ኤርምያስ 10:1-25

  • የብሔራት አማልክትና ሕያው የሆነው አምላክ (1-16)

  • የሚጠፉበትና የሚማረኩበት ጊዜ ተቃረበ (17, 18)

  • ኤርምያስ እጅግ አዘነ (19-22)

  • ነቢዩ ያቀረበው ጸሎት (23-25)

    • ሰው አካሄዱን አቃንቶ መምራት አይችልም (23)

10  የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ይሖዋ በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ። 2  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የብሔራትን መንገድ አትማሩ፤+በሰማያት ምልክቶችም አትሸበሩ፤ምክንያቱም ብሔራት በእነዚህ ነገሮች ተሸብረዋል።+  3  የእነዚህ ሕዝቦች ልማድ ከንቱ* ነውና፤ የእጅ ጥበብ ባለሙያ ዛፍ ከጫካ ይቆርጥናበመሣሪያው* ጠርቦ ጣዖት ይሠራል።+  4  በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፤+እንዳይወድቅም በመዶሻና በምስማር ይቸነክሩታል።+  5  እነሱ በኪያር እርሻ ውስጥ ለወፍ ማስፈራሪያነት እንደሚተከል ማስፈራርቾ መናገር አይችሉም፤+መራመድ ስለማይችሉ ተሸካሚ ያስፈልጋቸዋል።+ ጉዳት ማድረስም ሆነምንም ዓይነት መልካም ነገር መሥራት ስለማይችሉ አትፍሯቸው።”+  6  ይሖዋ ሆይ፣ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም።+ አንተ ታላቅ ነህ፤ ስምህም ታላቅና ኃያል ነው።  7  የብሔራት ንጉሥ ሆይ፣+ አንተን የማይፈራ ማን ነው? አንተ ልትፈራ ይገባሃልና፤ምክንያቱም ከብሔራት ጠቢባን ሁሉ እንዲሁም ከመንግሥቶቻቸው ሁሉ መካከልእንደ አንተ ያለ ማንም የለም።+  8  ሁሉም የማመዛዘን ችሎታ የጎደላቸውና ሞኞች ናቸው።+ ከእንጨት ምስል የሚመጣ መመሪያ ፈጽሞ ከንቱ* ነው።+  9  በእጅ ጥበብ ባለሙያና በአንጥረኛ የተሠራየተጠፈጠፈ ብር ከተርሴስ፣+ ወርቅም ከዑፋዝ ይመጣል። ልብሳቸው በሰማያዊ ክርና በሐምራዊ ሱፍ የተሠራ ነው። ሁሉም በባለሙያዎች የተሠሩ ናቸው። 10  ይሖዋ ግን እውነተኛ አምላክ ነው። እሱ ሕያው አምላክና+ ዘላለማዊ ንጉሥ ነው።+ ከቁጣው የተነሳ ምድር ትናወጣለች፤+የእሱን ውግዘት ሊቋቋም የሚችል አንድም ብሔር የለም። 11  * እናንተ እንዲህ በሏቸው፦ “ሰማያትንና ምድርን ያልሠሩት አማልክትከምድር ገጽ፣ ከእነዚህም ሰማያት በታች ይጠፋሉ።”+ 12  ምድርን በኃይሉ የሠራው፣ፍሬያማ የሆነችውን መሬት በጥበቡ የመሠረተውና+ሰማያትን በማስተዋሉ የዘረጋው እሱ ነው።+ 13  ድምፁን ሲያሰማበሰማያት ያሉ ውኃዎች ይናወጣሉ፤+ደመና* ከምድር ዳርቻዎች ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርጋል።+ በዝናብ ጊዜ መብረቅን ያበርቃል፤*ነፋሱንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።+ 14  እያንዳንዱ ሰው ማስተዋልና እውቀት የጎደለው ድርጊት ይፈጽማል። እያንዳንዱ አንጥረኛ፣ በተቀረጸው ምስል የተነሳ ኀፍረት ይከናነባል፤+ከብረት የተሠራው ምስሉ* ሐሰት ነውና፤በውስጣቸውም መንፈስ* የለም።+ 15  እነሱ ከንቱና* መሳለቂያ ናቸው።+ የሚመረመሩበት ቀን ሲመጣ ይጠፋሉ። 16  የያዕቆብ ድርሻ ግን እንደነዚህ ነገሮች አይደለም፤እሱ የሁሉ ነገር ሠሪ ነውና፤እስራኤልም የርስቱ በትር ነው።+ ስሙ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው።+ 17  አንቺ የተከበብሽ ሴት፣ጓዝሽን ከመሬት ላይ ሰብስቢ። 18  ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “እነሆ፣ በዚህ ጊዜ ነዋሪዎቹን ከምድሪቱ ውጭ እወረውራቸዋለሁ፤*+ጭንቀት እንዲይዛቸውም አደርጋለሁ።” 19  ስብራት* ደርሶብኛልና ወዮልኝ!+ ቁስሌ የማይድን ነው። እኔም እንዲህ አልኩ፦ “በእርግጥ ይህ የእኔ ሕመም ነው፤ ልሸከመውም ይገባል። 20  ድንኳኔ ፈርሷል፤ የድንኳኔም ገመዶች ሁሉ ተበጥሰዋል።+ ወንዶች ልጆቼ ጥለውኝ ሄደዋል፤ ከዚህ በኋላ አይኖሩም።+ ድንኳኔን የሚተክልልኝ ወይም የድንኳኔን ሸራዎች የሚዘረጋልኝ አንድም ሰው የለም። 21  እረኞቹ የሞኝነት ድርጊት ፈጽመዋልና፤+ይሖዋንም አልጠየቁም።+ ማስተዋል የጎደለው ድርጊት የፈጸሙት ለዚህ ነው፤መንጎቻቸውም ሁሉ ተበታትነዋል።”+ 22  አዳምጡ! አንድ ወሬ ስሙ! ወደዚህ እየመጣ ነው! የይሁዳን ከተሞች ባድማና የቀበሮዎች ጎሬ ሊያደርግ+ከሰሜን ምድር ድም፣ ድም የሚል ኃይለኛ ድምፅ እየቀረበ ነው።+ 23  ይሖዋ ሆይ፣ የሰው መንገድ በራሱ እጅ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።+ 24  ይሖዋ ሆይ፣ አርመኝ፤ሆኖም ፈጽመህ እንዳታጠፋኝ+ በፍትሕ እንጂ በቁጣህ አይሁን።+ 25  አንተን ችላ በሚሉ ብሔራት+እንዲሁም ስምህን በማይጠሩ ነገዶች ላይ ቁጣህን አፍስስ። ያዕቆብን በልተውታልና፤+አዎ፣ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስ በልተውታል፤+የትውልድ አገሩንም አውድመዋል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ዋጋ ቢስ።”
ወይም “በገጀራው።”
ወይም “ዋጋ ቢስ።”
ኤር 10:11 በመጀመሪያ የተጻፈው በአረማይክ ነበር።
“ለዝናብ መውጫ ያዘጋጃል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ተን።”
ወይም “ቀልጦ የተሠራው ሐውልቱ።”
ወይም “እስትንፋስ።”
ወይም “ዋጋ ቢስና።”
ወይም “እወነጭፋቸዋለሁ።”
ወይም “ስንጥቅ።”