ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 11:1-40
11 እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው፤+ በተጨማሪም የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።
2 በጥንት ዘመን የኖሩት ሰዎች* የተመሠከረላቸው በዚህ አማካኝነት ነው።
3 ሥርዓቶቹ* የተቋቋሙት በአምላክ ቃል መሆኑን የምንረዳው በእምነት ነው፤ በመሆኑም የሚታየው ነገር ወደ ሕልውና የመጣው ከማይታዩ ነገሮች ነው።
4 አቤል፣ ቃየን ካቀረበው የበለጠ ዋጋ ያለው መሥዋዕት ለአምላክ በእምነት አቀረበ፤+ አምላክ ስጦታውን ስለተቀበለ* በዚህ እምነቱ የተነሳ ጻድቅ እንደሆነ ተመሥክሮለታል፤+ ቢሞትም እንኳ በእምነቱ አማካኝነት አሁንም ይናገራል።+
5 ሄኖክ+ ሞትን እንዳያይ በእምነት ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ፤ አምላክ ወደ ሌላ ቦታ ስለወሰደውም የትም ቦታ ሊገኝ አልቻለም፤+ ከመወሰዱ በፊት አምላክን በሚገባ ደስ እንዳሰኘ ተመሥክሮለት ነበርና።
6 በተጨማሪም ያለእምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታልና።+
7 ኖኅ+ ገና ስላልታዩት ነገሮች መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ከተቀበለ በኋላ+ አምላካዊ ፍርሃት ያሳየውና ቤተሰቡን ለማዳን መርከብ የሠራው በእምነት ነበር፤+ በዚህ እምነት አማካኝነትም ዓለምን ኮንኗል፤+ እንዲሁም በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ ለመውረስ በቅቷል።
8 አብርሃም+ በተጠራ ጊዜ ወደፊት ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ በመሄድ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም ይኖርበት የነበረውን ስፍራ ለቆ ወጣ።+
9 በባዕድ አገር እንደሚኖር እንግዳ በተስፋይቱ ምድር በእምነት ኖረ፤+ ደግሞም አብረውት የዚሁ ተስፋ ቃል ወራሾች ከሆኑት ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር+ በድንኳን ኖረ።+
10 አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን፣ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበርና።+
11 ሣራም የተስፋን ቃል የሰጠው እሱ ታማኝ* እንደሆነ አድርጋ ስላሰበች ዕድሜዋ ካለፈ በኋላም እንኳ ዘር ለመፀነስ በእምነት ኃይል አገኘች።+
12 ከዚህም የተነሳ እንደሞተ ያህል ከሚቆጠረው+ ከአንድ ሰው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዙና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የማይቆጠሩ ልጆች ተወለዱ።+
13 እነዚህ ሁሉ የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ባያዩም እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ፤+ ሆኖም ከሩቅ አይተው በደስታ ተቀበሉት፤+ በምድሩም ላይ እንግዶችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች መሆናቸውን በይፋ ተናገሩ።
14 እንዲህ ብለው የሚናገሩት ሰዎች የራሳቸው የሆነ ቦታ ለማግኘት ከልብ እንደሚሹ ያሳያሉ።
15 ይሁንና ትተውት የወጡትን ቦታ ሁልጊዜ ቢያስቡ ኖሮ+ መመለስ የሚችሉበት አጋጣሚ በኖራቸው ነበር።
16 አሁን ግን የተሻለውን ይኸውም ከሰማይ የሆነውን ስፍራ ለማግኘት ይጣጣራሉ። ስለዚህ አምላክ፣ እሱን አምላካችን ብለው ቢጠሩት አያፍርባቸውም፤+ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።+
17 አብርሃም በተፈተነ ጊዜ+ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ድረስ እምነት አሳይቷል፤ የተስፋን ቃል በደስታ የተቀበለው ይህ ሰው አንድያ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ተዘጋጅቶ ነበር፤+
18 ይህን ያደረገው “ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ይሆናል” ተብሎ ተነግሮት እያለ ነው።+
19 ይሁንና አምላክ ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር፤ ልጁንም ከሞት አፋፍ መልሶ አገኘው፤ ይህም እንደ ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል።+
20 ይስሐቅም ወደፊት ከሚሆኑት ነገሮች ጋር በተያያዘ ያዕቆብንና+ ኤሳውን+ በእምነት ባረካቸው።
21 ያዕቆብ መሞቻው በተቃረበ ጊዜ+ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን የባረካቸውና+ የበትሩን ጫፍ ተመርኩዞ ለአምላክ የሰገደው በእምነት ነበር።+
22 ዮሴፍ ሊሞት በተቃረበ ጊዜ ስለ እስራኤል ልጆች ከግብፅ መውጣት* በእምነት ተናገረ፤ ስለ አፅሙም* መመሪያ* ሰጣቸው።+
23 ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ መልኩ የሚያምር ሕፃን+ መሆኑን ስላዩ የንጉሡን ትእዛዝ ሳይፈሩ+ ለሦስት ወር የሸሸጉት+ በእምነት ነበር።
24 ሙሴ ካደገ በኋላ+ የፈርዖን የልጅ ልጅ* ተብሎ ለመጠራት በእምነት እንቢ አለ፤+
25 በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን መረጠ፤
26 ምክንያቱም ቅቡዕ* ሆኖ የሚደርስበት ነቀፋ በግብፅ ከሚገኝ ውድ ሀብት የላቀ እንደሆነ አስቧል፤ የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት ተመልክቷልና።
27 ደግሞም በእምነት ግብፅን ለቆ ወጣ፤+ ሆኖም ይህን ያደረገው የንጉሡን ቁጣ ፈርቶ አይደለም፤+ የማይታየውን አምላክ+ እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏልና።
28 አጥፊው የበኩር ልጆቻቸውን እንዳይገድል* ሙሴ ፋሲካን* ያከበረውና መቃኖቹ ላይ ደም የረጨው በእምነት ነው።+
29 እስራኤላውያን በደረቅ ምድር የሚሄዱ ያህል ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ፤+ ይሁንና ግብፃውያን እንዲህ ለማድረግ በሞከሩ ጊዜ ሰመጡ።+
30 እስራኤላውያን የኢያሪኮን ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ በእምነት ወደቀ።+
31 ዝሙት አዳሪዋ ረዓብ ታዛዥ ሳይሆኑ ከቀሩት ሰዎች ጋር ከመጥፋት የዳነችው በእምነት ነው፤ ምክንያቱም ሰላዮቹን በሰላም ተቀብላለች።+
32 እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን እላለሁ? ስለ ጌድዮን፣+ ስለ ባርቅ፣+ ስለ ሳምሶን፣+ ስለ ዮፍታሔ፣+ ስለ ዳዊት+ እንዲሁም ስለ ሳሙኤልና+ ስለ ሌሎቹ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል።
33 እነዚህ ሰዎች በእምነት መንግሥታትን ድል አድርገዋል፤+ ጽድቅን አስፍነዋል፤ የተስፋን ቃል ተቀብለዋል፤+ የአንበሶችን አፍ ዘግተዋል፤+
34 የእሳትን ኃይል አጥፍተዋል፤+ ከሰይፍ ስለት አምልጠዋል፤+ ደካማ የነበሩት ብርታት አግኝተዋል፤+ በጦርነት ኃያላን ሆነዋል፤+ ወራሪ ሠራዊትን አባረዋል።+
35 ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀብለዋል፤+ ሌሎች ወንዶች ግን ቤዛ ተከፍሎላቸው ነፃ መሆን ስላልፈለጉ ከባድ ሥቃይ ደርሶባቸዋል፤ ይህን ያደረጉት የተሻለ ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ ነው።
36 አዎ፣ ሌሎች ደግሞ መዘባበቻ በመሆንና በመገረፍ ይባስ ብሎም በመታሰርና ወህኒ ቤት በመጣል+ ፈተና ደርሶባቸዋል።
37 በድንጋይ ተወግረዋል፤+ ተፈትነዋል፤ በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቀዋል፤ በሰይፍ ተቀልተዋል፤+ እየተቸገሩ፣ መከራ እየተቀበሉና+ እየተንገላቱ+ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ተንከራተዋል፤+
38 ዓለም እንዲህ ዓይነት ሰዎች የሚገቡት ሆኖ አልተገኘም። በየበረሃው፣ በየተራራው፣ በየዋሻውና+ በምድር ውስጥ ባሉ ጉድጓዶች ተቅበዝብዘዋል።
39 ይሁንና እነዚህ ሁሉ በእምነታቸው ምክንያት በመልካም የተመሠከረላቸው ቢሆኑም እንኳ የተስፋውን ቃል ፍጻሜ አላዩም፤
40 ምክንያቱም አምላክ ያለእኛ ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ዓላማው ስላልነበረ ለእኛ የተሻለ ነገር ለመስጠት አስቀድሞ አስቧል።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “አባቶቻችን።”
^ ወይም “ዘመናቱ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “በመቀበል ምሥክርነት ስለሰጠ።”
^ ወይም “እምነት የሚጣልበት።”
^ ወይም “ትእዛዝ።”
^ ወይም “ስለ ቀብሩም።”
^ እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል ለዘፀአት መጽሐፍ ከተሰጠው ግሪክኛ ስያሜ ጋር ተዛማጅነት አለው።
^ ወይም “የፈርዖን ሴት ልጅ፣ ልጅ።”
^ በግሪክኛ “ክርስቶስ።”
^ ወይም “የማለፍ በዓልን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “እንዳይነካ።”