ኤርምያስ 38:1-28

  • ኤርምያስ ጉድጓድ ውስጥ ተጣለ (1-6)

  • ኤቤድሜሌክ ኤርምያስን አዳነው (7-13)

  • ኤርምያስ፣ እጁን እንዲሰጥ ሴዴቅያስን አሳሰበው (14-28)

38  የማታን ልጅ ሰፋጥያህ፣ የጳስኮር ልጅ ጎዶልያስ፣ የሸሌምያህ ልጅ ዩካልና+ የማልኪያህ ልጅ ጳስኮር፣+ ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ የተናገረውን የሚከተለውን ቃል ሰሙ፦  “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚህች ከተማ የሚቀር በሰይፍ፣ በረሃብና በቸነፈር* ይሞታል።+ ለከለዳውያን እጁን የሚሰጥ* ግን ይተርፋል፤ ሕይወቱ * እንደ ምርኮ ትሆንለታለች፤* በሕይወትም ይኖራል።’+  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህች ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት መሰጠቷ አይቀርም፤ እሱም ይይዛታል።’”+  መኳንንቱ ንጉሡን እንዲህ አሉት፦ “ይህ ሰው እንዲህ ያለ ቃል በመናገር በዚህች ከተማ ውስጥ የቀሩትን ወታደሮችና የሕዝቡን ሁሉ ወኔ* እያዳከመ ስለሆነ እባክህ አስገድለው።+ ይህ ሰው ለዚህ ሕዝብ ጥፋትን እንጂ ሰላምን አይመኝምና።”  ንጉሥ ሴዴቅያስም “እነሆ፣ እሱ በእጃችሁ ነው፤ ንጉሡ እናንተን ለማስቆም ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልምና” ሲል መለሰላቸው።  እነሱም ኤርምያስን ወስደው በክብር ዘቦቹ ግቢ+ በሚገኘው በንጉሡ ልጅ በማልኪያህ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት። ኤርምያስን በገመድ ወደ ጉድጓዱ አወረዱት። በጉድጓዱ ውስጥም ጭቃ ብቻ እንጂ ውኃ አልነበረም፤ ኤርምያስም ጭቃው ውስጥ መስመጥ ጀመረ።  በንጉሡ ቤት* የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ* ኤቤድሜሌክ+ ኤርምያስን በውኃ ማጠራቀሚያው ጉድጓድ ውስጥ እንደጣሉት ሰማ። በዚህ ጊዜ ንጉሡ በቢንያም በር ተቀምጦ ነበር፤+  በመሆኑም ኤቤድሜሌክ ከንጉሡ ቤት* ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው፦  “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች በነቢዩ ኤርምያስ ላይ ክፉ ነገር ፈጽመዋል! በውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውስጥ ጥለውታል፤ ከረሃቡም የተነሳ እዚያው ይሞታል፤ በከተማዋ ውስጥ ዳቦ የሚባል ነገር የለምና።”+ 10  ከዚያም ንጉሡ ኢትዮጵያዊውን ኤቤድሜሌክን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ከዚህ 30 ሰዎች ይዘህ ሂድ፤ ነቢዩ ኤርምያስንም ከመሞቱ በፊት ከውኃ ማጠራቀሚያው ጉድጓድ ውስጥ ጎትተህ አውጣው።” 11  በመሆኑም ኤቤድሜሌክ ሰዎቹን ይዞ በንጉሡ ቤት* ከግምጃ ቤቱ+ ሥር ወዳለው ቦታ ሄደ፤ ከዚያም የተቦጫጨቀ ጨርቅና ያረጀ ልብስ ከዚያ ወስደው በውኃ ማጠራቀሚያው ጉድጓድ ውስጥ ላለው ለኤርምያስ በገመድ አወረዱለት። 12  ኢትዮጵያዊው ኤቤድሜሌክ ኤርምያስን “ይህን የተቦጫጨቀ ጨርቅና ያረጀ ልብስ በብብትህና በገመዱ መካከል አድርገው” አለው። ኤርምያስም እንደተባለው አደረገ፤ 13  እነሱም ኤርምያስን በገመዱ ጎትተው ከውኃ ማጠራቀሚያው ጉድጓድ ውስጥ አወጡት። ኤርምያስም በክብር ዘቦቹ ግቢ+ ተቀመጠ። 14  ንጉሥ ሴዴቅያስ ሰው ልኮ ነቢዩ ኤርምያስን እሱ ወዳለበት፣ በይሖዋ ቤት ወደሚገኘው ወደ ሦስተኛው መግቢያ አስመጣው፤ ንጉሡም ኤርምያስን “አንድ ነገር ልጠይቅህ እፈልጋለሁ። ምንም ነገር እንዳትደብቀኝ” አለው። 15  በዚህ ጊዜ ኤርምያስ ሴዴቅያስን “ብነግርህ ትገድለኛለህ። ብመክርህም አትሰማኝም” አለው። 16  ንጉሥ ሴዴቅያስም በሚስጥር ለኤርምያስ እንዲህ ሲል ማለለት፦ “ይህን ሕይወት በሰጠን* ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ አልገድልህም፤ ሕይወትህን ለማጥፋት ለሚሹት* ለእነዚህ ሰዎችም አሳልፌ አልሰጥህም።” 17  ከዚያም ኤርምያስ ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለባቢሎን ንጉሥ መኳንንት እጅህን ብትሰጥ* ሕይወትህ ትተርፋለች፤* ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፤ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ በሕይወት ትተርፋላችሁ።+ 18  ለባቢሎን ንጉሥ መኳንንት እጅህን የማትሰጥ ከሆነ* ግን ይህች ከተማ ለከለዳውያን አልፋ ትሰጣለች፤ እነሱም በእሳት ያቃጥሏታል፤+ አንተም ከእጃቸው አታመልጥም።’”+ 19  ከዚያም ንጉሥ ሴዴቅያስ ኤርምያስን “ወደ ከለዳውያን የኮበለሉትን አይሁዳውያን እፈራለሁ፤ ለእነሱ አሳልፈው የሰጡኝ እንደሆነ ሊያሠቃዩኝ ይችላሉ” አለው። 20  ኤርምያስ ግን እንዲህ አለው፦ “ለእነሱ አሳልፈው አይሰጡህም። እባክህ የምነግርህን የይሖዋን ቃል ታዘዝ፤ መልካምም ይሆንልሃል፤ በሕይወትም ትኖራለህ።* 21  እጅህን ለመስጠት* ፈቃደኛ ካልሆንክ ግን ይሖዋ የገለጠልኝ ነገር ይህ ነው፦ 22  እነሆ፣ በይሁዳ ንጉሥ ቤት* የቀሩት ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ይወሰዳሉ፤+ እነሱም እንዲህ ይላሉ፦‘ተማምነህባቸው የነበሩት ሰዎች* አታለውሃል፤ ደግሞም አሸንፈውሃል።+ እግርህ ጭቃ ውስጥ እንዲሰምጥ አድርገዋል። አሁን አፈግፍገው ተመልሰዋል።’ 23  “ሚስቶችህንና ወንዶች ልጆችህን ሁሉ ለከለዳውያን ይሰጣሉ፤ አንተም ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይልቁንም የባቢሎን ንጉሥ ይይዝሃል፤+ በአንተም ምክንያት ይህች ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።”+ 24  ከዚያም ሴዴቅያስ ኤርምያስን እንዲህ አለው፦ “ስለዚህ ጉዳይ ማንም ሰው እንዳይሰማ፤ አለዚያ ትሞታለህ። 25  መኳንንቱ ከአንተ ጋር እንደተነጋገርኩ ሰምተው ወደ አንተ ቢመጡና ‘ለንጉሡ የነገርከውን ነገር እስቲ ንገረን። ምንም ነገር አትደብቀን፤ እኛም አንገድልህም።+ ንጉሡ የነገረህ ምንድን ነው?’ ቢሉህ፣ 26  ‘በዚያ እንዳልሞት ንጉሡ ወደ የሆናታን ቤት መልሶ እንዳይልከኝ ስለምነው ነበር’ በላቸው።”+ 27  በኋላም መኳንንቱ ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁት። እሱም ንጉሡ እንዲናገር ያዘዘውን ቃል ሁሉ ነገራቸው። እነሱም ከዚያ በኋላ ምንም አላሉትም፤ ያደረጉትን ውይይት የሰማ ሰው አልነበረምና። 28  ኤርምያስ ኢየሩሳሌም እስከተያዘችበት ጊዜ ድረስ በክብር ዘቦቹ ግቢ+ ተቀመጠ፤ ኢየሩሳሌም በተያዘችበት ጊዜም እዚያው ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በበሽታ።”
ቃል በቃል “ወደ ከለዳውያን የሚወጣ።”
ወይም “ነፍሱ።”
ወይም “ሕይወቱን ያተርፋል።”
ቃል በቃል “እጆች።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ነፍስህን ለሚሿት።”
ወይም “ይህችን ነፍስ በፈጠረልን።”
ቃል በቃል “ወደ ባቢሎን ንጉሥ መኳንንት ብትወጣ።”
ወይም “ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች።”
ቃል በቃል “ወደ ባቢሎን ንጉሥ መኳንንት የማትወጣ ከሆነ።”
ወይም “ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች።”
ቃል በቃል “ለመውጣት።”
ቃል በቃል “የሰላምህ ሰዎች።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”