ኤርምያስ 2:1-37

  • እስራኤል ይሖዋን ትታ ሌሎች አማልክትን ተከተለች (1-37)

    • እስራኤል በባዕድ የወይን ተክል ተመሰለች (21)

    • ልብሶቿ በደም ቆሽሸዋል (34)

2  የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “ሂድና ኢየሩሳሌም ጆሮዋ እየሰማ ይህን አውጅ፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በወጣትነትሽ ጊዜ ለአምላክ ያደርሽ እንደነበርሽ፣*+ደግሞም ለጋብቻ በታጨሽበት ጊዜ ያሳየሽውን ፍቅር፣+ዘር በማይዘራበት ምድር፣ በምድረ በዳእንዴት እንደተከተልሽኝ በሚገባ አስታውሳለሁ።+   እስራኤል ለይሖዋ የተቀደሰ፣+ የመከሩ በኩር ነበር።”’ ‘እሱን የሚውጥ ሁሉ በደለኛ ይሆናል። በእነሱም ላይ ጥፋት ይመጣል’ ይላል ይሖዋ።”+   የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ የእስራኤልም ቤት ወገኖች ሁሉ፣የይሖዋን ቃል ስሙ።   ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አባቶቻችሁ ከእኔ እጅግ የራቁት፣ከንቱ የሆኑ ጣዖቶችን የተከተሉትና+እነሱ ራሳቸው ከንቱ የሆኑት+ ምን ጥፋት አግኝተውብኝ ነው?+   እነሱ ‘ከግብፅ ምድር ያወጣን፣+በምድረ በዳ፣ በረሃማ በሆነና+ጉድጓድ ባለበት ምድር፣በድርቅ በተጠቃና+ ድቅድቅ ጨለማ በዋጠው ምድርእንዲሁም ማንም ሰው በማይጓዝበትናሰው በማይኖርበት ምድርየመራን ይሖዋ የት አለ?’ ብለው አልጠየቁም።   በዚያን ጊዜ እኔ ፍሬዋንና በውስጧ ያሉትን ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንድትበሉየፍራፍሬ ዛፎች ወዳሉባት ምድር አመጣኋችሁ።+ እናንተ ግን መጥታችሁ ምድሬን አረከሳችሁ፤ርስቴንም አስጸያፊ ነገር አደረጋችሁት።+   ካህናቱ ‘ይሖዋ የት አለ?’ ብለው አልጠየቁም፤+ ሕጉ በአደራ የተሰጣቸውም እኔን አላወቁም፤እረኞቹ በእኔ ላይ ዓመፁ፤+ነቢያቱ በባአል ስም ትንቢት ተናገሩ፤+ምንም ጥቅም የማያስገኙላቸውንም አማልክት ተከተሉ።   ‘በመሆኑም ከእናንተ ጋር ገና እሟገታለሁ’+ ይላል ይሖዋ፤‘ከልጅ ልጆቻችሁም ጋር እሟገታለሁ።’ 10  ‘እስቲ ወደ ኪቲም+ የባሕር ዳርቻዎች* ተሻግራችሁ ተመልከቱ። አዎ፣ መልእክተኞችን ወደ ቄዳር+ ልካችሁ ጉዳዩን በጥሞና መርምሩ፤እንዲህ ያለ ነገር ተፈጽሞ እንደሆነ እዩ። 11  አማልክቱን፣ አማልክት ባልሆኑት ለውጦ የሚያውቅ ብሔር አለ? የገዛ ሕዝቤ ግን ክብሬን ምንም ጥቅም በሌለው ነገር ለውጧል።+ 12  እናንተ ሰማያት በዚህ ተደነቁ፤በታላቅ ድንጋጤም ተርበትበቱ’ ይላል ይሖዋ፤ 13  ‘ምክንያቱም ሕዝቤ ሁለት መጥፎ ነገሮች ፈጽመዋል፦ የሕያው ውኃ ምንጭ የሆንኩትን እኔን ትተው+የውኃ ማጠራቀሚያዎችን ይኸውም ውኃ መያዝ የማይችሉና የሚያፈሱየውኃ ማጠራቀሚያዎችን ለራሳቸው ቆፍረዋል።’* 14  ‘እስራኤል፣ አገልጋይ ወይም የቤት ውልድ ባሪያ ነው? ታዲያ እንዲበዘበዝ የተደረገው ለምንድን ነው? 15  ደቦል አንበሶች በእሱ ላይ አገሡ፤+በኃይለኛ ድምፅ ጮኹበት። ምድሩን የሚያስፈራ ቦታ አደረጉት። ከተሞቹ ማንም እንዳይኖርባቸው በእሳት ተቃጠሉ። 16  የኖፍና*+ የጣፍነስ+ ሕዝቦች፣ መሃል አናትሽን ይበላሉ። 17  አምላክሽ ይሖዋ በመንገዱ በመራሽ ወቅትእሱን በመተው+ይህን በራስሽ ላይ አላመጣሽም? 18  ደግሞስ የሺሆርን ውኃዎች* ለመጠጣትወደ ግብፅ የሚወስደውን መንገድ የመረጥሽው ለምንድን ነው?+ የወንዙን* ውኃዎች ለመጠጣትወደ አሦር የሚወስደውን መንገድ የመረጥሽው ለምንድን ነው?+ 19  ከክፋትሽ ትምህርት ልታገኚ ይገባል፤ታማኝነት በማጉደል የፈጸምሻቸው ድርጊቶችም ወቀሳ ያስከትሉብሻል። አምላክሽን ይሖዋን መተውሽመጥፎና መራራ እንደሆነ ማወቅና መገንዘብ ይኖርብሻል፤+እኔን ፈጽሞ አልፈራሽም’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት አምላክ ይሖዋ። 20  ‘ከረጅም ጊዜ በፊት ቀንበርሽን ሰባበርኩ፤+የታሰርሽበትንም ሰንሰለት በጣጠስኩ። አንቺ ግን “አንተን አላገለግልም” አልሽ፤ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይና ቅጠሉ በተንዠረገገ ዛፍ ሁሉ ሥር+ለማመንዘር ተንጋለሽ ተኝተሻልና።+ 21  እኔ፣ እንደ ምርጥ ቀይ የወይን ተክል፣ ሙሉ በሙሉ ንጹሕ የሆነ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤+ታዲያ በፊቴ እንዲህ ተለውጠሽ የተበላሸ ባዕድ የወይን ተክል የሆንሽው እንዴት ነው?’+ 22  ‘በሶዳ* ብትታጠቢና ብዛት ያለው እንዶድ* ብትጠቀሚ እንኳከበደልሽ የተነሳ ዕድፍሽ በፊቴ ይኖራል’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። 23  ‘ራሴን አላረከስኩም። ባአልንም አልተከተልኩም’ እንዴት ትያለሽ? በሸለቆው ውስጥ ያለውን መንገድሽን ተመልከቺ። ያደረግሽውን ነገር ልብ በይ። በመንገዷ ላይ ወዲያና ወዲህ እንደምትፋንንየደረሰች ፈጣን ግመል ነሽ፤ 24  በምድረ በዳ መኖር እንደለመደች፣በፍትወቷ* ነፋሱን እንደምታነፈንፍ የዱር አህያ ነሽ። ስሜቷ ሲነሳሳ ማን ሊመልሳት ይችላል? የሚፈልጓት ሁሉ እሷን ለማግኘት ብዙ ድካም አይጠይቅባቸውም። በመራቢያዋ ወቅት* ያገኟታል። 25  እግርሽ እስኪነቃ አትዙሪ፤ጉሮሮሽም በውኃ ጥም አይቃጠል። አንቺ ግን ‘አይሆንም! ምንም ተስፋ የሌለው ነገር ነው!+ እኔ ከባዕዳን* ጋር ፍቅር ይዞኛል፤+እነሱንም እከተላለሁ’ አልሽ።+ 26  ሌባ ሲያዝ እንደሚያፍር፣የእስራኤል ቤት ሰዎችም እንዲሁ አፍረዋል፤እነሱም ሆኑ ነገሥታታቸው፣ መኳንንታቸው፣ካህናታቸውና ነቢያታቸው ውርደት ተከናንበዋል።+ 27  ዛፉን ‘አንተ አባቴ ነህ’፤+ ድንጋዩንም ‘የወለድከኝ አንተ ነህ’ ይላሉ። ለእኔ ግን ፊታቸውን ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጥተውኛል።+ ጥፋት ሲመጣባቸውም‘ተነስተህ አድነን!’ ይላሉ።+ 28  ለራስህ የሠራሃቸው አማልክት ታዲያ የት አሉ?+ ጥፋት ሲደርስብህ ሊያድኑህ የሚችሉ ከሆነ ይነሱ፤ይሁዳ ሆይ፣ አማልክትህ የከተሞችህን ያህል በዝተዋልና።+ 29  ‘አሁንም ከእኔ ጋር የምትሟገቱት ለምንድን ነው? ሁላችሁም በእኔ ላይ ያመፃችሁት ለምንድን ነው?’+ ይላል ይሖዋ። 30  ልጆቻችሁን የመታሁት በከንቱ ነው።+ ለመታረም ፈቃደኞች አይደሉም፤+የገዛ ራሳችሁ ሰይፍ እንደሚያደባ አንበሳነቢያታችሁን በልቷል።+ 31  የዚህ ትውልድ ሰዎች ሆይ፣ የይሖዋን ቃል ልብ በሉ። እኔ ለእስራኤል፣ እንደ ምድረ በዳወይም ድቅድቅ ጨለማ እንደዋጠው ምድር ሆኛለሁ? የእኔ ሕዝብ የሆኑት እነዚህ ሰዎች ‘እኛ ወደፈለግንበት እንሄዳለን። ከእንግዲህ ወደ አንተ አንመጣም’ ለምን ይላሉ?+ 32  ለመሆኑ አንዲት ድንግል ጌጣጌጧን፣ሙሽሪትስ ጌጠኛ መቀነቷን* ትረሳለች? የገዛ ሕዝቤ ግን ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ቀናት ረስቶኛል።+ 33  አንቺ ሴት፣ ፍቅረኛ ለማግኘት መንገድሽን ምንኛ በጥበብ አመቻቸሽ! የክፋትን መንገዶች ተምረሻል።+ 34  ልብሶችሽ በንጹሐን ድሆች* ደም ቆሽሸዋል፤+ይሁንና ይህን ያገኘሁት ቤት ሲዘረፍ አይደለም፤ይልቁንም በልብሶችሽ ሁሉ ላይ ነው።+ 35  አንቺ ግን ‘እኔ ንጹሕ ነኝ። በእርግጥ ቁጣው ከእኔ ተመልሷል’ ትያለሽ። ‘ኃጢአት አልሠራሁም’ ስለምትዪ፣በአንቺ ላይ ፍርድ አመጣለሁ። 36  መንገድሽን በመለዋወጥ የምትፈጽሚውን ድርጊት አቅልለሽ የምትመለከቺው ለምንድን ነው? በአሦር እንዳፈርሽ ሁሉ+በግብፅም ታፍሪያለሽ።+ 37  በዚህም የተነሳ እጆችሽን በራስሽ ላይ አድርገሽ ትወጫለሽ፤+ይሖዋ የምትተማመኚባቸውን ነገሮች አስወግዷልና፤እነሱ ለስኬት አያበቁሽም።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ታማኝ ፍቅር ታሳዪ እንደነበር።”
ወይም “ደሴቶች።”
ወይም “ፈልፍለዋል።” ከዓለት ሊሆን ይችላል።
ወይም “የሜምፊስና።”
ከአባይ ወንዝ ተገንጥሎ የሚፈሰውን ውኃ ያመለክታል።
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ለማጠብ የሚያገለግል ንጥረ ነገር።
ወይም “ሳሙና።”
ወይም “ነፍሷ በምኞት ስትቃጠል።”
ቃል በቃል “በወሯ።”
ወይም “ከባዕዳን አማልክት።”
ወይም “ሙሽሪትስ የሠርጓን መቀነት።”
ወይም “በንጹሐን ድሆች ነፍሳት።”