ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 6:1-20
6 ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት አልፈን ስለሄድን+ ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር፤+ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፤ ይኸውም ከሞቱ ሥራዎች ንስሐ ስለ መግባት፣ በአምላክ ስለ ማመን፣
2 እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣+ ስለ ሙታን ትንሣኤና+ ስለ ዘላለማዊ ፍርድ የሚገልጹ ትምህርቶችን ደግመን አንማር።
3 አምላክ ከፈቀደ ይህን እናደርጋለን።
4 ቀደም ሲል ብርሃን በርቶላቸው የነበሩትን፣+ ሰማያዊውን ነፃ ስጦታ የቀመሱትን፣ መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን፣
5 መልካም የሆነውን የአምላክ ቃልና በሚመጣው ሥርዓት* የሚገኙትን በረከቶች* የቀመሱትን፣
6 በኋላ ግን ከእምነት ጎዳና የራቁትን+ እንደገና ወደ ንስሐ መመለስ አይቻልም፤ ምክንያቱም የአምላክን ልጅ ለራሳቸው እንደገና በእንጨት ላይ ይቸነክሩታል፤ እንዲሁም በአደባባይ ያዋርዱታል።+
7 በየጊዜው በላዩ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የሚጠጣና ለአራሾቹ መብል የሚሆን አትክልት የሚያፈራ መሬት ከአምላክ በረከትን ያገኛልና።
8 እሾህና አሜኬላ የሚያበቅል ከሆነ ግን የተተወና ለመረገም የተቃረበ ይሆናል፤ በመጨረሻም በእሳት ይቃጠላል።
9 ይሁን እንጂ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ምንም እንኳ እንደዚህ ብለን ብንናገርም እናንተ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይኸውም ወደ መዳን በሚያደርስ ሁኔታ ላይ እንደምትገኙ እርግጠኞች ነን።
10 አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም* ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር+ በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።
11 ይሁንና ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነውን ተስፋ+ እስከ መጨረሻው መያዝ እንድትችሉ+ እያንዳንዳችሁ ያንኑ ትጋት እንድታሳዩ እንመኛለን፤
12 ይህም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ነው።+
13 አምላክ ለአብርሃም ቃል በገባለት ጊዜ ሊምልበት የሚችል ከእሱ የሚበልጥ ሌላ ማንም ስለሌለ በራሱ ስም ማለ፤+
14 እንዲህም አለ፦ “በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም በእርግጥ አበዛዋለሁ።”+
15 በመሆኑም አብርሃም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ ይህን የተስፋ ቃል አገኘ።
16 ሰዎች ከእነሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላቸውም እንደ ሕጋዊ ዋስትና ስለሆነ ማንኛውም ሙግት በመሐላው ይቋጫል።+
17 በተመሳሳይም አምላክ ዓላማው ፈጽሞ የማይለወጥ መሆኑን ለተስፋው ቃል ወራሾች+ ይበልጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ለማሳየት በወሰነ ጊዜ የተስፋውን ቃል በመሐላ አረጋገጠ።
18 ይህን ያደረገው መጠጊያ ለማግኘት ወደ እሱ የሸሸን እኛ፣ አምላክ ሊዋሽ በማይችልባቸው፣+ ፈጽሞ በማይለወጡት በእነዚህ ሁለት ነገሮች አማካኝነት በፊታችን ያለውን ተስፋ አጥብቀን እንድንይዝ የሚረዳንን ከፍተኛ ማበረታቻ እንድናገኝ ነው።
19 እኛ ለነፍሳችን* እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን፤+ ተስፋውም መጋረጃውን አልፎ ወደ ውስጥ ይገባል፤+
20 ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ለዘላለም ሊቀ ካህናት+ የሆነው ኢየሱስ+ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ስለ እኛ ወደዚያ ገብቷል።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በሚመጣው ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “ኃይሎች።”
^ ወይም “በመርዳትም።”
^ ወይም “እኛ ለሕይወታችን።”