ዘኁልቁ 8:1-26

  • አሮን ሰባቱን መብራቶች ለኮሰ (1-4)

  • ሌዋውያኑ ነጽተው ማገልገል ጀመሩ (5-22)

  • ሌዋውያን የሚያገለግሉበት የዕድሜ ገደብ (23-26)

8  ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2  “ለአሮን ‘መብራቶቹን በምታበራበት ጊዜ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ለፊት ላለው አካባቢ ብርሃን መስጠት ይኖርባቸዋል’ ብለህ ንገረው።”+ 3  አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመቅረዙ+ ፊት ለፊት ያለው አካባቢ ብርሃን እንዲያገኝ የመቅረዙን መብራቶች ለኮሳቸው። 4  የመቅረዙ አሠራር ይህ ነበር፦ አንድ ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፎ የተሠራ ነበር፤ ግንዱም ሆነ የፈኩት አበቦቹ ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፈው የተሠሩ ነበሩ።+ መቅረዙ የተሠራው ይሖዋ ለሙሴ ባሳየው ራእይ መሠረት ነበር።+ 5  ይሖዋ ሙሴን ዳግመኛ እንዲህ አለው፦ 6  “ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ወስደህ አንጻቸው።+ 7  እነሱንም የምታነጻቸው በሚከተለው መንገድ ነው፦ ከኃጢአት የሚያነጻ ውኃ እርጫቸው፤ እነሱም ሰውነታቸውን በሙሉ በምላጭ ይላጩ፤ እንዲሁም ልብሳቸውን ይጠቡ፤ ራሳቸውንም ያንጹ።+ 8  ከዚያም አንድ ወይፈንና+ አብሮት የሚቀርበውን በዘይት ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተዘጋጀ የእህል መባ+ ይወስዳሉ፤ አንተም ለኃጢአት መባ+ እንዲሆን ሌላ ወይፈን ትወስዳለህ። 9  እንዲሁም ሌዋውያኑን በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ታቀርባቸዋለህ፤ መላውን የእስራኤል ማኅበረሰብ ትሰበስባለህ።+ 10  ሌዋውያኑን በይሖዋ ፊት በምታቀርባቸው ጊዜ እስራኤላውያን በሌዋውያኑ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ።+ 11  አሮንም ከእስራኤላውያን መካከል ሌዋውያኑን እንደሚወዘወዝ መባ+ አድርጎ በይሖዋ ፊት ያቅርባቸው፤* እነሱም ለይሖዋ የሚቀርበውን አገልግሎት ያከናውናሉ።+ 12  “ከዚያም ሌዋውያኑ በወይፈኖቹ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ።+ ይህን ካደረጉ በኋላ ለእነሱ ማስተሰረያ እንዲሆኑ+ አንደኛውን ወይፈን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርገው ለይሖዋ ያቀርባሉ። 13  ሌዋውያኑንም በአሮንና በወንዶች ልጆቹ ፊት እንዲቆሙ ካደረግክ በኋላ እንደሚወዘወዝ መባ አድርገህ ለይሖዋ አቅርባቸው።* 14  ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ለያቸው፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሆናሉ።+ 15  ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በመገናኛ ድንኳኑ ለማገልገል ይመጣሉ። እነሱን የምታነጻቸውና እንደሚወዘወዝ መባ አድርገህ የምታቀርባቸው* በዚህ መንገድ ነው። 16  ምክንያቱም እነሱ የተሰጡ ይኸውም ከእስራኤላውያን መካከል ለእኔ የተሰጡ ናቸው። በእስራኤላውያን በኩሮች ሁሉ* ምትክ+ እነሱን ለራሴ እወስዳቸዋለሁ። 17  ምክንያቱም ሰውም ሆነ እንስሳ ከእስራኤላውያን መካከል በኩር የሆነ ሁሉ የእኔ ነው።+ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ በመታሁበት ቀን እነሱን ለራሴ ቀድሻቸዋለሁ።+ 18  ሌዋውያኑን በእስራኤላውያን በኩር ሁሉ ምትክ እወስዳቸዋለሁ። 19  የእስራኤል ሕዝብ ወደ ቅዱሱ ስፍራ በመቅረቡ የተነሳ በመካከሉ መቅሰፍት እንዳይከሰት+ በእስራኤላውያን ምትክ በመገናኛ ድንኳኑ ያገለግሉና+ ለእነሱ ያስተሰርዩ ዘንድ ከእስራኤላውያን መካከል ሌዋውያኑን ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የተሰጡ አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።” 20  ሙሴ፣ አሮንና መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ ለሌዋውያኑ እንዲሁ አደረጉ። እስራኤላውያንም ይሖዋ ሌዋውያኑን አስመልክቶ ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። 21  በመሆኑም ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሶቻቸውንም አጠቡ፤+ በመቀጠልም አሮን እንደሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት አቀረባቸው።*+ ከዚያም አሮን እነሱን ለማንጻት ማስተሰረያ አቀረበላቸው።+ 22  ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ሌዋውያኑ በመገናኛ ድንኳኑ በአሮንና በወንዶች ልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ገቡ። ይሖዋ ሌዋውያኑን በተመለከተ ሙሴን ባዘዘው መሠረት እንዲሁ አደረጉላቸው። 23  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 24  “ሌዋውያኑን በተመለከተ የተደረገው ዝግጅት የሚከተለው ነው፦ አንድ ወንድ ዕድሜው 25 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆነ በመገናኛ ድንኳኑ ከሚያገለግለው ቡድን ጋር ይቀላቀላል። 25  ዕድሜው 50 ዓመት ከሞላ ግን ከሚያገለግልበት ቡድን ጡረታ ይወጣል፤ ከዚያ በኋላ ማገልገል አይጠበቅበትም። 26  ይህ ሰው በመገናኛ ድንኳኑ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉትን ወንድሞቹን ሊያገለግል ይችላል፤ ሆኖም በዚያ ማገልገል የለበትም። ሌዋውያኑንና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተመለከተ ማድረግ ያለብህ ይህን ነው።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ይወዝውዛቸው።”
ቃል በቃል “ወዝውዛቸው።”
ቃል በቃል “የምትወዘውዛቸው።”
ወይም “ማህፀን በሚከፍተው በኩር ሁሉ።”
ቃል በቃል “ወዘወዛቸው።”