔ* ይሰበር። 23  ከአምላክ የሚመጣ ጥፋት ያስፈራኛልና፤በግርማውም ፊት መቆም አልችልም። 24  ወርቅን መታመኛዬ አድርጌ፣ወይም ምርጥ የሆነውን ወርቅ ‘አንተ መመኪያዬ ነህ!’ ብዬ ከሆነ፣+ 25  ታላቅ ሀብት በማፍራቴ፣እንዲሁም ብዙ ንብረት በማግኘቴ ደስ ብሎኝ ከሆነ፣+ 26  ፀሐይ ስትፈነጥቅ፣*ወይም ጨረቃ ግርማ ተላብሳ ስትሄድ አይቼ ከሆነ፣+ 27  ልቤ በስውር ተታሎ፣አፌም ለእነሱ አምልኮ ለማቅረብ እጄን ስሞ ከሆነ፣+ 28  ይህ በዳኞች ሊያስቀጣ የሚገባ በደል በሆነ ነበር፤በላይ ያለውን እውነተኛውን አምላክ መካድ ይሆንብኝ ነበርና። 29  ጠላቴ በደረሰበት ጥፋት ደስ ብሎኝ ያውቃል?+ወይስ ክፉ ነገር ስለደረሰበት ሐሴት አድርጌ አውቃለሁ? 30  በእርግማን ሕይወቱን* በመሻት፣አንደበቴ ኃጢአት እንዲሠራ አልፈቀድኩም።+ 31  በድንኳኔ የሚኖሩ ሰዎች‘እሱ ካቀረበው ምግብ* በልቶ ያልጠገበ ሰው ማግኘት የሚችል ማን አለ?’ አላሉም?+ 32  አንድም እንግዳ* ደጅ አያድርም ነበር፤+ቤቴን ለመንገደኛ እከፍት ነበር። 33  በደሌን በልብሴ ኪስ በመሸሸግ፣እንደ ሌሎች ሰዎች ጥፋቴን ለመሸፋፈን ሞክሬ አውቃለሁ?+ 34  የብዙ ሰዎችን ምላሽ በመፍራት፣ወይም በሌሎች ቤተሰቦች ንቀት በመሸበር፣ዝም ብያለሁ? ደግሞስ ወደ ውጭ መውጣት ፈርቻለሁ? 35  ምነው የሚሰማኝ ባገኘሁ!+ በተናገርኩት ነገር ላይ ስሜን አሰፍር ነበር።* ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ መልስ ይስጠኝ!+ ምነው ከሳሼ ክሱን በሰነድ ላይ ባሰፈረ ኖሮ! 36  በትከሻዬ እሸከመው ነበር፤እንደ አክሊልም በራሴ ላይ አስረው ነበር። 37  የወሰድኩትን እያንዳንዱን እርምጃ ባሳወቅኩት ነበር፤እንደ አለቃ በልበ ሙሉነት ወደ እሱ እቀርብ ነበር። 38  እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ፣ትልሞቿም በአንድ ላይ አልቅሰው ከሆነ፣ 39  ፍሬዋን ያለዋጋ በልቼ፣+ባለቤቶቿንም* አሳዝኜ ከሆነ፣+ 40  በስንዴ ፋንታ እሾህ፣በገብስም ምትክ የሚገማ አረም ይብቀልብኝ።” የኢዮብ ቃል እዚህ ላይ ተፈጸመ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ከሚዋሹ ሰዎች ጋር ሄጄ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ኢዮብ 2:9 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “ዘሮቼም ይነቀሉ።”
ቃል በቃል “ሌሎች ወንዶችም በእሷ ላይ ይንበርከኩ።”
ቃል በቃል “በልቶ (ውጦ) የሚያወድም።”
ወይም “የሚነቅል።”
ወይም “ሙግታቸውን።”
ቃል በቃል “ሲነሳ።”
ቃል በቃል “በማህፀን ውስጥ።”
ቃል በቃል “እንዲደክም።”
ቃል በቃል “እሱን።”
ቃል በቃል “ከእናቴም ማህፀን።”
ቃል በቃል “እሷን።”
“በከተማዋ በር ላይ ደጋፊ እንዳለኝ አይቼ ወላጅ አልባ በሆነው ልጅ ላይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ብራኳዬ።”
ወይም “ከመጋጠሚያው፤ ከላይኛው አጥንት።”
ቃል በቃል “ብርሃን (ሲፈነጥቅ)።”
ወይም “ነፍሱን።”
ቃል በቃል “ሥጋ።”
ወይም “የባዕድ አገር ሰው።”
ወይም “ፊርማዬ ይኸውና።”
ወይም “የባለቤቶቿንም ነፍስ።”