ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 9:1-28

  • በምድራዊው መቅደስ ይቀርብ የነበረው ቅዱስ አገልግሎት (1-10)

  • ክርስቶስ ደሙን ይዞ ወደ ሰማይ ገባ (11-28)

    • “የአዲስ ቃል ኪዳን መካከለኛ” (15)

9  የቀድሞው ቃል ኪዳን በበኩሉ ቅዱስ አገልግሎት የሚከናወንባቸው ደንቦችና በምድር ላይ የራሱ ቅዱስ ስፍራ+ ነበረው። 2  መቅረዙ፣+ ጠረጴዛውና በአምላክ ፊት የቀረበው ኅብስት+ የሚገኙበት የድንኳኑ የመጀመሪያው ክፍል ተሠርቶ ነበር፤ ይህም ቅድስት ይባላል።+ 3  ከሁለተኛው መጋረጃ+ በስተ ኋላ ግን ቅድስተ ቅዱሳን የሚባለው የድንኳኑ ክፍል ይገኝ ነበር።+ 4  በዚህ ክፍል ውስጥ የወርቅ ጥና+ እና ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠው+ የቃል ኪዳኑ ታቦት+ ይገኙ ነበር፤ በታቦቱ ውስጥም መና የያዘው የወርቅ ማሰሮ፣+ ያቆጠቆጠችው የአሮን በትርና+ የቃል ኪዳኑ ጽላቶች+ ነበሩ፤ 5  በላዩ ላይ ደግሞ የስርየት መክደኛውን* የሚጋርዱ ክብራማ ኪሩቦች ነበሩ።+ ይሁንና ስለ እነዚህ ነገሮች በዝርዝር ለመናገር አሁን ጊዜው አይደለም። 6  እነዚህ ነገሮች በዚህ መንገድ ከተሠሩ በኋላ ካህናቱ ቅዱስ አገልግሎቶችን ለማከናወን ወደ ድንኳኑ የመጀመሪያ ክፍል ሁልጊዜ ይገባሉ፤+ 7  ወደ ሁለተኛው ክፍል የሚገባው ግን ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤+ ደግሞም ለራሱና+ ሕዝቡ+ ባለማወቅ ለፈጸመው ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም።+ 8  በዚህ መንገድ፣ የመጀመሪያው ድንኳን* ተተክሎ ሳለ ወደ ቅዱሱ ስፍራ* የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ግልጽ አድርጓል።+ 9  ይህ ድንኳን ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ+ ሲሆን ከዚህ ዝግጅት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ስጦታዎችና መሥዋዕቶች ይቀርባሉ።+ ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርበው ሰው ፍጹም በሆነ መንገድ ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው ሊያደርጉ አይችሉም።+ 10  እነዚህ ነገሮች ከምግብ፣ ከመጠጥና ከተለያዩ የመንጻት ሥርዓቶች* ጋር ብቻ የተያያዙ ናቸው።+ ደግሞም አካልን የሚመለከቱ ደንቦች+ ሲሆኑ በሥራ ላይ የዋሉትም፣ ሁኔታዎች የሚስተካከሉበት የተወሰነው ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ነበር። 11  ይሁን እንጂ ክርስቶስ አሁን ላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው እጅ ወዳልተሠራው ይኸውም ከዚህ ፍጥረት ወዳልሆነው ይበልጥ ታላቅና ፍጹም ወደሆነው ድንኳን ገብቷል። 12  ወደ ቅዱሱ ስፍራ የገባው የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ራሱን ደም ይዞ+ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ፤ ደግሞም ለእኛ ዘላለማዊ መዳን* አስገኘልን።+ 13  የፍየሎችና የኮርማዎች ደም+ እንዲሁም በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ ሥጋን በማንጻት የሚቀድስ ከሆነ+ 14  በዘላለማዊ መንፈስ አማካኝነት ራሱን ያላንዳች እንከን ለአምላክ ያቀረበው የክርስቶስ ደም+ ሕያው ለሆነው አምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንድናቀርብ+ ሕሊናችንን ከሞቱ ሥራዎች እንዴት አብልጦ አያነጻም?+ 15  የአዲስ ቃል ኪዳን መካከለኛ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው።+ መካከለኛ የሆነውም የተጠሩት የዘላለማዊውን ውርሻ+ ተስፋ ይቀበሉ ዘንድ ነው። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በሞቱ የተነሳ ሲሆን በእሱ ሞት አማካኝነት በቀድሞው ቃል ኪዳን ሥር ሆነው ሕግ በመተላለፍ ከፈጸሟቸው ድርጊቶች በቤዛ ነፃ ወጥተዋል።+ 16  ቃል ኪዳን ሲኖር ቃል ኪዳኑን የፈጸመው ሰው* መሞቱ መረጋገጥ አለበት፤ 17  ምክንያቱም ቃል ኪዳኑን የፈጸመው ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ቃል ኪዳኑ መቼም ተፈጻሚ ሊሆን ስለማይችል ቃል ኪዳን የሚጸናው ሞትን መሠረት በማድረግ ነው። 18  ከዚህም የተነሳ የቀድሞው ቃል ኪዳንም ያለደም ሥራ ላይ መዋል አልጀመረም።* 19  ሙሴ በሕጉ ላይ የሰፈረውን እያንዳንዱን ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ የወይፈኖችንና የፍየሎችን ደም ከውኃ፣ ከቀይ ሱፍና ከሂሶጵ ጋር ወስዶ መጽሐፉንና* ሕዝቡን ሁሉ ረጭቷል፤ 20  የረጨውም “አምላክ እንድትጠብቁት ያዘዛችሁ የቃል ኪዳኑ ደም ይህ ነው” ብሎ ነው።+ 21  በተመሳሳይም በድንኳኑና ቅዱስ አገልግሎት* በሚቀርብባቸው ዕቃዎች ሁሉ ላይ ደም ረጭቷል።+ 22  አዎ፣ በሕጉ መሠረት ሁሉም ነገር ማለት ይቻላል በደም ይነጻል፤+ ደም ካልፈሰሰ በስተቀር ይቅርታ ማግኘት አይቻልም።+ 23  ስለዚህ በሰማያት ላሉት ነገሮች ዓይነተኛ አምሳያ+ የሆኑት ሁሉ በዚህ መንገድ መንጻታቸው+ የግድ አስፈላጊ ነበር፤ በሰማያት ያሉት ነገሮች ግን የተሻሉ መሥዋዕቶች ያስፈልጓቸዋል። 24  ክርስቶስ የገባው በሰው እጅ ወደተሠራውና የእውነተኛው ቅዱስ ስፍራ አምሳያ+ ወደሆነው ስፍራ አይደለምና፤+ ከዚህ ይልቅ አሁን ስለ እኛ በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ+ ወደ ሰማይ ገብቷል።+ 25  የገባው ግን ሊቀ ካህናቱ የራሱን ሳይሆን የእንስሳ ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ይገባ እንደነበረው ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አይደለም።+ 26  አለዚያማ ዓለም ከተመሠረተ* ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ኃጢአትን ለማስወገድ በሥርዓቶቹ* መደምደሚያ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ራሱን ገልጧል።+ 27  ሰው ሁሉ አንድ ጊዜ መሞቱ አይቀርም፤ ከዚያ በኋላ ግን ፍርድ ይቀበላል፤ 28  በተመሳሳይም ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ለመሸከም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ ቀርቧል፤+ ለሁለተኛ ጊዜ የሚገለጠውም ኃጢአትን ለማስወገድ አይደለም፤ መዳን ለማግኘት እሱን በጉጉት የሚጠባበቁትም ያዩታል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የስርየት ስፍራውን።”
በምድር ላይ የነበረውን ድንኳን ያመለክታል።
በሰማይ የሚገኘውን ቅዱስ ስፍራ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ቃል በቃል “ከተለያዩ ጥምቀቶች።”
ቃል በቃል “ቤዛነት።”
ወይም “ቃል ኪዳን የሚያጋባው ወገን።”
ቃል በቃል “አልተመረቀም።”
ወይም “ጥቅልሉንና።”
ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት።”
ይህ አባባል የአዳምንና የሔዋንን ዘሮች ያመለክታል።
ወይም “በዘመናቱ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።