ኤርምያስ 21:1-14

  • ይሖዋ ሴዴቅያስ ያቀረበውን ልመና አልሰማም (1-7)

  • ‘የሕይወት መንገድና የሞት መንገድ’ (8-14)

21  ንጉሥ ሴዴቅያስ+ የማልኪያህን ልጅ ጳስኮርንና+ የማአሴያህን ልጅ ካህኑን ሶፎንያስን+ ወደ ኤርምያስ በላካቸው ጊዜ የይሖዋ ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤ እነሱም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦ 2  “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* ሊወጋን ስለሆነ+ እባክህ፣ ስለ እኛ ይሖዋን ጠይቅልን። ንጉሡ ከእኛ እንዲመለስ ይሖዋ እንደቀድሞው ሁሉ አሁንም ተአምር ይፈጽምልን ይሆናል።”+ 3  ኤርምያስ እንዲህ አላቸው፦ “ሴዴቅያስን እንዲህ በሉት፦ 4  ‘የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎንን ንጉሥና ከቅጥሩ ውጭ የከበቧችሁን ከለዳውያንን ለመውጋት የምትጠቀሙባቸውን በገዛ እጃችሁ ላይ ያሉትን የጦር መሣሪያዎች በእናንተው ላይ አዞራለሁ።+ በዚህችም ከተማ መሃል እሰበስባቸዋለሁ። 5  እኔ ራሴ በተዘረጋች እጅና በኃያል ክንድ እንዲሁም በመዓትና በታላቅ ቁጣ እዋጋችኋለሁ።+ 6  የዚህችን ከተማ ነዋሪዎች፣ ሰውንም ሆነ እንስሳን እመታለሁ። እነሱም በታላቅ ቸነፈር* ይሞታሉ።”’+ 7  “‘“ከዚያም በኋላ” ይላል ይሖዋ፣ “የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን፣ አገልጋዮቹን እንዲሁም ከቸነፈር፣ ከሰይፍና ከረሃብ ተርፎ በከተማዋ ውስጥ የሚቀረውን ሕዝብ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነጾር* እጅ፣ በጠላቶቻቸው እጅና ሕይወታቸውን ለማጥፋት በሚሹ* ሰዎች እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።+ እሱም በሰይፍ ይመታቸዋል። አያዝንላቸውም፤ ርኅራኄም ሆነ ምሕረት አያሳያቸውም።”’+ 8  “ደግሞም ይህን ሕዝብ እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ በፊታችሁ አድርጌአለሁ። 9  በዚህች ከተማ የሚቀሩ ሰዎች በሰይፍ፣ በረሃብና በቸነፈር ይሞታሉ። ይሁንና ከከተማዋ ወጥቶ፣ ለከበቧችሁ ከለዳውያን እጁን የሚሰጥ በሕይወት ይኖራል፤ ሕይወቱም* እንደ ምርኮ ትሆንለታለች።”’*+ 10  “‘“መልካም ነገር ሳይሆን ጥፋት ለማምጣት ፊቴን ወደዚህች ከተማ አዙሬአለሁና”+ ይላል ይሖዋ። “ለባቢሎን ንጉሥ ትሰጣለች፤+ እሱም በእሳት ያቃጥላታል።”+ 11  “‘የይሁዳ ንጉሥ ቤት ሆይ፦ የይሖዋን ቃል ስሙ። 12  የዳዊት ቤት ሆይ፣ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከክፉ ድርጊታችሁ የተነሳቁጣዬ እንደ እሳት እንዳይቀጣጠልና+ማንም ሊያጠፋው እስከማይችል ድረስ እንዳይነድበየማለዳው ለፍትሕ ቁሙ፤የተዘረፈውንም ሰው ከአጭበርባሪው እጅ ታደጉ።”’+ 13  ‘አንቺ በሸለቆ ውስጥ* የምትኖሪ፣ በደልዳላው መሬት ላይ የተቀመጥሽ ዓለት ሆይ፣እነሆ፣ እኔ በአንቺ ላይ እነሳለሁ’ ይላል ይሖዋ። ‘“በእኛ ላይ ማን ይወርዳል? ደግሞስ መኖሪያዎቻችንን ማን ይወራል?” የምትሉ ይህን እወቁ፤ 14  እንደ ሥራችሁ መጠንተጠያቂ አደርጋችኋለሁ’+ ይላል ይሖዋ። ‘ጫካዋን በእሳት አነዳለሁ፤እሳቱም በዙሪያዋ ያለውን ነገር ሁሉ ይበላል።’”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “በከባድ በሽታ።”
ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “ነፍሳቸውን በሚሹ።”
ወይም “ነፍሱም።”
ወይም “ሕይወቱን ያተርፋል።”
ወይም “በረባዳማ ሜዳ።”