ዘፀአት 20:1-26
20 ከዚያም አምላክ ይህን ቃል ሁሉ ተናገረ፦+
2 “ከግብፅ ምድር፣ ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ።+
3 ከእኔ በቀር* ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።+
4 “በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ።+
5 አትስገድላቸው፤ ተታለህም እነሱን አታገልግል፤+ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግና+ በሚጠሉኝ ሁሉ ላይ በአባቶች ስህተት የተነሳ በልጆቻቸው እንዲሁም በሦስተኛና በአራተኛ ትውልዶቻቸው ላይ ቅጣት የማመጣ አምላክ ነኝ፤
6 ሆኖም ለሚወዱኝና ትእዛዛቴን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ታማኝ ፍቅር የማሳይ አምላክ ነኝ።+
7 “የአምላክህን የይሖዋን ስም በከንቱ አታንሳ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ስሙን በከንቱ የሚያነሳውን ሳይቀጣ አይተወውም።+
8 “የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ መጠበቅ እንዳለብህ አትርሳ።+
9 ሥራህንና የምታከናውናቸውን ነገሮች በሙሉ በስድስት ቀን ሠርተህ አጠናቅ፤+
10 ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለይሖዋ ሰንበት ነው። በዚህ ቀን አንተም ሆንክ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህም ሆነ ሴት ባሪያህ፣ የቤት እንስሳህም ሆነ በሰፈርህ* ውስጥ ያለ የባዕድ አገር ሰው ምንም ሥራ አትሥሩ።+
11 ምክንያቱም ይሖዋ ሰማያትን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ ካጠናቀቀ በኋላ በሰባተኛው ቀን ማረፍ ጀምሯል።+ ይሖዋ የሰንበትን ቀን የባረከውና የቀደሰው ለዚህ ነው።
12 “አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም+ አባትህንና እናትህን አክብር።+
13 “አትግደል።*+
14 “አታመንዝር።+
15 “አትስረቅ።+
16 “በባልንጀራህ ላይ ምሥክር ሆነህ ስትቀርብ በሐሰት አትመሥክር።+
17 “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ። የባልንጀራህን ሚስት፣+ ወንድ ባሪያውን፣ ሴት ባሪያውን፣ በሬውን ወይም አህያውን አሊያም የባልንጀራህ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ።”+
18 ሕዝቡም ሁሉ የነጎድጓዱንና የቀንደ መለከቱን ድምፅ ሰሙ፤ እንዲሁም የመብረቁን ብልጭታና የተራራውን ጭስ ተመለከቱ፤ ይህም በፍርሃት እንዲንቀጠቀጡና ርቀው እንዲቆሙ አደረጋቸው።+
19 በመሆኑም ሙሴን “አንተ አነጋግረን፤ እኛም እናዳምጥሃለን፤ ሆኖም እንዳንሞት ስለምንፈራ አምላክ አያነጋግረን” አሉት።+
20 ሙሴም ሕዝቡን “አትፍሩ፤ ምክንያቱም እውነተኛው አምላክ የመጣው እናንተን ለመፈተን+ ይኸውም ዘወትር እሱን በመፍራት ኃጢአት ከመሥራት እንድትቆጠቡ ለማድረግ ነው”+ አላቸው።
21 ሕዝቡም እዚያው ርቆ ባለበት ቆመ፤ ሙሴ ግን እውነተኛው አምላክ ወዳለበት ጥቁር ደመና ቀረበ።+
22 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘ከሰማይ ሆኜ እንዳነጋገርኳችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል።+
23 እኔን የሚቀናቀኑ ከብር የተሠሩ አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከወርቅ የተሠሩ አማልክትም አይኑሯችሁ።+
24 ከጭቃ መሠዊያ ሥራልኝ፤ በእሱም ላይ የሚቃጠሉ መባዎችህን፣ የኅብረት መሥዋዕቶችህን፣* መንጎችህንና ከብቶችህን ሠዋ። ስሜ እንዲታወስ በማደርግበት ቦታ ሁሉ+ ወደ አንተ እመጣለሁ፣ ደግሞም እባርክሃለሁ።
25 ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ በተጠረቡ ድንጋዮች አትሥራው።+ ምክንያቱም ድንጋዮቹን በመሮህ ከጠረብካቸው ታረክሳቸዋለህ።
26 ኀፍረተ ሥጋህ* በእሱ ላይ እንዳይጋለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።’
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “እኔን የሚቀናቀኑ።”
^ ቃል በቃል “በደጆችህ።”
^ እዚህ ላይ የሚገኘው “አትግደል” የሚለው ቃል ሆን ብሎ መግደልን ወይም ሕገ ወጥ ግድያን ያመለክታል።
^ ወይም “የሰላም መባዎችህን።”
^ ቃል በቃል “እርቃንህ።”