ዘፀአት 26:1-37

  • የማደሪያ ድንኳኑ (1-37)

    • የድንኳኑ ጨርቆች (1-14)

    • አራት ማዕዘን ቋሚዎችና መሰኪያዎቻቸው (15-30)

    • መጋረጃውና መከለያው (31-37)

26  “በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ እንዲሁም ከደማቅ ቀይ ማግ ከተዘጋጁ አሥር የድንኳን ጨርቆች የማደሪያ ድንኳኑን+ ትሠራለህ። በጨርቆቹ ላይ ኪሩቦችን+ ትጠልፍባቸዋለህ።+ 2  የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 28 ክንድ* ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ይሆናል። ሁሉም የድንኳን ጨርቆች መጠናቸው እኩል ይሆናል።+ 3  አምስቱ የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ ይቀጣጠላሉ፤ የቀሩት አምስቱ የድንኳን ጨርቆችም እንዲሁ አንድ ላይ ይቀጣጠላሉ። 4  እርስ በርስ ከተቀጣጠሉት የድንኳን ጨርቆች በመጨረሻው ጨርቅ ጠርዝ ላይ ከሰማያዊ ክር የተሠሩ ማቆላለፊያዎችን ታደርጋለህ፤ እርስ በርስ የተቀጣጠለው ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት የመጨረሻው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይም እንዲሁ ታደርጋለህ። 5  በአንደኛው የድንኳን ጨርቅ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ትሠራለህ፤ በሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ጠርዝ ላይም 50 ማቆላለፊያዎችን ታደርጋለህ፤ ማቆላለፊያዎቹም የሚጋጠሙበት ቦታ ላይ እርስ በርሳቸው ትይዩ ይሆናሉ። 6  ከዚያም 50 የወርቅ ማያያዣዎችን ሠርተህ የድንኳን ጨርቆቹን በማያያዣዎቹ አማካኝነት እርስ በርስ ታጋጥማቸዋለህ፤ በዚህ መንገድ ማደሪያ ድንኳኑ አንድ ወጥ ይሆናል።+ 7  “በተጨማሪም ለማደሪያ ድንኳኑ ልባስ የሚሆኑ ጨርቆችን ከፍየል ፀጉር+ ትሠራለህ። አሥራ አንድ የድንኳን ጨርቆችን ትሠራለህ።+ 8  የእያንዳንዱ የድንኳን ጨርቅ ርዝመት 30 ክንድ ወርዱ ደግሞ 4 ክንድ ይሆናል። የአሥራ አንዱም የድንኳን ጨርቆች መጠን እኩል ይሆናል። 9  አምስቱን የድንኳን ጨርቆች አንድ ላይ ትቀጣጥላቸዋለህ፤ የቀሩትን ስድስቱን የድንኳን ጨርቆች ደግሞ አንድ ላይ ትቀጣጥላቸዋለህ፤ ስድስተኛውን የድንኳን ጨርቅ በድንኳኑ ፊት በኩል ታጥፈዋለህ። 10  እርስ በርስ ከተቀጣጠሉት የድንኳን ጨርቆች በመጨረሻው ጠርዝ ላይ 50 ማቆላለፊያዎችን ትሠራለህ፤ እርስ በርስ የተቀጣጠለው ሌላኛው የድንኳን ጨርቅ ከዚህኛው ጋር በሚጋጠምበት ጨርቅ ጠርዝ ላይም 50 ማቆላለፊያዎችን ታደርጋለህ። 11  ከዚያም 50 የመዳብ ማያያዣዎችን ትሠራለህ፤ ማያያዣዎቹንም ማቆላለፊያዎቹ ውስጥ በማስገባት ድንኳኑን ታጋጥመዋለህ፤ በዚህ መንገድ የድንኳኑ ጨርቅ አንድ ወጥ ይሆናል። 12  ከድንኳኑ ጨርቆች ትርፍ ሆኖ የወጣው እንደተንጠለጠለ ይተዋል። ትርፍ ሆኖ የወጣው ግማሹ የድንኳን ጨርቅ በማደሪያ ድንኳኑ ጀርባ ላይ ይንጠለጠላል። 13  ትርፍ ሆኖ የወጣው አንድ አንድ ክንድ ጨርቅ ድንኳኑን እንዲሸፍን በማደሪያ ድንኳኑ ጎንና ጎን ይንጠለጠላል። 14  “በተጨማሪም ቀይ ቀለም ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ለድንኳኑ መደረቢያ ትሠራለህ፤ በዚያ ላይ የሚደረግ መደረቢያም ከአቆስጣ ቆዳ ትሠራለህ።+ 15  “የግራር እንጨት ጣውላዎችን በማገጣጠም ለማደሪያ ድንኳኑ የሚሆኑ አራት ማዕዘን ቋሚዎችን ትሠራለህ።+ 16  የእያንዳንዱ ቋሚ ቁመት አሥር ክንድ ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ይሆናል። 17  እያንዳንዱ ቋሚም እርስ በርስ የተያያዙ ሁለት ጉጦች ይኑሩት። ለማደሪያ ድንኳኑ የሚያገለግሉትን ቋሚዎች በሙሉ በዚህ መንገድ ሥራቸው። 18  በስተ ደቡብ በኩል ለሚገኘው ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ላለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን 20 ቋሚዎችን ትሠራለህ። 19  “ከ20ዎቹ ቋሚዎች ሥር የሚሆኑ 40 የብር መሰኪያዎችን+ ትሠራለህ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ያሉት ሁለት ጉጦች ሁለት መሰኪያዎች፣ ቀጥሎ ባለው በእያንዳንዱ ቋሚ ሥር ያሉት ሁለት ጉጦችም+ ሁለት መሰኪያዎች ይኖሯቸዋል። 20  በስተ ሰሜን በኩል ላለው ለሌላኛውም የማደሪያ ድንኳኑ ጎን 20 ቋሚዎችን ሥራ፤ 21  እንዲሁም 40 የብር መሰኪያዎቻቸውን ሥራ፤ በአንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎች፣ ቀጥሎ ባለው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎች ይኑሩ። 22  በስተ ምዕራብ በኩል ለሚገኘው ለኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ስድስት ቋሚዎችን ትሠራለህ።+ 23  በማደሪያ ድንኳኑ በስተ ኋላ በኩል የማዕዘን ቋሚዎች እንዲሆኑ ሁለት ቋሚዎችን ትሠራለህ። 24  ቋሚዎቹም ከታች አንስቶ የመጀመሪያው ቀለበት እስከሚገኝበት እስከ ላይ ድረስ ድርብ መሆን አለባቸው። ሁለቱም በዚህ መንገድ መሠራት አለባቸው፤ እነሱም ሁለት የማዕዘን ቋሚዎች ሆነው ያገለግላሉ። 25  ስምንት ቋሚዎችና ከብር የተሠሩ 16 መሰኪያዎች ይኸውም በአንዱ ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎች፣ ቀጥሎ ባለው በእያንዳንዱም ቋሚ ሥር ሁለት መሰኪያዎች ይኖራሉ። 26  “ከግራር እንጨት አግዳሚ እንጨቶችን ታዘጋጃለህ፤ በአንዱ ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን፣+ 27  በሌላኛው ጎን ላሉት የማደሪያ ድንኳኑ ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን እንዲሁም በስተ ምዕራብ በኩል ባለው በኋለኛው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ላሉት ቋሚዎች አምስት አግዳሚ እንጨቶችን ታዘጋጃለህ። 28  በቋሚዎቹ መሃል ላይ የሚያርፈው መካከለኛው አግዳሚ እንጨት ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚዘልቅ መሆን ይኖርበታል። 29  “ቋሚዎቹን በወርቅ ትለብጣቸዋለህ፤+ አግዳሚ እንጨቶቹን የሚሸከሙትን የቋሚዎቹን ቀለበቶች ከወርቅ ትሠራቸዋለህ፤ አግዳሚ እንጨቶቹንም በወርቅ ትለብጣቸዋለህ። 30  የማደሪያ ድንኳኑን በተራራው ላይ ተገልጦልህ ባየኸው ንድፍ መሠረት ትከለው።+ 31  “ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር መጋረጃ+ ትሠራለህ። በላዩም ላይ ኪሩቦች ይጠለፉበታል። 32  መጋረጃውንም በወርቅ በተለበጡ አራት የግራር እንጨት ዓምዶች ላይ ታንጠለጥለዋለህ። ማንጠልጠያዎቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ። ዓምዶቹም ከብር በተሠሩ አራት መሰኪያዎች ላይ ይቆማሉ። 33  መጋረጃውን ከማያያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፤ የምሥክሩንም ታቦት+ በመጋረጃው ውስጥ ታስቀምጠዋለህ። መጋረጃውም ቅድስቱንና+ ቅድስተ ቅዱሳኑን+ ለመለየት ያገለግላችኋል። 34  መክደኛውንም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በሚገኘው በምሥክሩ ታቦት ላይ ግጠመው። 35  “ጠረጴዛውንም ከመጋረጃው ውጭ ታስቀምጠዋለህ፤ መቅረዙን+ በስተ ደቡብ በኩል ባለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ከጠረጴዛው ትይዩ ታስቀምጠዋለህ፤ ጠረጴዛውን ደግሞ በስተ ሰሜን በኩል ታስቀምጠዋለህ። 36  ለድንኳኑ መግቢያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር የተሸመነ መከለያ* ትሠራለህ።+ 37  ለመከለያውም* አምስት ዓምዶችን ከግራር እንጨት ትሠራለህ፤ በወርቅም ትለብጣቸዋለህ። ማንጠልጠያዎቹም ከወርቅ የተሠሩ ይሆናሉ፤ ለዓምዶቹም አምስት የመዳብ መሰኪያዎችን ትሠራለህ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “ለመጋረጃውም።”