ኤርምያስ 46:1-28

  • በግብፅ ላይ የተነገረ ትንቢት (1-26)

    • ናቡከደነጾር ግብፅን ድል ያደርጋል (13, 26)

  • ለእስራኤል የተገባ ቃል (27, 28)

46  ብሔራትን አስመልክቶ ወደ ነቢዩ ኤርምያስ የመጣው የይሖዋ ቃል ይህ ነው፦+ 2  የኢዮስያስ ልጅ የሆነው የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓቄም+ በነገሠ በአራተኛው ዓመት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውንና የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* በካርከሚሽ ድል ያደረገውን የግብፅን ንጉሥ የፈርዖን ኒካዑን+ ሠራዊት በተመለከተ ለግብፅ+ የተነገረ መልእክት፦  3  “ትንሹንና* ትልቁን ጋሻችሁን አዘጋጁ፤ለውጊያም ውጡ።  4  እናንተ ፈረሰኞች፣ ፈረሶችን ጫኑ፤ በላያቸውም ተቀመጡ። ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ የራስ ቁራችሁንም አድርጉ። ጦሩን ወልውሉ፤ ጥሩራችሁንም ልበሱ።  5  ‘እንዲህ ተሸብረው ያየኋቸው ለምንድን ነው? እያፈገፈጉ ነው፤ ተዋጊዎቻቸው ተፍረክርከዋል። በድንጋጤ እግሬ አውጪኝ ብለዋል፤ ተዋጊዎቻቸው ወደ ኋላ አልተመለከቱም። በየቦታው ሽብር ነግሦአል’ ይላል ይሖዋ።  6  ‘ፈጣን የሆኑት መሸሽ አይችሉም፤ ተዋጊዎቹም ማምለጥ አይችሉም። በሰሜን በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻተሰናክለው ወድቀዋል።’+  7  እንደ አባይ ወንዝ፣እንደሚናወጥም የወንዝ ውኃ ሆኖ የሚመጣው ይህ ማን ነው?  8  ግብፅ እንደ አባይ ወንዝና+እንደሚናወጥ የወንዝ ውኃ ሆኖ ይመጣል፤ደግሞም ‘እወጣለሁ፤ ምድርንም እሸፍናለሁ። ከተማዋንና ነዋሪዎቿን አጠፋለሁ’ ይላል።  9  እናንተ ፈረሶች፣ ወደ ላይ ውጡ! እናንተ ሠረገሎች፣ በፍጥነት ገስግሱ! ተዋጊዎቹ ይውጡ፤ጋሻ የሚያነግቡት የኢትዮጵያ* እና የፑጥ ሰዎች+እንዲሁም ደጋን የመወጠርና*+ በጥበብ የመጠቀም ችሎታ ያላቸው የሉድ+ ሰዎች ይውጡ። 10  “ያ ቀን የሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ነው፤ ጠላቶቹን የሚበቀልበት የበቀል ቀን ነው። ሰይፉ ይበላል፤ ይጠግባልም፤ ደማቸውንም እስኪረካ ድረስ ይጠጣል፤ ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት አምላክ ይሖዋ በኤፍራጥስ ወንዝ+ አጠገብ በሚገኘው የሰሜን ምድር መሥዋዕት* አዘጋጅቷልና። 11  ድንግሊቱ የግብፅ ሴት ልጅ ሆይ፣ወደ ጊልያድ ወጥተሽ በለሳን አምጪ።+ መድኃኒት የምታበዢው እንዲያው በከንቱ ነው፤ፈውስ አታገኚምና።+ 12  ብሔራት በአንቺ ላይ የደረሰውን ውርደት ሰምተዋል፤+ጩኸትሽም አገር ምድሩን አናውጧል። ተዋጊ በተዋጊው ይሰናከላልና፤ሁለቱም በአንድነት ተያይዘው ወድቀዋል።” 13  የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር* የግብፅን ምድር ለመምታት ስለመምጣቱ ይሖዋ ለነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦+ 14  “ይህን በግብፅ ተናገሩ፤ በሚግዶል+ አውጁት። በኖፍ* እና በጣፍነስ+ አውጁት። እንዲህም በሉ፦ ‘ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ ተዘጋጁም፤ሰይፍ በዙሪያችሁ ያለውን ሁሉ ይበላልና። 15  ኃያላኖቻችሁ ተጠራርገው የጠፉት ለምንድን ነው? ጸንተው መቆም አልቻሉም፤ይሖዋ ገፍትሮ ጥሏቸዋልና። 16  ብዙዎቹ ይሰናከላሉ፤ ደግሞም ይወድቃሉ። እርስ በርሳቸውም “ተነሱ! ከጨካኙ ሰይፍ የተነሳወደ ሕዝባችንና ወደ ትውልድ አገራችን እንመለስ” ይባባላሉ።’ 17  በዚያም ‘ያገኘውን አጋጣሚ* ያልተጠቀመበትየግብፅ ንጉሥ ፈርዖንጉራውን የሚነዛው በከንቱ ነው’ ብለዋል።+ 18  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ተብሎ የተጠራው ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤እሱ* በተራሮች መካከል እንዳለው እንደ ታቦርና+በባሕር አጠገብ እንዳለው እንደ ቀርሜሎስ+ ሆኖ ይመጣል። 19  አንቺ በግብፅ የምትኖሪ ሴት ልጅ ሆይ፣በግዞት ለመሄድ ጓዝሽን አሰናጂ። ኖፍ* አስፈሪ ቦታ ትሆናለችና፤በእሳት ትጋያለች፤* ማንም ሰው የማይኖርባትም ምድር ትሆናለች።+ 20  ግብፅ እንደምታምር ጊደር ናት፤ሆኖም ከሰሜን ተናዳፊ ዝንቦች ይመጡባታል። 21  በመካከሏ ያሉት ቅጥረኛ ወታደሮችም እንኳ እንደሰቡ ጥጆች ናቸው፤ይሁንና እነሱም ጭምር ወደ ኋላ ተመልሰው በአንድነት ሸሽተዋል። ጸንተው መቆም አልቻሉም፤+የሚጠፉበት ቀን፣የሚመረመሩበትም ጊዜ ደርሶባቸዋልና።’ 22  ‘ድምፅዋ እየተጥመዘመዘ እንደሚሄድ እባብ ድምፅ ነው፤ዛፍ እንደሚቆርጡ* ሰዎችመጥረቢያ ይዘው በኃይል ይመጡባታልና። 23  በውስጡ ማለፍ የማይቻል ቢመስልም ጫካዋን ይመነጥራሉ’ ይላል ይሖዋ። ‘ቁጥራቸው ከአንበጣ ይበልጥ ይበዛልና፤ ስፍር ቁጥርም የላቸውም። 24  የግብፅ ሴት ልጅ ለኀፍረት ትዳረጋለች። ለሰሜን ሰዎች ትሰጣለች።’+ 25  “የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘አሁን ትኩረቴን በኖእ*+ ከተማ ወደሚገኘው ወደ አምዖን፣+ ወደ ፈርዖን፣ ወደ ግብፅ፣ ወደ አማልክቷና+ ወደ ነገሥታቷ፣ አዎ በፈርዖንና በእሱ ወደሚታመኑት ሰዎች ሁሉ አደርጋለሁ።’+ 26  “‘ሕይወታቸውን ማጥፋት ለሚሹ* ሰዎች፣ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነጾርና* ለአገልጋዮቹ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።+ ከዚያ በኋላ ግን እንደቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች’ ይላል ይሖዋ።+ 27  ‘አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፣ አትፍራ፤እስራኤልም ሆይ፣ አትሸበር።+ አንተን ከሩቅ ቦታ፣ዘሮችህንም ተማርከው ከተወሰዱበት ምድር አድናለሁና።+ ያዕቆብ ይመለሳል፤ የሚያስፈራውም ሳይኖርተረጋግቶና ሰላም አግኝቶ ይቀመጣል።+ 28  ስለዚህ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፣ አትፍራ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘እኔ ከአንተ ጋር ነኝና። አንተን የበተንኩባቸውን ብሔራት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋቸዋለሁ፤+አንተን ግን ሙሉ በሙሉ አላጠፋህም።+ በተገቢው መጠን እገሥጽሃለሁ* እንጂ+በምንም ዓይነት ሳልቀጣ አልተውህም።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
አብዛኛውን ጊዜ ቀስተኞች የሚይዙት ትንሽ ጋሻ።
ቃል በቃል “የመርገጥና።”
ወይም “የኩሽ።”
ወይም “እርድ።”
ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “በሜምፊስ።”
ቃል በቃል “የተወሰነውን ጊዜ።”
ግብፅን ድል የሚያደርገውን ያመለክታል።
ወይም “ሜምፊስ።”
“ጠፍ መሬት ትሆናለች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “እንጨት እንደሚሰበስቡ።”
ቴብስን ያመለክታል።
ወይም “ነፍሳቸውን ለሚሹ።”
ቃል በቃል “ለናቡከደረጾርና።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “አርምሃለሁ።”