ኤርምያስ 34:1-22

  • ለሴዴቅያስ የተነገረ የፍርድ መልእክት (1-7)

  • ለባሪያዎች ነፃነት አስገኝቶ የነበረው ቃል ኪዳን ፈረሰ (8-22)

34  የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር፣* ሠራዊቱ ሁሉ፣ በእሱ ግዛት ሥር ያሉ የምድር መንግሥታት ሁሉ እንዲሁም ሕዝቡ ሁሉ ኢየሩሳሌምንና በዙሪያዋ ያሉትን ከተሞች በሙሉ እየወጉ ሳሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው የይሖዋ ቃል ይህ ነው፦+  “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሂድና የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን+ አናግረው፤ እንዲህም በለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እሱም በእሳት ያቃጥላታል።+  አንተም ከእጁ አታመልጥም፤ ያለጥርጥር ትያዛለህና፤ በእጁም አልፈህ ትሰጣለህ።+ የባቢሎንንም ንጉሥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፤ ፊት ለፊትም ያነጋግርሃል፤ ወደ ባቢሎንም ትወሰዳለህ።’+  ይሁንና የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ፣ የይሖዋን ቃል ስማ፤ ‘ይሖዋ ስለ አንተ እንዲህ ይላል፦ “በሰይፍ አትሞትም።  በሰላም ትሞታለህ፤+ ለአባቶችህ ይኸውም ከአንተ ቀድሞ ለነበሩት ነገሥታት እንዳደረጉት ለክብርህ እሳት ያነዱልሃል፤ ‘ወዮ፣ ጌታችን!’ እያሉም ያለቅሱልሃል፤ ‘እኔ ይህን ቃል ተናግሬአለሁና’ ይላል ይሖዋ።”’”’”  ከዚያም ነቢዩ ኤርምያስ በኢየሩሳሌም ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ ይህን ሁሉ ቃል ነገረው፤  በዚህ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ይኸውም ለኪሶንና+ አዜቃን+ እየወጋ ነበር፤+ ከይሁዳ ከተሞች መካከል ድል ሳይደረጉ የቀሩት እነዚህ የተመሸጉ ከተሞች ብቻ ነበሩና።  ንጉሥ ሴዴቅያስ ነፃነት ለማወጅ+ በኢየሩሳሌም ከነበረው ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ከገባ በኋላ የይሖዋ ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤  ቃል ኪዳኑ፣ እያንዳንዱ ሰው ዕብራውያን የሆኑ ወንድና ሴት ባሪያዎቹን በነፃ እንዲለቅ፣ ደግሞም ማንኛውም ሰው ወገኑ የሆነውን አይሁዳዊ፣ ባሪያው አድርጎ እንዳያሠራ የሚያዝዝ ነበር። 10  በመሆኑም መኳንንቱና ሕዝቡ ሁሉ እንደተባሉት አደረጉ። እያንዳንዳቸው ወንድና ሴት ባሪያዎቻቸውን በነፃ ለመልቀቅና ከዚያ በኋላ ባሪያ አድርገው ላለማሠራት ቃል ኪዳን ገቡ። እንደተባሉት በማድረግ ባሪያዎቻቸውን አሰናበቷቸው። 11  በኋላ ግን ነፃ ለቀዋቸው የነበሩትን ወንድና ሴት ባሪያዎቻቸውን መለሷቸው፤ እንደገናም አስገድደው በባርነት ገዟቸው። 12  ስለዚህ የይሖዋ ቃል ከይሖዋ ዘንድ እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦ 13  “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር፣ ከባርነት ቤት ባወጣኋቸው ጊዜ+ እንዲህ ስል ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፦+ 14  “እያንዳንዳችሁ የተሸጠላችሁንና ስድስት ዓመት ሲያገለግላችሁ የቆየውን ዕብራዊ የሆነውን ወንድማችሁን በሰባተኛው ዓመት ማብቂያ ላይ ልቀቁት፤ በነፃ ልታሰናብቱት ይገባል።”+ አባቶቻችሁ ግን አልሰሙኝም ወይም ጆሯቸውን አልሰጡኝም። 15  እናንተም በቅርቡ* ተመልሳችሁ ለወገኖቻችሁ ነፃነት በማወጅ በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር አደረጋችሁ፤ ስሜ በተጠራበትም ቤት በፊቴ ቃል ኪዳን ገባችሁ። 16  በኋላ ግን ሐሳባችሁን ቀይራችሁ፣ እንደ ፍላጎታቸው* በነፃ የለቀቃችኋቸውን ወንድና ሴት ባሪያዎቻችሁን መልሳችሁ በማምጣት ስሜን አረከሳችሁ፤+ አስገድዳችሁም ወደ ባርነት መለሳችኋቸው።’ 17  “ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እያንዳንዳችሁ ለወንድማችሁና ለወገናችሁ ነፃነት በማወጅ አልታዘዛችሁኝም።+ በመሆኑም እኔ ለእናንተ ያወጅኩት ነፃነት ይህ ነው’ ይላል ይሖዋ፤ ‘በሰይፍ፣ በቸነፈርና* በረሃብ ታልቃላችሁ፤+ ለምድር መንግሥታትም ሁሉ መቀጣጫ አደርጋችኋለሁ።+ 18  ጥጃውን ሁለት ቦታ ከፍለው በመካከሉ ባለፉ ጊዜ በፊቴ የገቡትን ቃል ኪዳን+ ባለማክበር ቃል ኪዳኔን የጣሱት ሰዎች የሚደርስባቸው ነገር ይህ ነው፤ 19  ይኸውም የይሁዳ መኳንንት፣ የኢየሩሳሌም መኳንንት፣ የቤተ መንግሥቱ ባለሥልጣናት፣ ካህናቱና ለሁለት በተከፈለው ጥጃ መካከል ያለፈው የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይህ ነገር ይደርስባቸዋል፦ 20  ለጠላቶቻቸውና ሕይወታቸውን ማጥፋት ለሚሹ* ሰዎች አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል።+ 21  የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መኳንንቱን ሁሉ ለጠላቶቻቸው፣ ሕይወታቸውን ማጥፋት ለሚሹ* ሰዎችና እናንተን መውጋት ትቶ ለተመለሰው+ የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት አሳልፌ እሰጣለሁ።’+ 22  “‘እነሆ፣ እኔ ይህን ትእዛዝ አስተላልፋለሁ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘እነሱንም ወደዚህች ከተማ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ እነሱም ይወጓታል፣ ይይዟታል፣ በእሳትም ያቃጥሏታል፤+ የይሁዳንም ከተሞች ማንም የማይኖርበት ጠፍ መሬት አደርጋቸዋለሁ።’”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ቃል በቃል “ዛሬ።”
ወይም “እንደ ነፍሳቸው።”
ወይም “በበሽታና።”
ወይም “ነፍሳቸውን ለሚሹ።”
ወይም “ነፍሳቸውን ለሚሹ።”