ኤርምያስ 41:1-18

  • እስማኤል ጎዶልያስን ገደለው (1-10)

  • ዮሃናን እስማኤልን አሳደደው (11-18)

41  በሰባተኛው ወር፣ ከንጉሣውያን ቤተሰብ* የሆነውና ከንጉሡ ባለሥልጣናት አንዱ የነበረው የኤሊሻማ ልጅ፣ የነታንያህ ልጅ እስማኤል+ ከሌሎች አሥር ሰዎች ጋር ሆኖ በምጽጳ+ ወዳለው ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ። በምጽጳ አንድ ላይ ምግብ እየበሉ ሳለ 2  የነታንያህ ልጅ እስማኤልና ከእሱ ጋር የነበሩት አሥሩ ሰዎች ተነስተው የሳፋንን ልጅ፣ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መተው ገደሉት። በዚህ መንገድ እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ በምድሪቱ ላይ የሾመውን ሰው ገደለው። 3  በተጨማሪም እስማኤል በምጽጳ ከጎዶልያስ ጋር የነበሩትን አይሁዳውያን በሙሉ እንዲሁም በዚያ የነበሩትን ከለዳውያን ወታደሮች ገደላቸው። 4  ጎዶልያስ በተገደለ በሁለተኛው ቀን ስለ ሁኔታው ማንም ሰው ከማወቁ በፊት፣ 5  ከሴኬም፣+ ከሴሎና+ ከሰማርያ+ 80 ሰዎች መጡ። ጢማቸውን ላጭተው፣ ልብሳቸውን ቀደውና ሰውነታቸውን ተልትለው+ የነበረ ሲሆን በይሖዋ ቤት የሚያቀርቧቸውን የእህል መባዎችና ነጭ ዕጣን+ ይዘው ነበር። 6  የነታንያህ ልጅ እስማኤልም ከእነሱ ጋር ለመገናኘት ከምጽጳ ወጥቶ እያለቀሰ ሄደ። ባገኛቸው ጊዜ “ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ” አላቸው። 7  ሆኖም ወደ ከተማዋ ሲገቡ የነታንያህ ልጅ እስማኤልና ከእሱ ጋር የነበሩት ሰዎች አረዷቸው፤ ወደ ውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድም ጣሏቸው። 8  ይሁንና በመካከላቸው የነበሩ አሥር ሰዎች እስማኤልን “በእርሻ ውስጥ የደበቅነው የተከማቸ እህል ይኸውም ስንዴ፣ ገብስ፣ ዘይትና ማር ስላለን አትግደለን” አሉት። ስለዚህ ከወንድሞቻቸው ጋር አልገደላቸውም። 9  እስማኤል የገደላቸውን ሰዎች አስከሬን በሙሉ በአንድ ትልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ውስጥ ጣለ፤ ይህ ጉድጓድ ንጉሥ አሳ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ባስፈራራው ጊዜ የሠራው ነበር።+ የነታንያህ ልጅ እስማኤል ይህን ጉድጓድ ባረዳቸው ሰዎች አስከሬን ሞላው። 10  እስማኤል በምጽጳ+ የቀረውን ሕዝብ በሙሉ ይኸውም የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን+ በላያቸው ገዢ አድርጎ የሾመባቸውን፣ የንጉሡን ሴቶች ልጆችና በምጽጳ የቀሩትን ሰዎች ሁሉ ማረከ። የነታንያህ ልጅ እስማኤል እነሱን ማርኮ ወደ አሞናውያን ለመሻገር ጉዞ ጀመረ።+ 11  የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን+ እና ከእሱ ጋር የነበሩት የሠራዊቱ አለቆች የነታንያህ ልጅ እስማኤል ስላደረገው ክፉ ነገር ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ 12  ከእነሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ይዘው ከነታንያህ ልጅ ከእስማኤል ጋር ለመዋጋት ሄዱ፤ እሱንም በገባኦን ባለው በታላቁ ውኃ* አጠገብ አገኙት። 13  ከእስማኤል ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ የቃሬሃን ልጅ ዮሃናንን እና ከእሱ ጋር የነበሩትን የሠራዊቱን አለቆች ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው። 14  ከዚያም እስማኤል ከምጽጳ+ ማርኮ የወሰዳቸው ሰዎች ሁሉ ዞረው ከቃሬሃ ልጅ ከዮሃናን ጋር ተመለሱ። 15  የነታንያህ ልጅ እስማኤልና ከእሱ ጋር የነበሩት ስምንት ሰዎች ግን ከዮሃናን ፊት ሸሽተው ወደ አሞናውያን ሄዱ። 16  የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን እና ከእሱ ጋር የነበሩት የሠራዊቱ አለቆች ሁሉ ከምጽጳ የተወሰዱትን የቀሩትን ሰዎች ይዘዋቸው ሄዱ፤ እነዚህ ሰዎች የነታንያህ ልጅ እስማኤል፣ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ከገደለው በኋላ+ ዮሃናን እና የሠራዊቱ አለቆች ከእሱ የታደጓቸው ናቸው። ወንዶቹን፣ ወታደሮቹን፣ ሴቶቹንና ልጆቹን እንዲሁም የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱን ከገባኦን መልሰው አመጧቸው። 17  ከዚያም ተነስተው ሄዱ፤ ወደ ግብፅ ለመሄድ+ ስላሰቡም በቤተልሔም+ አጠገብ በሚገኘው በኪምሃም ማረፊያ ቦታ ቆዩ፤ 18  ይህን ያደረጉት ከከለዳውያን የተነሳ ነው። የነታንያህ ልጅ እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ በምድሪቱ ላይ ሾሞት የነበረውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ስለገደለው ከለዳውያንን ፈርተዋቸው ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የመንግሥት ዘር።”
“በታላቁ ኩሬ” ማለትም ሊሆን ይችላል።