ኤርምያስ 43:1-13
43 ኤርምያስ አምላካቸው ይሖዋ ለእነሱ እንዲነግራቸው የላከውን የአምላካቸውን የይሖዋን ቃል ሁሉ፣ አንድም ሳያስቀር ለሕዝቡ በሙሉ ተናግሮ ሲጨርስ
2 የሆሻያህ ልጅ አዛርያስ፣ የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን+ እና እብሪተኛ የሆኑት ሰዎች ሁሉ ኤርምያስን እንዲህ አሉት፦ “የምትናገረው ነገር ውሸት ነው! አምላካችን ይሖዋ ‘በግብፅ ለመኖር ወደዚያ አትሂዱ’ ብሎ አላከህም።
3 ከዚህ ይልቅ ከለዳውያን እንዲገድሉን ወይም ወደ ባቢሎን በግዞት እንዲወስዱን በእጃቸው አሳልፈህ ትሰጠን ዘንድ በእኛ ላይ ያነሳሳህ የነሪያህ ልጅ ባሮክ+ ነው።”+
4 በመሆኑም የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን፣ የሠራዊቱ አለቆች ሁሉና ሕዝቡ በሙሉ በይሁዳ ምድር እንዲቀመጡ ያዘዛቸውን የይሖዋን ቃል አልሰሙም።
5 እንዲያውም የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን እና የሠራዊቱ አለቆች በሙሉ፣ በይሁዳ ምድር ለመኖር ከተበተኑባቸው ብሔራት ሁሉ የተመለሱትን የይሁዳ ቀሪዎች በሙሉ ይዘው ሄዱ።+
6 ወንዶቹን፣ ሴቶቹን፣ ልጆቹን፣ የንጉሡን ሴቶች ልጆችና የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን+ ከሳፋን+ ልጅ፣ ከአኪቃም+ ልጅ ከጎዶልያስ+ ጋር የተዋቸውን ሁሉ* እንዲሁም ነቢዩን ኤርምያስንና የነሪያህን ልጅ ባሮክን ይዘው ሄዱ።
7 የይሖዋን ቃል ባለመታዘዝ ወደ ግብፅ ምድር ገቡ፤ እስከ ጣፍነስ+ ድረስም ሄዱ።
8 ከዚያም የይሖዋ ቃል በጣፍነስ እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦
9 “ትላልቅ ድንጋዮችን ውሰድና አይሁዳውያኑ እያዩ በጣፍነስ በሚገኘው በፈርዖን ቤት መግቢያ፣ ከጡብ ከተሠራው መደብ ሥር ሸሽገህ በቅጥራን ለስናቸው።
10 ከዚያም እንዲህ በላቸው፦ ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ አገልጋዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን* እጠራዋለሁ፤+ ዙፋኑንም እኔ ከሸሸግኳቸው ከእነዚህ ድንጋዮች በላይ አስቀምጣለሁ፤ ንጉሣዊ ድንኳኑንም በእነሱ ላይ ይዘረጋል።+
11 እሱም መጥቶ የግብፅን ምድር ይመታል።+ ገዳይ መቅሰፍት የሚገባው ሁሉ ለገዳይ መቅሰፍት፣ በምርኮ መወሰድ የሚገባው ሁሉ ለምርኮ እንዲሁም ሰይፍ የሚገባው ሁሉ ለሰይፍ ይሰጣል።+
12 የግብፅን አማልክት ቤቶችም* በእሳት አያይዛለሁ፤+ እሱም ያቃጥላቸዋል፤ ማርኮም ይወስዳቸዋል። እረኛ ልብሱን እንደሚጎናጸፍ የግብፅን ምድር ይጎናጸፋል፤ ከዚያም ቦታ በሰላም* ይሄዳል።
13 በግብፅም ምድር የሚገኙትን የቤትሼሜሽን* ዓምዶች* ይሰባብራል፤ የግብፅን አማልክት ቤቶችም* በእሳት ያቃጥላል።”’”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ነፍሳት ሁሉ።”
^ ቃል በቃል “ናቡከደረጾርን።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
^ ወይም “ቤተ መቅደሶችም።”
^ ወይም “ጉዳት ሳይደርስበት።”
^ ወይም “የፀሐይን ቤት (ቤተ መቅደስ)።” ሂሊዮፖሊስ ማለት ነው።
^ ወይም “ሐውልቶች።”
^ ወይም “ቤተ መቅደሶችም።”