ኤርምያስ 14:1-22

  • ድርቅ፣ ረሃብና ሰይፍ (1-12)

  • ሐሰተኛ ነቢያት ተወገዙ (13-18)

  • ኤርምያስ ሕዝቡ ኃጢአት መሥራቱን አምኖ ተቀበለ (19-22)

14  ድርቅን አስመልክቶ ወደ ኤርምያስ የመጣው የይሖዋ ቃል ይህ ነው፦+   ይሁዳ ታለቅሳለች፤+ በሮቿም ወላልቀዋል። በሐዘን ተውጠው መሬት ላይ ይቀመጣሉ፤ከኢየሩሳሌምም ጩኸት ይሰማል።   ጌቶቻቸውም አገልጋዮቻቸውን* ውኃ እንዲፈልጉ ላኳቸው። እነሱም ወደ ውኃ ጉድጓዶቹ* ሄዱ፤ ውኃ ግን አላገኙም። ባዶ ዕቃ ይዘው ተመለሱ። በኀፍረት ተዋጡ፤ ተስፋም ቆረጡ፤ራሳቸውንም ተከናነቡ።   በምድሪቱ ላይ ዝናብ ባለመዝነቡ የተነሳመሬቱ ስለተሰነጣጠቀ+ገበሬዎቹ እጅግ አዘኑ፤ ራሳቸውንም ተከናነቡ።   በሜዳ ያለች እንስት ርኤም* እንኳምንም ሣር ባለመኖሩ እንደወለደች ግልገሏን ጥላ ትሄዳለች።   የዱር አህዮች በተራቆቱ ኮረብቶች ላይ ይቆማሉ። እንደ ቀበሮ አየር አጥሯቸው ያለከልካሉ፤ምንም ዓይነት ተክል ባለመኖሩ ዓይኖቻቸው ፈዘዙ።+   ይሖዋ ሆይ፣ የገዛ ራሳችን በደል በእኛ ላይ የሚመሠክርብን ቢሆንምለስምህ ስትል እርምጃ ውሰድ።+ የክህደት ሥራችን በዝቷልና፤+ኃጢአት የሠራነውም በአንተ ላይ ነው።   አንተ የእስራኤል ተስፋ፣ በጭንቀትም ጊዜ አዳኙ+ የሆንክ ሆይ፣በምድሪቱ እንደ እንግዳ፣ሌሊቱን ለማሳለፍ ሲል ብቻ ጎራ እንዳለ መንገደኛ የሆንከው ለምንድን ነው?   ክው ብሎ እንደቀረ ሰው፣ማዳን እንደማይችል ኃያል ሰው የሆንከው ለምንድን ነው? ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በመካከላችን ነህና፤+እኛም በስምህ ተጠርተናል።+ እባክህ አትተወን። 10  ይሖዋ ይህን ሕዝብ አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “መቅበዝበዝ ይወዳሉ፤+ እግራቸውን አልሰበሰቡም።+ ስለዚህ ይሖዋ በእነሱ ደስ አይሰኝም።+ አሁን በደላቸውን ያስባል፤ በኃጢአታቸውም የተነሳ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።”+ 11  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ “ይህ ሕዝብ መልካም ሁኔታ እንዲገጥመው አትጸልይ።+ 12  በሚጾሙበት ጊዜ የሚያቀርቡትን ልመና አልሰማም፤+ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠሉ መባዎችና የእህል መባዎች በሚያቀርቡበት ጊዜም በእነሱ ደስ አልሰኝም፤+ በሰይፍ፣ በረሃብና በቸነፈር* አጠፋቸዋለሁና።”+ 13  በዚህ ጊዜ እንዲህ አልኩ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ወዮ! እነሆ፣ ነቢያቱ ‘ሰይፍ አታዩም፤ ለረሃብም አትዳረጉም፤ ከዚህ ይልቅ በዚህ ስፍራ እውነተኛ ሰላም እሰጣችኋለሁ’ ይሏቸዋል።”+ 14  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ።+ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኳቸውም ወይም አላናገርኳቸውም።+ የሐሰት ራእይን፣ ከንቱ የሆነ ሟርትንና የገዛ ልባቸውን ማታለያ ይተነብዩላችኋል።+ 15  ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ ሳልካቸው በስሜ የሚተነብዩትና በዚህች ምድር ላይ ሰይፍም ሆነ ረሃብ አይከሰትም የሚሉት እነዚህ ነቢያት በሰይፍና በረሃብ ይጠፋሉ።+ 16  የሚተነብዩለትም ሕዝብ ከረሃቡና ከሰይፉ የተነሳ አስከሬኑ በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ ይጣላል፤ እነሱን፣ አዎ እነሱን፣ ሚስቶቻቸውን፣ ወንዶች ልጆቻቸውንም ሆነ ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቀብራቸው አይኖርም፤+ የሚገባቸውን ጥፋት በላያቸው ላይ አመጣለሁና።’+ 17  “ይህን ቃል ንገራቸው፦‘ዓይኖቼ ሌት ተቀን ሳያቋርጡ እንባ ያፍስሱ፤+ድንግሊቱ የሕዝቤ ሴት ልጅ እጅግ አስከፊ በሆነ ቁስል ሙሉ በሙሉ ደቃለችና፤ደግሞም ተሰብራለች።+ 18  ወደ መስክ ብወጣ፣እነሆ፣ በሰይፍ የተገደሉትን አያለሁ!+ ወደ ከተማም ብገባ፣በረሃብ የተነሳ የታመሙ ሰዎችን አያለሁ!+ ነቢዩና ካህኑ በማያውቁት አገር ተቅበዝብዘዋልና።’”+ 19  ይሁዳን ጨርሶ ትተኸዋል? ወይስ ጽዮንን ተጸይፈሃታል?*+ ታዲያ ፈውስ እስከማይገኝልን ድረስ የመታኸን ለምንድን ነው?+ ሰላምን ተስፋ አደረግን፤ ሆኖም መልካም ነገር አልመጣም፤የፈውስ ጊዜ ይመጣል ብለን ጠበቅን፤ ነገር ግን ሽብር ነገሠ!+ 20  ይሖዋ ሆይ፣ ክፋት መሥራታችንን፣አባቶቻችንም በደል መፈጸማቸውን አምነን እንቀበላለን፤በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና።+ 21  ስለ ስምህ ስትል አትናቀን፤+ክብር የተላበሰውን ዙፋንህን አታቃልል። ከእኛ ጋር የገባኸውን ቃል ኪዳን አስታውስ፤ አታፍርሰውም።+ 22  ከንቱ ከሆኑት የአሕዛብ ጣዖቶች መካከል ዝናብ ሊያዘንብ የሚችል አለ?ሰማያትስ በራሳቸው ዝናብ ማውረድ ይችላሉ? አምላካችን ይሖዋ ሆይ፣ ይህን የምታደርገው አንተ ብቻ አይደለህም?+ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረግከው አንተ ብቻ ስለሆንክአንተን ተስፋ እናደርጋለን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ታናናሾቻቸውን።”
ወይም “ወደ ቦዮቹ፤ ወደ ውኃ ማጠራቀሚያዎቹ።”
ቅርንጫፍ የሚመስሉ ቀንዶች ያሉት አጥቢ እንስሳ፤ ከአጋዘን ጋር ይመሳሰላል።
ወይም “በበሽታ።”
ወይም “ነፍስህ ተጸይፋታለች?”