ኤርምያስ 4:1-31

  • ንስሐ መግባት በረከት ያስገኛል (1-4)

  • ከሰሜን ጥፋት ይመጣል (5-18)

  • ኤርምያስ የተሰማው ሐዘን (19-31)

4  “እስራኤል ሆይ፣ ብትመለስ” ይላል ይሖዋ፣“ወደ እኔ ብትመለስ፣አስጸያፊ ጣዖቶችህን ከፊቴ ብታስወግድተንከራታች አትሆንም።+   ‘በእውነት፣ በፍትሕና በጽድቅሕያው ይሖዋን!’ ብለህ ብትምል፣ብሔራት በእሱ አማካኝነት በረከት ያገኛሉ፤በእሱም ይኮራሉ።”+  ይሖዋ ለይሁዳ ሰዎችና ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላልና፦ “ያልለማውን መሬት እረሱ፤በእሾህ መካከልም አትዝሩ።+   እናንተ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ለይሖዋ ተገረዙ፤የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ፤+አለዚያ በክፉ ሥራችሁ የተነሳቁጣዬ እንደ እሳት ይነድዳል፤ማንም ሊያጠፋው አይችልም።”+   ይህን በይሁዳ ተናገሩ፤ በኢየሩሳሌምም አውጁ። ጩኹ፤ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ቀንደ መለከት ንፉ።+ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዲህ በሉ፦ “አንድ ላይ ተሰብሰቡ፤ወደተመሸጉት ከተሞችም እንሽሽ።+   ወደ ጽዮን የሚጠቁም ምልክት* አቁሙ። መጠለያ ፈልጉ፤ ዝም ብላችሁም አትቁሙ።” ከሰሜን ጥፋት ብሎም ታላቅ መዓት አመጣለሁና።+   ጠላት እንደ አንበሳ ከጥሻው ውስጥ ወጥቷል፤+ብሔራትንም የሚያጠፋው ተነስቷል።+ ምድርሽን አስፈሪ ቦታ ሊያደርግ ከቦታው ወጥቷል። ከተሞችሽ አንድም ሰው የማይኖርባቸው የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ።+   ስለዚህ ማቅ ልበሱ፤+እዘኑ፤* ዋይ ዋይም በሉ፤ምክንያቱም የሚነደው የይሖዋ ቁጣ ከእኛ አልተመለሰም።   “በዚያ ቀን” ይላል ይሖዋ፣ “የንጉሡ ልብናየመኳንንቱ ልብ ይቀልጣል፤*+ካህናቱም ይሸበራሉ፤ ነቢያቱም ይገረማሉ።”+ 10  ከዚያም እንዲህ አልኩ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ወዮ! ሰይፍ አንገታችን ላይ ተጋድሞ* እያለ ‘ሰላም ታገኛላችሁ’+ ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ አታለሃል።”+ 11  በዚያን ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይባላል፦ “የሚለበልብ ነፋስ በበረሃ ከሚገኙ ጠፍ ኮረብቶች ተነስቶወደ ሕዝቤ ሴት ልጅ* በፍጥነት ይነፍሳል፤ነፋሱ የሚነፍሰው እህል ለማዝራትም* ሆነ ለማጥራት አይደለም። 12  በእኔ ትእዛዝ ኃይለኛው ነፋስ ከእነዚህ ስፍራዎች ይመጣል። አሁን በእነሱ ላይ ፍርድ አስተላልፋለሁ። 13  እነሆ፣ እሱ ዝናብ እንዳዘሉ ደመናት ይመጣል፤ሠረገሎቹም እንደ አውሎ ነፋስ ናቸው።+ ፈረሶቹ ከንስር ይበልጥ ፈጣኖች ናቸው።+ ጠፍተናልና ወዮልን! 14  ኢየሩሳሌም ሆይ፣ እንድትድኚ ልብሽን ከክፋት ሁሉ አጥሪ።+ እስከ መቼ በውስጥሽ ክፉ ሐሳብ ይዘሽ ትኖሪያለሽ? 15  አንድ ድምፅ ከዳን ዜናውን ይናገራልና፤+ከኤፍሬም ተራሮችም ጥፋትን ያውጃል። 16  ይህን አሳውቁ፤ አዎ ለብሔራት ተናገሩ፤በኢየሩሳሌም ላይ አውጁ።” “ጠባቂዎች* ከሩቅ አገር እየመጡ ነው፤በይሁዳ ከተሞችም ላይ ይጮኻሉ። 17  ማሳ እንደሚጠብቁ ሰዎች ከሁሉም አቅጣጫ ይመጡባታል፤+ምክንያቱም እሷ በእኔ ላይ ዓምፃለች”+ ይላል ይሖዋ። 18  “ለተከተልሽው መንገድና ለፈጸምሽው ተግባር ዋጋሽን ትቀበያለሽ።+ የሚደርስብሽ ጥፋት ምንኛ መራራ ነው፤ወደ ልብሽ ዘልቆ ይገባልና!” 19  ወይ አበሳዬ!* ወይ አበሳዬ! ልቤን ሥቃይ ቀስፎታል። ልቤ በውስጤ በኃይል ይመታል። ዝም ማለት አልችልም፤የቀንደ መለከት ድምፅ፣የጦርነት ማስጠንቀቂያ ድምፅ* ሰምቻለሁና።*+ 20  በጥፋት ላይ ጥፋት መድረሱ ተወርቷል፤ምድሪቱ በሙሉ ወድማለችና። የገዛ ድንኳኖቼ በድንገት፣የድንኳን ሸራዎቼም በቅጽበት ጠፍተዋል።+ 21  ምልክቱን* የማየውናየቀንደ መለከቱን ድምፅ የምሰማው እስከ መቼ ድረስ ነው?+ 22  “ሕዝቤ ሞኝ ነውና፤+እነሱ ለእኔ ትኩረት አይሰጡም። ማስተዋል የሌላቸው ቂል ልጆች ናቸው። ክፉ ነገር ለማድረግ ብልሃተኞች* ናቸው፤መልካም ነገር ማድረግ ግን አያውቁም።” 23  ምድሪቱን አየሁ፤ እነሆም፣ ባዶና ወና ነበረች።+ ወደ ሰማያት ተመለከትኩ፤ ብርሃናቸው ጠፍቶ ነበር።+ 24  ተራሮቹን አየሁ፤ እነሆ፣ ይናወጡ ነበር፤ኮረብቶቹም ይንቀጠቀጡ ነበር።+ 25  እኔም ተመለከትኩ፤ እነሆ፣ በዚያ አንድም ሰው አልነበረም፤የሰማይ ወፎችም ሁሉ ሸሽተው ነበር።+ 26  እኔም አየሁ፤ እነሆ፣ የፍራፍሬ እርሻው ምድረ በዳ ሆኖ ነበር፤ከተሞቹም ሁሉ ፈራርሰው ነበር።+ ይህም የሆነው በይሖዋ፣በሚነደውም ቁጣው የተነሳ ነው። 27  ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ “ምድሪቱ በሙሉ ባድማ ትሆናለች፤+ሆኖም ፈጽሜ አላጠፋትም። 28  ከዚህ የተነሳ ምድሪቱ ታዝናለች፤+በላይ ያሉት ሰማያትም ይጨልማሉ።+ ምክንያቱም እኔ ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም ወስኛለሁ፤ሐሳቤንም አለውጥም፤* ወደ ኋላም አልመለስም።+ 29  ከፈረሰኞቹና ከቀስተኞቹ ድምፅ የተነሳከተማዋ በሙሉ ትሸሻለች።+ ጥሻ ውስጥ ይገባሉ፤ዓለቶቹም ላይ ይወጣሉ።+ ከተሞቹ ሁሉ ተትተዋል፤የሚኖርባቸውም ሰው የለም።” 30  ለጥፋት ተዳርገሻል፤ ታዲያ ምን ታደርጊ ይሆን? ደማቅ ቀይ ልብስ ትጎናጸፊ፣በወርቅ ጌጣጌጦች ታጌጪናዓይኖችሽን ትኳዪ ነበር። ይሁንና ትዋቢ የነበረው እንዲያው በከንቱ ነው፤+በፍትወት ስሜት ይከተሉሽ የነበሩት ትተውሻልና፤አሁን ሕይወትሽን* ይሿታል።+ 31  እንደታመመች ሴት ድምፅ፣የመጀመሪያ ልጇንም ለመውለድ እንደምታምጥ ሴት ያለ የጭንቅ ድምፅ፣ደግሞም ትንፋሽ አጥሯት ቁና ቁና የምትተነፍሰውን የጽዮን ሴት ልጅ ድምፅ ሰምቻለሁና። እሷም እጆቿን ዘርግታ+ “ወዮልኝ! ከገዳዮች የተነሳ ዝያለሁና”* ትላለች።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለምልክት የሚተከል ምሰሶ።”
ወይም “ደረታችሁን ምቱ።”
ወይም “መኳንንቱ ወኔ ይከዳቸዋል።”
ወይም “ሰይፍ ነፍሳችን ላይ ደርሶ።”
በሰውኛ ዘይቤ የተገለጸ ቅኔያዊ አነጋገር፤ አዘኔታን ወይም ርኅራኄን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
እህልን ወደ ላይ በመበተንና ለነፋስ በመስጠት ከገለባ መለየት።
ቃል በቃል “ተመልካቾች።” መቼ ጥቃት መሰንዘር እንዳለባቸው ለመወሰን ከተማዋን የሚቃኙ ሰዎችን ያመለክታል።
ቃል በቃል “አንጀቴ።”
“የውጊያ ሁካታ ድምፅ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሴ ሰምታለችና።”
ወይም “ለምልክት የሚተከለውን ምሰሶ።”
ወይም “ጥበበኞች።”
ወይም “አልጸጸትም።”
ወይም “ነፍስሽን።”
ወይም “ነፍሴ ዝላለችና።”