ኤርምያስ 35:1-19

  • ሬካባውያን የተዉት ግሩም የታዛዥነት ምሳሌ (1-19)

35  በኢዮስያስ ልጅ፣ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮዓቄም+ የግዛት ዘመን የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦  “ወደ ሬካባውያን+ ቤት ሄደህ አነጋግራቸው፤ ወደ ይሖዋም ቤት አምጥተህ ወደ አንዱ መመገቢያ ክፍል አስገባቸው፤ ከዚያም የሚጠጡትን የወይን ጠጅ አቅርብላቸው።”  ስለዚህ የሃባጺንያን ልጅ፣ የኤርምያስን ልጅ፣ ያአዛንያህን፣ ወንድሞቹን፣ ወንዶች ልጆቹን ሁሉና የሬካባውያንን ወገን ሁሉ ወሰድኩ፤  ወደ ይሖዋ ቤትም አመጣኋቸው። የእውነተኛው አምላክ ሰው፣ የይግዳልያ ልጅ፣ የሃናን ልጆች መመገቢያ ወደሆነው ክፍል አስገባኋቸው፤ ክፍሉም የሚገኘው ከበር ጠባቂው ከሻሉም ልጅ፣ ከማአሴያህ መመገቢያ ክፍል በላይ ካለው ከመኳንንቱ መመገቢያ ክፍል አጠገብ ነው።  ከዚያም ከሬካባውያን ወገን በሆኑት ሰዎች ፊት በወይን ጠጅ የተሞሉ ጽዋዎችንና ዋንጫዎችን አቅርቤ “የወይን ጠጅ ጠጡ” አልኳቸው።  እነሱ ግን እንዲህ አሉ፦ “የወይን ጠጅ አንጠጣም፤ ምክንያቱም አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ*+ እንዲህ ሲል አዞናል፦ ‘እናንተም ሆናችሁ ወንዶች ልጆቻችሁ መቼም ቢሆን የወይን ጠጅ አትጠጡ።  ቤት አትሥሩ፤ ዘር አትዝሩ፤ ወይን አትትከሉ ወይም የወይን እርሻ አይኑራችሁ። ይልቁንም የባዕድ አገር ሰዎች ሆናችሁ በተቀመጣችሁበት ምድር ረጅም ዘመን እንድትኖሩ ምንጊዜም በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ።’  ስለዚህ እኛም ሆንን ሚስቶቻችን እንዲሁም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን የአባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ያዘዘንን ቃል ሁሉ በማክበር የወይን ጠጅ የሚባል ነገር መቼም ቢሆን አንጠጣም።  መኖሪያ ቤትም አንሠራም፤ የወይን እርሻ፣ መሬትም ሆነ የእህል ዘር የለንም። 10  በድንኳን ውስጥ መኖራችንንና አባታችን ኢዮናዳብ* የሰጠንን ትእዛዝ ማክበራችንን እንቀጥላለን። 11  ሆኖም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* ምድሪቱን ሊወጋ በመጣ ጊዜ+ እንዲህ አልን፦ ‘ኑ፣ ከከለዳውያንና ከሶርያውያን ሠራዊት ለማምለጥ ወደ ኢየሩሳሌም እንግባ’፤ በመሆኑም አሁን በኢየሩሳሌም እየኖርን ነው።” 12  የይሖዋም ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦ 13  “የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲህ በል፦ “ቃሌን እንድትታዘዙ በተደጋጋሚ ጊዜ ማሳሰቢያ አልተሰጣችሁም?”+ ይላል ይሖዋ። 14  “የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ፣ ዘሮቹ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ አዝዞ ነበር፤ እነሱም እስከ ዛሬ ድረስ የወይን ጠጅ ባለመጠጣት ቃሉን ጠብቀዋል፤ በዚህም መንገድ የአባታቸውን ትእዛዝ አክብረዋል።+ ይሁንና እኔ ደግሜ ደጋግሜ ብነግራችሁም* አልታዘዛችሁኝም።+ 15  እኔም አገልጋዮቼን ነቢያትን ሁሉ ወደ እናንተ መላኬን ቀጠልኩ፤ እንዲህ በማለትም ደግሜ ደጋግሜ* ላክኋቸው፦+ ‘እባካችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤+ ትክክል የሆነውንም ነገር አድርጉ! ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፤ ደግሞም አታገልግሏቸው። እንዲህ ካደረጋችሁ ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ።’+ እናንተ ግን ጆሯችሁን አልሰጣችሁም፤ እኔንም አልሰማችሁም። 16  የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ዘሮች አባታቸው የሰጣቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋል፤+ እነዚህ ሰዎች ግን እኔን አልሰሙም።”’” 17  “ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ ላይ አደርሳለሁ ያልኩትን ጥፋት ሁሉ አመጣባቸዋለሁ፤+ ብነግራቸውም እንኳ አይሰሙኝምና፤ ደጋግሜ ብጠራቸውም አይመልሱልኝም።’”+ 18  ኤርምያስም ለሬካባውያን ወገኖች እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የአባታችሁን የኢዮናዳብን ትእዛዝ ስላከበራችሁ እንዲሁም ትእዛዙን ሁሉ ስለጠበቃችሁና ያዘዛችሁን በትክክል ስለፈጸማችሁ፣ 19  የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ* ዘር በፊቴ የሚያገለግል ሰው ፈጽሞ አይታጣም።”’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ዮናዳብ።” የኢዮናዳብ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ቃል በቃል “ዮናዳብ።” የኢዮናዳብ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ቃል በቃል “በማለዳ እየተነሳሁ ብናገርም።”
ቃል በቃል “በማለዳ እየተነሳሁ።”
ቃል በቃል “ዮናዳብ።” የኢዮናዳብ ስም አጭር መጠሪያ ነው።