ኤርምያስ 15:1-21

  • ይሖዋ ፍርዱን አይለውጥም (1-9)

  • የኤርምያስ ስሞታ (10)

  • ይሖዋ የሰጠው መልስ (11-14)

  • ኤርምያስ ያቀረበው ጸሎት (15-18)

    • የአምላክን ቃል መብላት የሚያስገኘው ደስታ (16)

  • ይሖዋ ኤርምያስን አበረታታው (19-21)

15  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ “ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙ እንኳ+ ለዚህ ሕዝብ አልራራም።* ከፊቴ አስወጣቸው። ይሂዱ።  እነሱም ‘ወዴት እንሂድ?’ ቢሉህ፣ እንዲህ በላቸው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ገዳይ መቅሰፍት የሚገባው ሁሉ በመቅሰፍት እንዲሞት ይሂድ፤ ሰይፍ የሚገባው ሁሉ በሰይፍ ይሙት፤+ ረሃብ የሚገባው ሁሉ በረሃብ ይሙት፤ በምርኮ መወሰድ የሚገባው ሁሉ ደግሞ ተማርኮ ይወሰድ!”’+  “‘እኔም አራት ዓይነት ጥፋት* አዝባቸዋለሁ’+ ይላል ይሖዋ፤ ‘እነሱም፦ ለመግደል ሰይፍ፣ ጎትቶ ለመውሰድ ውሾች እንዲሁም ለመሰልቀጥና ለማጥፋት የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ናቸው።+  የይሁዳ ንጉሥ፣ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ከፈጸመው ድርጊት የተነሳ+ ለምድር መንግሥታት ሁሉ መቀጣጫ እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ።+   ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ማን ይራራልሻል?ማንስ ያዝንልሻል?ደህንነትሽንስ ማን ጎራ ብሎ ይጠይቃል?’   ‘ትተሽኛል’ ይላል ይሖዋ።+ ‘አሁንም ጀርባሽን ሰጥተሽኛል።*+ ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቼ አጠፋሻለሁ።+ ለአንቺ አዘኔታ ማሳየት* ታክቶኛል።   በምድሪቱ በሮች፣ በመንሽ እበትናቸዋለሁ። የወላድ መሃን አደርጋቸዋለሁ።+ ሕዝቤን አጠፋዋለሁ፤ከመንገዱ ለመመለስ አሻፈረኝ ብሏልና።+   መበለቶቻቸው በፊቴ ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይበዛሉ። በእነሱ ይኸውም በእናቶችና በወጣት ወንዶች ላይ በቀትር አጥፊ አመጣለሁ። ከባድ ጭንቀትና ሽብር በድንገት አመጣባቸዋለሁ።   ሰባት ልጆች የወለደችው ሴት ተዝለፍልፋለች፤ትንፋሽ አጥሯት* ታጣጥራለች። ገና ቀን ሳለ ፀሐይዋ ጠልቃለች፤ይህም ኀፍረትና ውርደት አስከትሎባታል።’* ‘ከእነሱ መካከል የተረፉትንም ጥቂት ሰዎችበጠላቶቻቸው ፊት ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ’ ይላል ይሖዋ።”+ 10  እናቴ ሆይ፣ ወዮልኝ!በምድሪቱ ሁሉ ላይ የጠብና የጭቅጭቅ መንስኤ የሆንኩትን እኔን ወልደሻልና።+ እኔ ለማንም አላበደርኩም፤ ከማንም አልተበደርኩም፤ይሁንና ሁሉም ይረግሙኛል። 11  ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ በእርግጥ ለአንተ መልካም ነገር አደርግልሃለሁ፤በጥፋትና በጭንቀት ጊዜበአንተና በጠላት መካከል ጣልቃ ገብቼ እረዳሃለሁ። 12  ሰው ብረትን ይኸውም ከሰሜን የመጣን ብረትናመዳብን መሰባበር ይችላል? 13  በመላው ክልልህ ከፈጸምከው ኃጢአት ሁሉ የተነሳንብረትህንና ውድ ሀብትህን፣ ያለዋጋ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣለሁ።+ 14  እነዚህን ነገሮች ጠላቶችህ ወደማታውቀው አገር እንዲወስዷቸውአሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።+ ቁጣዬ እሳት አስነስቷልና፤በእናንተም ላይ እየነደደ ነው።”+ 15  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ታውቃለህ፤አስበኝ፤ ትኩረትህንም ወደ እኔ አዙር። አሳዳጆቼን ተበቀልልኝ።+ ቁጣህን በማዘግየት እንድጠፋ አታድርግ።* ይህን ነቀፋ የተሸከምኩት ለአንተ ስል እንደሆነ እወቅ።+ 16  ቃልህ ተገኝቷል፤ እኔም በልቼዋለሁ፤+የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ በስምህ ተጠርቻለሁና፣ቃልህ ሐሴት፣ ለልቤም ደስታ ሆነልኝ። 17  ፈንጠዝያ ከሚወዱ ሰዎች ጋር አልተቀመጥኩም፤ ከእነሱም ጋር ሐሴት አላደረግኩም።+ እጅህ በእኔ ላይ ስለሆነ ብቻዬን እቀመጣለሁ፤በቁጣ* ሞልተኸኛልና።+ 18  ሕመሜ ሥር የሰደደው፣ ቁስሌም የማይፈወስ የሆነው ለምንድን ነው? ጨርሶ አልድን ብሏል። እምነት ሊጣልበት እንደማይችልየሚያታልል የውኃ ምንጭ ትሆንብኛለህ? 19  ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ብትመለስ፣ እኔም ወደ ቀድሞው ሁኔታህ እመልስሃለሁ፤በፊቴም ትቆማለህ። ውድ የሆነውን ነገር ከማይረባው ነገር ብትለይ፣እንደ አፌ* ትሆናለህ። እነሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ እንጂአንተ ወደ እነሱ አትመለስም።” 20  “ለዚህ ሕዝብ ጠንካራ የመዳብ ቅጥር አደርግሃለሁ።+ እነሱ በእርግጥ ይዋጉሃል፤ሆኖም በአንተ ላይ አያይሉም፤*+እኔ አንተን ለማዳንና ለመታደግ ከአንተ ጋር ነኝና” ይላል ይሖዋ። 21  “ከክፉዎች እጅ እታደግሃለሁ፤ከጨካኞችም መዳፍ እቤዥሃለሁ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍሴ ወደዚህ ሕዝብ አታዘነብልም።”
“አራት ዓይነት ፍርድ” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቃል በቃል “አራት ወገኖች።”
“ወደ ኋላ ማፈግፈግሽን ቀጥለሻል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “መጸጸት።”
“ኀፍረት ተከናንባለች፤ ተዋርዳለችም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሷ ትንፋሽ አጥሯት።”
ቃል በቃል “አትውሰደኝ።”
ወይም “በውግዘት መልእክት።”
ወይም “የእኔ ቃል አቀባይ።”
ወይም “አያሸንፉህም።”