ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 10:1-39
10 ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ+ ነው እንጂ የእነዚህ ነገሮች እውነተኛ አካል አይደለም፤ ስለዚህ ሕጉ ከዓመት ዓመት እነዚያኑ መሥዋዕቶች በማቅረብ አምላክን የሚያመልኩትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው አይችልም።*+
2 ቢችልማ ኖሮ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረም? ምክንያቱም ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት ሰዎች አንዴ ከነጹ በኋላ ሕሊናቸው በጥፋተኝነት ስሜት አይወቅሳቸውም ነበር።
3 ይሁንና እነዚህ መሥዋዕቶች ከዓመት ዓመት ኃጢአት እንዲታወስ ያደርጋሉ፤+
4 የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልምና።
5 ስለዚህ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ፦ “‘መሥዋዕትንና መባን አልፈለግክም፤ ከዚህ ይልቅ አካል አዘጋጀህልኝ።
6 ሙሉ በሙሉ በሚቃጠል መባና ለኃጢአት በሚቀርብ መባ ደስ አልተሰኘህም።’+
7 በዚህ ጊዜ ‘እነሆ፣ አምላክ ሆይ፣ (ስለ እኔ በመጽሐፍ ጥቅልል እንደተጻፈ) ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ’ አልኩ።”+
8 በመጀመሪያ እንዲህ አለ፦ “መሥዋዕትን፣ መባን፣ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባንና ለኃጢአት የሚቀርብ መባን አልፈለግክም፤ እንዲሁም ደስ አልተሰኘህበትም።” እነዚህ መሥዋዕቶች ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት የሚቀርቡ ናቸው።
9 ከዚያም “እነሆ፣ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” አለ።+ ሁለተኛውን ለማቋቋም የመጀመሪያውን ያስወግዳል።
10 በዚህ “ፈቃድ”+ መሠረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ በቀረበው የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አማካኝነት ተቀድሰናል።+
11 በተጨማሪም እያንዳንዱ ካህን ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብና*+ ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የማይችሉትን+ እነዚያኑ መሥዋዕቶች በየጊዜው ለማቅረብ+ ዕለት ዕለት በቦታው ይገኛል።
12 ይህ ሰው ግን ስለ ኃጢአት ለሁልጊዜ የሚሆን አንድ መሥዋዕት አቅርቦ በአምላክ ቀኝ ተቀምጧል፤+
13 ከዚያን ጊዜ አንስቶ ጠላቶቹ የእግሩ መርገጫ እስኪደረጉ ድረስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።+
14 እነዚያን የሚቀደሱትን ለሁልጊዜ ፍጹማን ያደረጋቸው አንድ መሥዋዕት በማቅረብ ነውና።+
15 ከዚህ በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስም ስለ እኛ ይመሠክራል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላልና፦
16 “‘ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእነሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው’ ይላል ይሖዋ።* ‘ሕግጋቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ፤ በአእምሯቸውም ላይ እጽፋቸዋለሁ።’”+
17 በመቀጠልም “ኃጢአታቸውንና የዓመፅ ድርጊታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስም” ይላል።+
18 እንግዲህ እነዚህ ይቅር ከተባሉ፣ ከዚህ በኋላ ለኃጢአት መባ ማቅረብ አያስፈልግም።
19 ስለዚህ ወንድሞች፣ በኢየሱስ ደም አማካኝነት ወደ ቅዱሱ ስፍራ በሚወስደው መንገድ ለመግባት የሚያስችል ድፍረት* አግኝተናል፤+
20 እሱ የከፈተልን* ይህ መንገድ ወደ ሕይወት የሚመራ አዲስ መንገድ ነው። ይህን ያደረገው በመጋረጃው+ ማለትም በሥጋው በኩል በማለፍ ነው፤
21 በተጨማሪም በአምላክ ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን+
22 ከክፉ ሕሊና ለመንጻት+ ልባችንን ተረጭተን እንዲሁም ሰውነታችንን በንጹሕ ውኃ ታጥበን+ በቅን ልቦና እና በሙሉ እምነት ወደ አምላክ እንቅረብ።
23 የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ስለሆነ ተስፋችንን በይፋ ለማወጅ የሚያስችለንን አጋጣሚ ያላንዳች ማወላወል አጥብቀን እንያዝ።+
24 እንዲሁም እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት* እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤*+
25 አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን* ቸል አንበል፤+ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤+ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።+
26 የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ካገኘን በኋላ ሆን ብለን በኃጢአት ጎዳና ብንመላለስ+ ለኃጢአታችን የሚቀርብ ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤+
27 ከዚህ ይልቅ አስፈሪ ፍርድ ይጠብቀናል፤ አምላክን የሚቃወሙትን የሚበላ የሚነድ ቁጣም ይኖራል።+
28 የሙሴን ሕግ የጣሰ ማንኛውም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሠከሩበት ያለርኅራኄ ይገደል ነበር።+
29 ታዲያ የአምላክን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የቃል ኪዳኑን ደም+ እንደ ተራ ነገር የቆጠረና የጸጋን መንፈስ በንቀት ያጥላላ ሰው ምን ያህል የከፋ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?+
30 “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቀዋለንና። ደግሞም “ይሖዋ* ሕዝቡን ይዳኛል።”+
31 በሕያው አምላክ እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር ነው።
32 ይሁን እንጂ ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ+ በመከራ ውስጥ በከፍተኛ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀድሞውን ጊዜ ዘወትር አስታውሱ።
33 በአደባባይ ለነቀፋና ለመከራ የተጋለጣችሁባቸው* ጊዜያት ነበሩ፤ ደግሞም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰባቸውን ሰዎች መከራ የተጋራችሁባቸው* ጊዜያት ነበሩ።
34 እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ዘላቂ የሆነ ንብረት እንዳላችሁ ስለምታውቁ+ በእስር ላይ ላሉት ራራችሁላቸው፤ እንዲሁም ንብረታችሁ ሲዘረፍ ሁኔታውን በደስታ ተቀበላችሁ።+
35 እንግዲህ ትልቅ ወሮታ የሚያስገኘውን በድፍረት የመናገር ነፃነታችሁን አሽቀንጥራችሁ አትጣሉት።+
36 የአምላክን ፈቃድ ከፈጸማችሁ በኋላ የተስፋው ቃል ሲፈጸም ማየት እንድትችሉ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።+
37 ምክንያቱም “ለጥቂት ጊዜ ነው”+ እንጂ “የሚመጣው እሱ ይመጣል፤ ደግሞም አይዘገይም።”+
38 “ሆኖም ጻድቅ አገልጋዬ በእምነት ይኖራል”፤+ ደግሞም “ወደኋላ ቢያፈገፍግ በእሱ ደስ አልሰኝም።”*+
39 እንግዲህ እኛ በሕይወት የሚያኖር* እምነት እንዳላቸው ሰዎች ነን እንጂ ወደ ጥፋት እንደሚያፈገፍጉ ሰዎች አይደለንም።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ “ስለዚህ ሰዎች . . . ሊያደርጓቸው አይችሉም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት ለመስጠትና።”
^ ወይም “የመተማመን ስሜት።”
^ ቃል በቃል “የመረቀልን።”
^ ወይም “እናስብ።”
^ ወይም “አንዳችን ሌላውን ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መቀስቀስ ወይም ማነሳሳት።”
^ ለአምልኮ መሰብሰብን ያመለክታል።
^ ቃል በቃል “ቲያትር ላይ የቀረባችሁ ያህል የተጋለጣችሁባቸው።”
^ ወይም “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከደረሰባቸው ሰዎች ጎን የቆማችሁባቸው።”
^ ወይም “ነፍሴ በእሱ ደስ አትሰኝም።”
^ ወይም “ነፍስን ጠብቆ የሚያኖር።”