ዘኁልቁ 11:1-35

  • ከይሖዋ የመጣ እሳት ባጉረመረሙት ሰዎች ላይ ነደደ (1-3)

  • የምንበላው ሥጋ አጣን ብለው አለቀሱ (4-9)

  • ሙሴ የእስራኤል ሕዝብ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ተሰማው (10-15)

  • ይሖዋ መንፈሱን ለ70ዎቹ ሽማግሌዎች ሰጠ (16-25)

  • ኤልዳድና ሞዳድ፤ ኢያሱ ለሙሴ ተቆረቆረ (26-30)

  • ድርጭቶች በሰፈሩ ዙሪያ ተበተኑ፤ ሕዝቡ በመስገብገቡ ተቀጣ (31-35)

11  በዚህ ጊዜ ሕዝቡ፣ ስለደረሰበት ችግር በይሖዋ ፊት ክፉኛ ማጉረምረም ጀመረ። ይሖዋ ይህን ሲሰማ ቁጣው ነደደ፤ ከይሖዋም የመጣ እሳት በእነሱ ላይ ተቀጣጠለ፤ በሰፈሩ ዳርቻ ያሉትን የተወሰኑ ሰዎችም በላ። 2  ሕዝቡ ወደ ሙሴ መጮኽ ሲጀምር ሙሴ ይሖዋን ተማጸነ፤+ እሳቱም ከሰመ። 3  ከይሖዋ የመጣ እሳት በእነሱ ላይ ስለነደደም የዚያ ቦታ ስም ታበራ* ተባለ።+ 4  እስራኤላውያንም በመካከላቸው የነበረው ድብልቅ ሕዝብ*+ ሲስገበገብ+ ሲያዩ እንዲህ በማለት እንደገና ያለቅሱ ጀመር፦ “እንግዲህ አሁን የምንበላው ሥጋ ማን ይሰጠናል?+ 5  በግብፅ እያለን በነፃ እንበላው የነበረው ዓሣ እንዲሁም ኪያሩ፣ ሐብሐቡ፣ ባሮ ሽንኩርቱ፣ ቀይ ሽንኩርቱና ነጭ ሽንኩርቱ በዓይናችን ላይ ዞሯል!+ 6  አሁን ግን ዝለናል።* ከዚህ መና በስተቀር ሌላ የምናየው ነገር የለም።”+ 7  መናው+ እንደ ድንብላል ዘር+ ነበር፤ መልኩም ሙጫ* ይመስል ነበር። 8  ሕዝቡም ሜዳ ላይ ወጥቶ መናውን ከለቀመ በኋላ በወፍጮ ይፈጨው ወይም በሙቀጫ ይወቅጠው ነበር። ከዚያም በድስት ይቀቅሉት ወይም እንደ ቂጣ ይጋግሩት ነበር፤+ ጣዕሙም በዘይት ተለውሶ እንደተጋገረ ጣፋጭ ቂጣ ነበር። 9  ሌሊት በሰፈሩ ላይ ጤዛ በሚወርድበት ጊዜ መናውም በላዩ ላይ ይወርድ ነበር።+ 10  ሙሴም ሕዝቡ ይኸውም እያንዳንዱ ሰው በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ሆኖ ከቤተሰቡ ጋር ሲያለቅስ ሰማ። ይሖዋም እጅግ ተቆጣ፤+ ሙሴም በጣም አዘነ። 11  ከዚያም ሙሴ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “አገልጋይህን የምታጎሳቁለው ለምንድን ነው? በፊትህ ሞገስ ያጣሁትና የዚህን ሁሉ ሕዝብ ሸክም በእኔ ላይ የጫንከው ለምንድን ነው?+ 12  ይህን ሁሉ ሕዝብ የፀነስኩት እኔ ነኝ? ለአባቶቻቸው ለመስጠት ቃል ወደገባህላቸው ምድር እንዳስገባቸው ‘የሚጠባን ሕፃን እንደሚታቀፍ ሞግዚት በጉያህ እቀፋቸው’ የምትለኝ የወለድኳቸው እኔ ነኝ?+ 13  ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ሥጋ ከየት ነው የማመጣው? ይኸው እነሱ ‘የምንበላው ሥጋ ስጠን!’ በማለት እያለቀሱብኝ ነው። 14  ይህን ሁሉ ሕዝብ እኔ ብቻዬን ልሸከመው አልችልም፤ ከአቅሜ በላይ ነው።+ 15  እንዲህስ ከምታደርገኝ እባክህ አሁኑኑ ግደለኝ።+ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ ከእንግዲህ መከራ እንዳይ አታድርገኝ።” 16  ይሖዋም መልሶ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከእስራኤል ሽማግሌዎች መካከል የሕዝቡ ሽማግሌዎችና አለቆች+ የመሆን ብቃት አላቸው የምትላቸውን 70 ሰዎች ሰብስብልኝ፤ እነሱንም ወደ መገናኛ ድንኳኑ ውሰዳቸውና በዚያ ከአንተ ጋር ይቁሙ። 17  እኔም ወርጄ+ በዚያ ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፤+ በአንተ ላይ ካለው መንፈስ+ ወስጄ በእነሱ ላይ አደርጋለሁ፤ እነሱም የሕዝቡን ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም ይረዱሃል።+ 18  ሕዝቡንም እንዲህ በለው፦ ‘ሥጋ ስለምትበሉ ለነገ ራሳችሁን ቀድሱ፤+ ምክንያቱም በይሖዋ ፊት አልቅሳችኋል፤+ ደግሞም “የምንበላው ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ የነበርንበት ሁኔታ የተሻለ ነበር”+ ብላችኋል። ይሖዋ በእርግጥ ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ትበላላችሁ።+ 19  የምትበሉትም ለአንድ ቀን ወይም ለ2 ቀን ወይም ለ5 ቀን ወይም ለ10 ቀን ወይም ለ20 ቀን አይደለም፤ 20  ከዚህ ይልቅ በአፍንጫችሁ እስኪወጣና እስኪያንገፈግፋችሁ+ ድረስ ወር ሙሉ ትበላላችሁ፤ ምክንያቱም በመካከላችሁ ያለውን ይሖዋን ትታችኋል፤ እንዲሁም “ከግብፅ የወጣነው ለምንድን ነው?” በማለት በፊቱ አልቅሳችኋል።’”+ 21  ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እኔ በመካከሉ የምገኘው ሕዝብ 600,000 እግረኛ ወንዶች+ ያሉበት ነው፤ አንተ ደግሞ ‘ሥጋ እሰጣቸዋለሁ፤ ወር ሙሉ እስኪጠግቡ ይበላሉ’ ትላለህ። 22  በጎቹና ከብቶቹ ሁሉ ቢታረዱ እንኳ ይበቃቸዋል? የባሕር ዓሣዎች ሁሉ ቢያዙስ ሊበቃቸው ይችላል?” 23  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ለመሆኑ የይሖዋ እጅ አጭር ነው?+ እንግዲህ ያልኩት ነገር ይፈጸምልህ እንደሆነና እንዳልሆነ ታያለህ” አለው። 24  ሙሴም ወጥቶ የይሖዋን ቃል ለሕዝቡ ተናገረ። እንዲሁም ከሕዝቡ ሽማግሌዎች መካከል 70 ሰዎችን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረገ።+ 25  ከዚያም ይሖዋ በደመና ወርዶ+ አነጋገረው፤+ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ+ ወስዶ በ70ዎቹ ሽማግሌዎች ላይ አደረገ። እነሱም ወዲያው መንፈሱ እንዳረፈባቸው እንደ ነቢያት አደረጋቸው፤*+ ሆኖም ዳግመኛ እንደዚያ አልሆኑም። 26  በዚህ ጊዜ ከሰዎቹ መካከል ሁለቱ በሰፈሩ ውስጥ ቀርተው ነበር። ስማቸውም ኤልዳድና ሞዳድ ነበር። እነዚህ ሰዎች ምንም እንኳ ወደ ድንኳኑ ባይሄዱም ስማቸው ከተመዘገቡት ሰዎች መካከል ስለነበሩ መንፈሱ በእነሱም ላይ ወረደ። በመሆኑም እነሱም በሰፈሩ ውስጥ እንደ ነቢያት ሆኑ። 27  አንድ ወጣትም እየሮጠ በመሄድ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈሩ ውስጥ እንደ ነቢያት እየሆኑ ነው!” ሲል ለሙሴ ነገረው። 28  በዚህ ጊዜ ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ+ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፣ እነዚህን ሰዎች ከልክላቸው እንጂ!”+ ሲል ተናገረ። 29  ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “ስለ እኔ ተቆርቁረህ ነው? አትቆርቆር፤ የይሖዋ ሕዝቦች በሙሉ ነቢያት ቢሆኑና ይሖዋ መንፈሱን ቢሰጣቸው እንዴት ደስ ባለኝ!” 30  በኋላም ሙሴ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈሩ ተመለሰ። 31  ከዚያም ነፋስ ከይሖዋ ዘንድ ወጥቶ ድርጭቶችን ከባሕሩ እየነዳ በማምጣት በሰፈሩ ዙሪያ በተናቸው፤+ ድርጭቶቹም የአንድ ቀን መንገድ ያህል በአንድ በኩል፣ የአንድ ቀን መንገድ ያህል ደግሞ በሌላ በኩል በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ተበትነው ነበር፤ መሬት ላይም ሁለት ክንድ* ከፍታ ያህል ተቆልለው ነበር። 32  ሕዝቡም በዚያን ዕለት ቀኑን ሙሉና ሌሊቱን ሙሉ እንዲሁም በማግስቱ ቀኑን ሙሉ ድርጭቶቹን ሲሰበስብ ዋለ። ከአሥር ሆሜር* ያነሰ የሰበሰበ አልነበረም፤ የሰበሰቧቸውንም በሰፈሩ ዙሪያ አሰጧቸው። 33  ሆኖም ሥጋውን ገና ሳያኝኩት፣ በጥርሳቸው መካከል እያለ የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ ይሖዋም ሕዝቡን ክፉኛ ፈጀ።+ 34  እነሱም ሲስገበገቡ+ የነበሩትን ሰዎች በዚያ ስለቀበሯቸው የቦታውን ስም ቂብሮትሃታባ*+ አሉት። 35  ሕዝቡም ከቂብሮትሃታባ ተነስቶ ወደ ሃጼሮት+ ተጓዘ፤ በሃጼሮትም ተቀመጠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“የሚነድ” የሚል ትርጉም አለው። የሚንቀለቀል፤ የሚንቦገቦግ መሆኑን ያመለክታል።
በመካከላቸው ያሉትን እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች የሚያመለክት ይመስላል።
ወይም “ነፍሳችን ዝሏል።”
ዘፍ 2:12 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “ትንቢት መናገር ጀመሩ።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ሆሜር 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
“የመጎምጀት የመቃብር ስፍራ” የሚል ትርጉም አለው።