ኤርምያስ 27:1-22
27 በኢዮስያስ ልጅ፣ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮዓቄም* ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ይህ የይሖዋ ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፦
2 “ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘ለራስህ ማሰሪያና ቀንበር ሠርተህ አንገትህ ላይ አድርገው።
3 ከዚያም በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሴዴቅያስ በመጡት መልእክተኞች እጅ፣ ወደ ኤዶም+ ንጉሥ፣ ወደ ሞዓብ+ ንጉሥ፣ ወደ አሞናውያን+ ንጉሥ፣ ወደ ጢሮስ+ ንጉሥና ወደ ሲዶና+ ንጉሥ ላከው።
4 ለጌቶቻቸው ይህን ትእዛዝ እንዲያስተላልፉ ንገራቸው፦
“‘“የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ለጌቶቻችሁ እንዲህ በሏቸው፦
5 ‘ምድርን እንዲሁም በምድር ላይ ያሉትን ሰዎችና እንስሳት በታላቅ ኃይሌና በተዘረጋችው ክንዴ የሠራሁት እኔ ነኝ፤ ለወደድኩትም ሰጥቼዋለሁ።+
6 አሁንም እነዚህን ሁሉ አገሮች ለአገልጋዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነጾር አሳልፌ ሰጥቻለሁ፤+ የዱር አራዊትም እንኳ እንዲገዙለት አድርጌአለሁ።
7 የእሱ መንግሥት የሚያበቃበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ+ ብሔራት ሁሉ እሱን፣ ልጁንና የልጅ ልጁን ያገለግላሉ፤ በዚያን ጊዜ ግን ብዙ ብሔራትና ታላላቅ ነገሥታት ባሪያቸው ያደርጉታል።’+
8 “‘“‘የትኛውም ብሔር ወይም መንግሥት የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን ለማገልገል ፈቃደኛ ባይሆን እንዲሁም አንገቱን በባቢሎን ንጉሥ ቀንበር ሥር ለማስገባት እንቢተኛ ቢሆን ያንን ብሔር በእሱ እጅ ፈጽሞ እስካጠፋው ድረስ በሰይፍ፣+ በረሃብና በቸነፈር* እቀጣዋለሁ’ ይላል ይሖዋ።
9 “‘“‘ስለዚህ “የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም” የሚሏችሁን በመካከላችሁ ያሉትን ነቢያት፣ ሟርተኞች፣ ሕልም አላሚዎች፣ አስማተኞችና መተተኞች አትስሙ።
10 የሚተነብዩላችሁ ነገር ሐሰት ነውና፤ እነሱን የምትሰሙ ከሆነ ከምድራችሁ ተፈናቅላችሁ ወደ ሩቅ ቦታ ትወሰዳላችሁ፤ እኔም እበትናችኋለሁ፤ እናንተም ትጠፋላችሁ።
11 “‘“‘ሆኖም አንገቱን በባቢሎን ንጉሥ ቀንበር ሥር የሚያስገባንና እሱን የሚያገለግልን ብሔር ምድሪቱን እንዲያርስና በዚያ እንዲኖር በገዛ ምድሩ እንዲቀር* አደርገዋለሁ’ ይላል ይሖዋ።”’”
12 ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም+ ተመሳሳይ ነገር ነገርኩት፤ እንዲህም አልኩት፦ “አንገታችሁን በባቢሎን ንጉሥ ቀንበር ሥር አስገቡ፤ እሱንና ሕዝቡንም አገልግሉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ።+
13 ይሖዋ የባቢሎንን ንጉሥ የማያገለግልን ብሔር አስመልክቶ በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት፣ አንተም ሆንክ ሕዝብህ በሰይፍ፣+ በረሃብና+ በቸነፈር ለምን ታልቃላችሁ?+
14 ‘የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሏችሁን ነቢያት ቃል አትስሙ፤+ ምክንያቱም የሚተነብዩላችሁ ነገር ሐሰት ነው።+
15 “‘እኔ አልላክኋቸውምና’ ይላል ይሖዋ፤ ‘እነሱ ግን በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እነሱን የምትሰሙ ከሆነ እናንተንና የሚተነብዩላችሁን ነቢያት እበትናለሁ፤ እናንተም ትጠፋላችሁ።’”+
16 ደግሞም ለካህናቱና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አልኩ፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘“እነሆ፣ የይሖዋ ቤት ዕቃዎች ከባቢሎን በቅርቡ ይመለሳሉ!”+ እያሉ የሚተነብዩላችሁን የነቢያታችሁን ቃል አትስሙ፤ የሚተነብዩላችሁ ነገር ሐሰት ነውና።+
17 እነሱን አትስሟቸው። የባቢሎንን ንጉሥ አገልግሉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ።+ ይህች ከተማ ለምን ትፈራርስ?
18 ሆኖም እነሱ ነቢያት ከሆኑና የይሖዋ ቃል እነሱ ጋር ካለ፣ በይሖዋ ቤት፣ በይሁዳ ንጉሥ ቤትና* በኢየሩሳሌም የቀሩት ዕቃዎች ወደ ባቢሎን እንዳይወሰዱ እስቲ የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ይለምኑ።’
19 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ስለ ዓምዶቹ፣+ ስለ ባሕሩ፣*+ ስለ ዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎቹና+ በዚህች ከተማ ስለቀሩት የተረፉ ዕቃዎች እንዲህ ይላልና፦
20 እነዚህ፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር የኢዮዓቄምን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ታላላቅ ሰዎች ሁሉ ጋር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ባጋዘበት ወቅት ሳይወስዳቸው የቀሩ ነገሮች ናቸው፤+
21 አዎ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ በይሖዋ ቤት፣ በይሁዳ ንጉሥ ቤትና* በኢየሩሳሌም ስለቀሩት ዕቃዎች እንዲህ ይላል፦
22 ‘“ትኩረቴን ወደ እነሱ እስከማዞርበት ጊዜ ድረስ ወደ ባቢሎን ይወሰዳሉ፤+ በዚያም ይቆያሉ” ይላል ይሖዋ። “ከዚያ በኋላ አመጣቸዋለሁ፤ ወደዚህ ስፍራም እመልሳቸዋለሁ።”’”+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በሴዴቅያስ።” የሲሪያክና የዓረብኛ ትርጉሞች እንዲሁም በእጅ የተጻፉ ሦስት ጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅጂዎች ይህን ስም ይጠቀማሉ።
^ ወይም “በበሽታ።”
^ ቃል በቃል “እንዲያርፍ።”
^ ወይም “በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥትና።”
^ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚገኘውን ከመዳብ የተሠራ ትልቅ ገንዳ ያመለክታል።
^ ወይም “ቤተ መንግሥትና።”