ኤርምያስ 12:1-17

  • ኤርምያስ አቤቱታ አቀረበ (1-4)

  • ይሖዋ የሰጠው መልስ (5-17)

12  ይሖዋ ሆይ፣ አቤቱታዬን ለአንተ ሳቀርብ፣ከፍትሕ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ሳናግርህ እነሆ፣ አንተ ጻድቅ ነህ።+ ታዲያ የክፉዎች መንገድ ለምን ይሰምራል?+ደግሞስ ከዳተኞች ሳይጨነቁ የሚኖሩት ለምንድን ነው?   አንተ ተክለሃቸዋል፤ እነሱም ሥር ሰደዋል። አድገዋል፤ ፍሬም አፍርተዋል። ከከንፈራቸው አይለዩህም፤ የውስጥ ሐሳባቸው* ግን ከአንተ የራቀ ነው።+   ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን በሚገባ ታውቀኛለህ፤+ ታየኛለህም፤ልቤን መረመርክ፤ ከአንተም ጋር የሚስማማ ሆኖ አገኘኸው።+ ለእርድ እንደተዘጋጁ በጎች ለያቸው፤ለሚገደሉበትም ቀን ለይተህ አቆያቸው።   ምድሪቱ ተራቁታ፣የሜዳውም ተክል ሁሉ ደርቆ የሚቆየው እስከ መቼ ድረስ ነው?+ በምድሪቱ በሚኖሩት ሰዎች ክፋት የተነሳአራዊቱና ወፎቹ ተጠራርገው ጠፉ። እነሱ፣ “ወደፊት ምን እንደሚገጥመን አያውቅም” ብለዋልና።   ከእግረኞች ጋር ሮጠህ ከደከምክ፣ከፈረሶች ጋር እንዴት ልትወዳደር ትችላለህ?+ በሰላም ምድር ተማምነህ ብትቀመጥ እንኳጥቅጥቅ ባለው የዮርዳኖስ ጥሻ ውስጥ እንዴት ልትሆን ነው?   የገዛ ወንድሞችህ፣የገዛ አባትህ ቤተሰቦች እንኳ አታለውሃልና።+ እነሱ በአንተ ላይ ጮኸዋል። መልካም ነገር ቢናገሩህ እንኳፈጽሞ አትመናቸው።   “ቤቴን ትቻለሁ፤+ ርስቴን ጥዬ ሄጃለሁ።+ እጅግ የምወዳትን* በጠላቶቿ እጅ አሳልፌ ሰጥቻታለሁ።+   ርስቴ በጫካ ውስጥ እንዳለ አንበሳ ሆነችብኝ። በእኔ ላይ ጮኻብኛለች። በዚህም የተነሳ ጠላኋት።   ርስቴ ለእኔ ብዙ ቀለማት እንዳለው* አዳኝ አሞራ ነች፤ሌሎች አዳኝ አሞሮች ይከቧታል፤ ደግሞም ያጠቋታል።+ እናንተ የዱር አራዊት ሁሉ ኑ፤ በአንድነት ተሰብሰቡ፤ትቀራመቷት ዘንድ ኑ።+ 10  ብዙ እረኞች የወይን እርሻዬን አጥፍተውታል፤+ይዞታዬንም ረግጠውታል።+ የተወደደውን ይዞታዬን ጠፍ ምድረ በዳ አድርገውታል። 11  ባድማ ሆኗል። ደግሞም ተራቁቷል፤*በፊቴ ወና ሆኗል።+ ምድሪቱ በሙሉ ባድማ ሆናለች፤ይሁንና ይህን ልብ ያለ አንድም ሰው የለም።+ 12  በምድረ በዳ ባሉት፣ በተበላሹ መንገዶች ሁሉ አጥፊዎች መጥተዋል፤የይሖዋ ሰይፍ ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ድረስ ምድሪቱን ትበላለችና።+ ማንም ሰው* ሰላም የለውም። 13  ስንዴ ዘሩ፤ ሆኖም እሾህን አጨዱ።+ እስኪዝሉ ድረስ ሠሩ፤ ነገር ግን ምንም ጥቅም አላገኙም። ከሚነደው የይሖዋ ቁጣ የተነሳበሚያገኙት ምርት ያፍራሉ።” 14  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ እስራኤል እንዲወርሰው ያደረግኩትን ርስት የሚነኩ ክፉ ጎረቤቶቼን ሁሉ+ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፤+ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅላለሁ። 15  ከነቀልኳቸው በኋላ ግን ዳግመኛ ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤ እያንዳንዳቸውን ወደየርስታቸው፣ እያንዳንዳቸውንም ወደየምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።” 16  “ሕዝቤን በባአል እንዲምሉ እንዳስተማሩ ሁሉ እነሱም የሕዝቤን መንገድ በእርግጥ ቢማሩና ‘ሕያው ይሖዋን!’ ብለው በስሜ ቢምሉ በሕዝቤ መካከል ጸንተው ይኖራሉ። 17  ይሁንና ከእነዚህ ብሔራት መካከል የማይታዘዝ ቢኖር ያን ብሔር እነቅለዋለሁ፤ ነቅዬም አጠፋዋለሁ” ይላል ይሖዋ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጥልቅ ስሜታቸው።” ቃል በቃል “ኩላሊታቸው።”
ወይም “ነፍሴ እጅግ የምትወዳትን።”
ወይም “እንደ ዥጉርጉር።”
“ያለቅሳል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ሥጋ ሁሉ።”