ኤርምያስ 11:1-23

  • ይሁዳ ከአምላክ ጋር የገባችውን ቃል ኪዳን አፈረሰች (1-17)

    • “አማልክትህ የከተሞችህን ያህል በዝተዋል” (13)

  • ኤርምያስ ለመታረድ እንደሚነዳ በግ ሆነ (18-20)

  • ኤርምያስ ከአገሩ ሰዎች ተቃውሞ ገጠመው (21-23)

11  ከይሖዋ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦  “እናንተ ሰዎች፣ የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ! “ለይሁዳ ሰዎችና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ቃሉን ተናገር፤*  እንዲህም በላቸው፦ ‘የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የዚህን ቃል ኪዳን ቃል የማይታዘዝ ሰው የተረገመ ነው፤+  ይህም አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር፣ ከብረት ማቅለጫ ምድጃው ባወጣኋቸው ጊዜ+ እንዲህ ብዬ ያዘዝኳቸው ቃል ነው፦+ ‘ድምፄን ስሙ፤ ያዘዝኳችሁንም ነገር ሁሉ አድርጉ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ፤+  ይህም ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ለመስጠት ለአባቶቻችሁ የገባሁትን መሐላ ለመፈጸም ነው።’”’”+ እኔም “ይሖዋ ሆይ፣ አሜን”* ብዬ መለስኩ።  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህን ቃላት ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ አውጅ፦ ‘የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ፤ በሥራም ላይ አውሉት።  አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ “ድምፄን ስሙ” በማለት ደግሜ ደጋግሜ* አጥብቄ ሳሳስባቸው ነበርና።+  እነሱ ግን አልሰሙም ወይም ጆሯቸውን አልሰጡም፤ ከዚህ ይልቅ እያንዳንዳቸው ግትር ሆነው የገዛ ክፉ ልባቸውን ተከተሉ።+ ስለዚህ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ያዘዝኳቸውንና እነሱ ሥራ ላይ ያላዋሉትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ሁሉ በእነሱ ላይ አመጣሁባቸው።’”  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ “የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሴራ ጠንስሰዋል። 10  ቃሌን ያልታዘዙት የቀድሞ አባቶቻቸው ይፈጽሙት ወደነበረው በደል ተመልሰዋል።+ እነሱም ሌሎች አማልክትን ተከትለዋል፤ ደግሞም አገልግለዋል።+ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት ከአባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል።+ 11  ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ ማምለጥ የማይችሉትን ጥፋት አመጣባቸዋለሁ።+ እርዳታ ለማግኘት ወደ እኔ ሲጮኹ አልሰማቸውም።+ 12  ከዚያም የይሁዳ ከተሞችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች መሥዋዕት* ወደሚያቀርቡላቸው አማልክት ሄደው እርዳታ ይጠይቃሉ፤+ ሆኖም ጥፋት በሚደርስባቸው ጊዜ ፈጽሞ አያድኗቸውም። 13  ይሁዳ ሆይ፣ አማልክትህ የከተሞችህን ያህል በዝተዋልና፤ ለአሳፋሪው ነገር* ይኸውም ለባአል መሥዋዕት ለማቅረብ የኢየሩሳሌምን ጎዳናዎች ያህል ብዛት ያላቸው መሠዊያዎች ሠርታችኋል።’+ 14  “አንተም* ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ። ስለ እነሱ የልመና ጩኸትም ሆነ ጸሎት አታሰማ፤+ ጥፋት ደርሶባቸው ወደ እኔ ሲጮኹ አልሰማቸውምና። 15  ብዙዎቹ የሸረቡትን ክፉ ሐሳብ እየፈጸሙ ሳለ፣ውዴ በቤቴ ለመገኘት ምን መብት አላት? ጥፋት በአንቺ ላይ ሲመጣ በቅዱስ ሥጋ* ጥፋቱን ሊከላከሉልሽ ይችላሉ? በዚያን ጊዜ ሐሴት ታደርጊ ይሆን? 16  በአንድ ወቅት ይሖዋ በመልካም ፍሬ የተዋበ፣የለመለመ የወይራ ዛፍ ብሎ ጠርቶሽ ነበር። በሚያስገመግም ታላቅ ድምፅ፣ በእሳት አነደዳት፤እነሱም ቅርንጫፎቿን ሰባበሩ። 17  “የተከለሽ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣+ ለባአል መሥዋዕት በማቅረብ እኔን ያስከፉኝ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት በሠሩት ክፉ ነገር የተነሳ በአንቺ ላይ ጥፋት እንደሚመጣ አስታውቋል።”+ 18  ይሖዋ ይህን እንዳውቅ ገለጠልኝ፤አምላክ ሆይ፣ በዚያን ጊዜ የፈጸሙትን ነገር እንዳይ አደረግከኝ። 19  እኔ ለመታረድ እንደሚነዳ የዋህ የበግ ጠቦት ነበርኩ። “ዛፉን ከነፍሬው እናጥፋው፤ ከእንግዲህም ወዲያ ስሙ እንዳይታወስከሕያዋን ምድር እናስወግደው” ብለውበእኔ ላይ ሴራ እንደጠነሰሱ አላወቅኩም ነበር።+ 20  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ግን በጽድቅ ይፈርዳል፤የውስጥ ሐሳብንና* ልብን ይመረምራል።+ አምላክ ሆይ፣ በእነሱ ላይ የምትወስደውን የበቀል እርምጃ እንዳይ አድርገኝ፤ጉዳዬን ለአንተ አቅርቤአለሁና። 21  ስለዚህ ይሖዋ ሕይወትህን ለማጥፋት በሚሹ* በአናቶት+ ሰዎች ላይ ይህን ቃል ተናግሯል፤ እነሱ “በይሖዋ ስም ትንቢት አትናገር፤+ አለዚያ በእጃችን ትጠፋለህ” ይላሉ፤ 22  ስለዚህ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ እነሱን ተጠያቂ አደርጋለሁ። ወጣት ወንዶቹ በሰይፍ ይወድቃሉ፤+ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው በረሃብ ያልቃሉ።+ 23  እነሱን ተጠያቂ በማደርግበት ዓመት፣ በአናቶት+ ሰዎች ላይ ጥፋት ስለማመጣ ከእነሱ መካከል የሚተርፍ አንድም ሰው አይኖርም።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ለኤርምያስ የተነገረ ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “ይሁን።”
ቃል በቃል “በማለዳ እየተነሳሁ።”
ወይም “የሚጨስ መሥዋዕት።”
ወይም “ለአሳፋሪው አምላክ።”
ኤርምያስን ያመለክታል።
በቤተ መቅደሱ የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች ያመለክታል።
ወይም “ጥልቅ ስሜትንና።” ቃል በቃል “ኩላሊትንና።”
ወይም “ነፍስህን በሚሿት።”