ዘኁልቁ 9:1-23
9 ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር+ ይሖዋ ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ በማለት አነጋገረው፦
2 “እስራኤላውያን የፋሲካን* መሥዋዕት+ በተወሰነለት ጊዜ ያዘጋጁ።+
3 በዚህ ወር በ14ኛው ቀን አመሻሹ ላይ* በተወሰነለት ጊዜ አዘጋጁት። ደንቦቹን ሁሉና ሥርዓቱን ሁሉ ተከትላችሁ አዘጋጁት።”+
4 በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያን የፋሲካን መሥዋዕት እንዲያዘጋጁ ነገራቸው።
5 እነሱም በመጀመሪያው ወር ከወሩም በ14ኛው ቀን አመሻሹ ላይ* የፋሲካን መሥዋዕት በሲና ምድረ በዳ አዘጋጁ። እስራኤላውያንም ሁሉንም ነገር ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት አደረጉ።
6 የሞተ ሰው ነክተው* በመርከሳቸው+ የተነሳ በዚያ ቀን የፋሲካን መሥዋዕት ማዘጋጀት ያልቻሉ ሰዎች ነበሩ። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በዚያ ቀን ሙሴና አሮን ፊት ቀረቡ፤+
7 እንዲህም አሉት፦ “እኛ የሞተ ሰው በመንካታችን* የተነሳ ረክሰናል። ይሁንና ከእስራኤላውያን ጋር መባውን በተወሰነለት ጊዜ ለይሖዋ እንዳናቀርብ የምንከለከለው ለምንድን ነው?”+
8 በዚህ ጊዜ ሙሴ “ይሖዋ እናንተን በተመለከተ የሚሰጠውን ትእዛዝ እስክሰማ ድረስ እዚያ ጠብቁ”+ አላቸው።
9 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦
10 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘ከእናንተ ወይም ከመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ መካከል ማንኛውም ሰው የሞተ ሰው በመንካቱ* ቢረክስ+ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ ለይሖዋ የፋሲካን መሥዋዕት ማዘጋጀት ይጠበቅበታል።
11 እነሱም በሁለተኛው ወር+ በ14ኛው ቀን አመሻሹ ላይ* ያዘጋጁት። ይህንም ከቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት።+
12 ከእሱም ላይ እስከ ጠዋት ድረስ ምንም ማስተረፍ+ ወይም ከአጥንቱ ውስጥ አንዱንም መስበር+ የለባቸውም። ፋሲካን በተመለከተ የወጣውን ደንብ ሁሉ ተከትለው ያዘጋጁት።
13 ይሁንና አንድ ሰው ንጹሕ ሆኖ ሳለ ወይም ሩቅ መንገድ ሳይሄድ በቸልተኝነት የፋሲካን መሥዋዕት ሳያዘጋጅ ቢቀር፣ ያ ሰው* የይሖዋን መባ በተወሰነለት ጊዜ ስላላቀረበ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።+ ይህ ሰው ለሠራው ኃጢአት ይጠየቅበታል።
14 “‘በመካከላችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ካለ እሱም ለይሖዋ የፋሲካን መሥዋዕት ማዘጋጀት አለበት።+ ይህን በፋሲካው ደንብና በወጣለት ሥርዓት መሠረት ማድረግ አለበት።+ ለሁላችሁም ማለትም ለባዕድ አገሩም ሰው ሆነ ለአገሬው ተወላጅ አንድ ዓይነት ደንብ ይኑር።’”+
15 የማደሪያ ድንኳኑ በተተከለበት ቀን+ ደመናው የማደሪያ ድንኳኑን ይኸውም የምሥክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ሆኖም ከምሽት ጀምሮ እስከ ጠዋት ድረስ በማደሪያ ድንኳኑ ላይ እሳት የሚመስል ነገር ታየ።+
16 ሁልጊዜም እንዲህ ይሆን ነበር፦ ቀን ቀን ደመናው ድንኳኑን ይሸፍነው ነበር፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ እሳት የሚመስል ነገር ይታይ ነበር።+
17 ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሳበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ወዲያውኑ ተነስተው ይጓዙ ነበር፤+ ደመናው በሚቆምበት ቦታ ደግሞ እስራኤላውያን ይሰፍሩ ነበር።+
18 እስራኤላውያን ተነስተው የሚጓዙት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር፤ የሚሰፍሩትም በይሖዋ ትእዛዝ ነበር።+ ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ በሚቆይባቸው ቀናት ሁሉ እነሱም በሰፈሩበት ቦታ ይቆዩ ነበር።
19 ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ ረዘም ላሉ ቀናት በሚቆይበትም ጊዜ እስራኤላውያን ይሖዋን በመታዘዝ ባሉበት ይቆዩ ነበር።+
20 አንዳንድ ጊዜ ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ የሚቆየው ለጥቂት ቀናት ነበር። እነሱም የሚሰፍሩት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር፤ ተነስተው የሚጓዙትም በይሖዋ ትእዛዝ ነበር።
21 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደመናው የሚቆየው ከምሽት እስከ ጠዋት ድረስ ብቻ ነበር፤ ጠዋት ላይ ደመናው ሲነሳ እነሱም ተነስተው ይጓዛሉ። ቀንም ሆነ ሌሊት ደመናው በሚነሳበት ጊዜ እነሱም ተነስተው ይጓዛሉ።+
22 እስራኤላውያን ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ እስካለ ድረስ ለሁለት ቀንም ይሁን ለአንድ ወር ወይም ረዘም ላለ ጊዜ በሰፈሩበት ይቆያሉ እንጂ ተነስተው አይጓዙም። ደመናው በሚነሳበት ጊዜ ግን ተነስተው ይጓዛሉ።
23 እነሱም የሚሰፍሩት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር፤ ተነስተውም የሚጓዙት በይሖዋ ትእዛዝ ነበር። ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ይሖዋ የጣለባቸውን ግዴታ ይወጡ ነበር።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “የማለፍን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
^ ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
^ ወይም “በሰው ነፍስ።”
^ ወይም “እኛ በሰው ነፍስ።”
^ ወይም “ማንኛውም ሰው በነፍስ።”
^ ቃል በቃል “በሁለቱ ምሽቶች መካከል።”
^ ወይም “ነፍስ።”