ኤርምያስ 37:1-21

  • ከለዳውያን ለጊዜው ኢየሩሳሌምን ለቀው ሄዱ (1-10)

  • ኤርምያስ ታሰረ (11-16)

  • ሴዴቅያስ ከኤርምያስ ጋር ተገናኘ (17-21)

    • ኤርምያስ ዳቦ ይሰጠው ነበር (21)

37  የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* የኢዮስያስን ልጅ ንጉሥ ሴዴቅያስን+ በይሁዳ ምድር ስላነገሠው በኢዮአቄም ልጅ በኮንያሁ*+ ፋንታ መግዛት ጀመረ።+  ይሁንና እሱም ሆነ አገልጋዮቹ እንዲሁም የምድሪቱ ሕዝብ ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል የተናገረውን ቃል አልሰሙም።  ንጉሥ ሴዴቅያስም የሸሌምያህን ልጅ የሁካልንና+ የካህኑን የማአሴያህን ልጅ ሶፎንያስን+ “እባክህ፣ ስለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ ይሖዋ ጸልይ” ብለው እንዲነግሩት ወደ ነቢዩ ኤርምያስ ላካቸው።  በዚያ ወቅት ኤርምያስ ገና እስር ቤት ስላላስገቡት በሕዝቡ መካከል በነፃነት ይገባና ይወጣ ነበር።+  በዚህ ጊዜ የፈርዖን ሠራዊት ከግብፅ ወጥቶ ነበር፤+ ኢየሩሳሌምን ከበው የነበሩት ከለዳውያንም ይህን ሰሙ። በመሆኑም ኢየሩሳሌምን ለቀው ሄዱ።+  ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ነቢዩ ኤርምያስ መጣ፦  “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኔን እንድትጠይቁ ወደ እኔ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ “እነሆ፣ እናንተን ለመርዳት የመጣው የፈርዖን ሠራዊት ወደ አገሩ ወደ ግብፅ ይመለሳል።+  ከለዳውያኑም ተመልሰው መጥተው ይህችን ከተማ ይወጓታል፤ ይይዟታልም፤ በእሳትም ያቃጥሏታል።”+  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “‘ከለዳውያን ያላንዳች ጥርጥር ትተውን ይሄዳሉ’ እያላችሁ ራሳችሁን አታታሉ፤* ምክንያቱም ትተዋችሁ አይሄዱም። 10  እናንተን የሚወጋችሁን መላውን የከለዳውያን ሠራዊት ብትመቱና ቁስለኞቻቸው ብቻ ቢቀሩ እንኳ ከድንኳናቸው ተነስተው ይህችን ከተማ በእሳት ያቃጥሏታል።”’”+ 11  የከለዳውያን ሠራዊት ከፈርዖን ሠራዊት የተነሳ ኢየሩሳሌምን ትቶ በተመለሰ ጊዜ፣+ 12  ኤርምያስ ወደ ቢንያም አገር+ ሄዶ በሕዝቡ መካከል ድርሻውን ለመውሰድ ከኢየሩሳሌም ተነሳ። 13  ይሁንና ወደ ቢንያም በር በደረሰ ጊዜ የሃናንያህ ልጅ፣ የሸሌምያህ ልጅ ይሪያህ የተባለ የጠባቂዎች አለቃ ነቢዩ ኤርምያስን ይዞ “ከድተህ ወደ ከለዳውያን ልትሄድ ነው!” አለው። 14  ኤርምያስ ግን “በፍጹም! ከድቼ ወደ ከለዳውያን ልሄድ አይደለም” አለ። እሱ ግን አልሰማውም። በመሆኑም ይሪያህ ኤርምያስን ይዞ ወደ መኳንንቱ ወሰደው። 15  መኳንንቱ ኤርምያስን እጅግ ተቆጥተው+ መቱት፤ ከዚያም በወቅቱ እስር ቤት አድርገውት በነበረው በጸሐፊው በየሆናታን ቤት አሰሩት።*+ 16  ኤርምያስ በምድር ቤት* ውስጥ ወደሚገኝ የእስረኞች ክፍል እንዲገባ ተደረገ፤ በዚያም ለብዙ ቀናት ቆየ። 17  ከዚያም ንጉሥ ሴዴቅያስ ልኮ አስመጣው፤ ንጉሡም በቤቱ* ውስጥ በሚስጥር ጠየቀው።+ “ከይሖዋ የመጣ ቃል አለ?” አለው። ኤርምያስም “አዎ፣ አለ!” ሲል መለሰለት፤ አክሎም “በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፈህ ትሰጣለህ!” አለው።+ 18  በተጨማሪም ኤርምያስ ንጉሥ ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ “እስር ቤት ያስገባችሁኝ በአንተ፣ በአገልጋዮችህና በዚህ ሕዝብ ላይ ምን የሠራሁት በደል ቢኖር ነው? 19  ‘የባቢሎን ንጉሥ እናንተንና ይህችን ምድር ለመውጋት አይመጣም’ ብለው የተነበዩላችሁ ነቢያታችሁ አሁን የት አሉ?+ 20  አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እባክህ ስማኝ። በፊትህ ሞገስ ለማግኘት የማቀርበውን ልመና እባክህ ተቀበል። ወደ ጸሐፊው ወደ የሆናታን ቤት+ መልሰህ አትላከኝ፤ ካልሆነ ግን በዚያ እሞታለሁ።”+ 21  በመሆኑም ንጉሥ ሴዴቅያስ፣ ኤርምያስ በክብር ዘቦቹ ግቢ+ እንዲታሰር አዘዘ፤ ዳቦ ከከተማዋ እስኪጠፋ ድረስም+ ከዳቦ ጋጋሪዎች ጎዳና በየዕለቱ አንድ አንድ ዳቦ ይሰጠው ነበር።+ ኤርምያስም በክብር ዘቦቹ ግቢ ተቀመጠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ዮአኪን እና ኢኮንያን ተብሎም ይጠራል።
ወይም “ነፍሳችሁን አታታሉ።”
ቃል በቃል “በእግር ብረት ቤት አኖሩት።”
ቃል በቃል “በውኃ ማጠራቀሚያው ቤት።”
ወይም “በቤተ መንግሥቱ።”