ኤርምያስ 28:1-17
-
ኤርምያስና ሐሰተኛው ነቢይ ሃናንያህ (1-17)
28 በዚያው ዓመት፣ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ+ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ፣ በአራተኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር፣ የገባኦን+ ሰው የሆነው የአዙር ልጅ ነቢዩ ሃናንያህ፣ በይሖዋ ቤት ውስጥ በካህናቱና በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ አለኝ፦
2 “የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁ።+
3 በሁለት ዓመት* ጊዜ ውስጥ፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ከዚህ ስፍራ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን የይሖዋን ቤት ዕቃዎች ሁሉ ወደዚህ ቦታ መልሼ አመጣለሁ።’”+
4 “‘የኢዮዓቄምን+ ልጅ፣ የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን+ እንዲሁም ወደ ባቢሎን በግዞት የተወሰዱትን የይሁዳ ሰዎች ሁሉ+ ወደዚህ ቦታ መልሼ አመጣለሁ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና።’”
5 ከዚያም ነቢዩ ኤርምያስ በካህናቱ ፊትና በይሖዋ ቤት ቆመው በነበሩት ሕዝብ ሁሉ ፊት ነቢዩ ሃናንያህን አናገረው።
6 ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ አለ፦ “አሜን! ይሖዋ ይህን ያድርግ! የይሖዋን ቤት ዕቃዎችና በግዞት የተወሰዱትን ሰዎች ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ እንዲመለሱ በማድረግ ይሖዋ የተነበይከውን ቃል ይፈጽም!
7 ይሁንና እባክህ፣ በጆሮህና በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ የምናገረውን ይህን መልእክት ስማ።
8 በጥንት ዘመን ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩት ነቢያት፣ ብዙ አገሮችና ታላላቅ መንግሥታት ስለሚያጋጥማቸው ጦርነት እንዲሁም ስለሚደርስባቸው ጥፋትና ቸነፈር* ይተነብዩ ነበር።
9 አንድ ነቢይ ስለ ሰላም ትንቢት ከተናገረና ነቢዩ የተናገረው ቃል ከተፈጸመ ይሖዋ ይህን ነቢይ በእርግጥ እንደላከው ይታወቃል።”
10 በዚህ ጊዜ ነቢዩ ሃናንያህ ቀንበሩን ከነቢዩ ኤርምያስ አንገት ላይ ወስዶ ሰበረው።+
11 ከዚያም ሃናንያህ በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ልክ እንዲሁ እኔም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነጾርን ቀንበር ከብሔራት ሁሉ አንገት ላይ እሰብራለሁ።’”+ ነቢዩ ኤርምያስም ትቶት ሄደ።
12 ነቢዩ ሃናንያህ ቀንበሩን ከነቢዩ ኤርምያስ አንገት ላይ ወስዶ ከሰበረው በኋላ ይህ የይሖዋ መልእክት ወደ ኤርምያስ መጣ፦
13 “ሄደህ ሃናንያህን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንተ የእንጨት ቀንበር ሰብረሃል፤+ ይሁንና በእሱ ምትክ የብረት ቀንበር ትሠራለህ።”
14 የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን እንዲያገለግሉ በእነዚህ ሁሉ ብሔራት አንገት ላይ የብረት ቀንበር አደርጋለሁ፤ እነሱም ያገለግሉታል።+ የዱር አራዊትንም እንኳ እሰጠዋለሁ።”’”+
15 ከዚያም ነቢዩ ኤርምያስ ነቢዩ ሃናንያህን+ እንዲህ አለው፦ “ሃናንያህ ሆይ፣ እባክህ ስማ! ይሖዋ ሳይልክህ ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል።+
16 ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ ከምድር ገጽ አስወግድሃለሁ። በይሖዋ ላይ ዓመፅ ስላነሳሳህ በዚህ ዓመት ትሞታለህ።’”+
17 በመሆኑም ነቢዩ ሃናንያህ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።