ዘፀአት 3:1-22

  • ሙሴና የሚነደው ቁጥቋጦ (1-12)

  • ይሖዋ የስሙን ትርጉም ገለጠ (13-15)

  • ይሖዋ ለሙሴ የሰጠው ትእዛዝ (16-22)

3  ሙሴ የምድያም ካህን የሆነው የአማቱ የዮቶር+ መንጋ እረኛ ሆነ። እሱም መንጋውን እየመራ ወደ ምድረ በዳው ምዕራባዊ ክፍል ከተጓዘ በኋላ በመጨረሻ ወደ እውነተኛው አምላክ ተራራ ወደ ኮሬብ+ ደረሰ። 2  ከዚያም የይሖዋ መልአክ በቁጥቋጦ መሃል በሚነድ የእሳት ነበልባል ውስጥ ተገለጠለት።+ እሱም ትኩር ብሎ ሲመለከት ቁጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም አለመቃጠሉን አስተዋለ። 3  ስለዚህ ሙሴ “ይህ እንግዳ ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅና ቁጥቋጦው የማይቃጠለው ለምን እንደሆነ ለማየት እስቲ ቀረብ ልበል” አለ። 4  ይሖዋም ሙሴ ሁኔታውን ለማየት ቀረብ ማለቱን ሲመለከት ከቁጥቋጦው መሃል “ሙሴ! ሙሴ!” ሲል ጠራው፤ እሱም “አቤት” አለ። 5  ከዚያም አምላክ “ከዚህ በላይ እንዳትቀርብ። የቆምክበት ስፍራ ቅዱስ መሬት ስለሆነ ጫማህን አውልቅ” አለው። 6  እሱም በመቀጠል “እኔ የአባትህ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣+ የይስሐቅ አምላክና+ የያዕቆብ አምላክ+ ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እውነተኛውን አምላክ ለማየት ስለፈራ ፊቱን ከለለ። 7  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “በግብፅ የሚኖረውን የሕዝቤን መከራ በእርግጥ አይቻለሁ፤ አስገድደው በሚያሠሯቸው ሰዎች የተነሳ የሚያሰሙትን ጩኸት ሰምቻለሁ፤ እየደረሰባቸው ያለውንም ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ።+ 8  እኔም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸው+ እንዲሁም ከዚያ ምድር አውጥቼ ወደ ከነአናውያን፣ ወደ ሂታውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፈሪዛውያን፣ ወደ ሂዋውያንና ወደ ኢያቡሳውያን ግዛት ይኸውም ወተትና ማር ወደምታፈሰው መልካምና ሰፊ ምድር+ ላስገባቸው እወርዳለሁ።+ 9  እነሆ የእስራኤል ሕዝብ የሚያሰማው ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብፃውያኑ እነሱን በመጨቆን እያደረሱባቸው ያለውን በደል ተመልክቻለሁ።+ 10  ስለዚህ አሁን ና፤ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ፤ አንተም ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ታወጣለህ።”+ 11  ይሁን እንጂ ሙሴ እውነተኛውን አምላክ “ወደ ፈርዖን የምሄደውና እስራኤላውያንን ከግብፅ የማወጣው ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ?” አለው። 12  እሱም በዚህ ጊዜ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤+ የላክሁህ እኔ ለመሆኔም ምልክቱ ይህ ነው፦ ሕዝቡን ከግብፅ ካወጣሃቸው በኋላ እውነተኛውን አምላክ በዚህ ተራራ ላይ ታገለግላላችሁ”*+ አለው። 13  ሆኖም ሙሴ እውነተኛውን አምላክ “ወደ እስራኤላውያን ሄጄ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው እነሱ ደግሞ ‘ስሙ ማን ነው?’+ ብለው ቢጠይቁኝ ምን ልበላቸው?” አለው። 14  በዚህ ጊዜ አምላክ ሙሴን “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ”*+ አለው። በመቀጠልም “እስራኤላውያንን ‘“እሆናለሁ” ወደ እናንተ ልኮኛል’+ በላቸው” አለው። 15  ከዚያም አምላክ ሙሴን በድጋሚ እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣+ የይስሐቅ አምላክና+ የያዕቆብ አምላክ+ የሆነው ይሖዋ ወደ እናንተ ልኮኛል።’ ይህ ለዘላለም ስሜ ነው፤+ ከትውልድ እስከ ትውልድ የምታወሰውም በዚህ ነው። 16  አሁን ሄደህ የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሰብስብ፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው ይሖዋ ተገልጦልኝ እንዲህ አለኝ፦ “እናንተንም ሆነ ግብፅ ውስጥ እየደረሰባችሁ ያለውን ነገር በእርግጥ ተመልክቻለሁ።+ 17  በመሆኑም እንዲህ አልኩ፦ ግብፃውያን ከሚያደርሱባችሁ መከራ አውጥቼ+ ከነአናውያን፣ ሂታውያን፣ አሞራውያን፣+ ፈሪዛውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን+ ወደሚኖሩባት ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር+ አስገባችኋለሁ።”’ 18  “እነሱም በእርግጥ ቃልህን ይሰማሉ፤+ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎችም ወደ ግብፁ ንጉሥ ሄዳችሁ እንዲህ በሉት፦ ‘የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ+ አነጋግሮን ነበር። በመሆኑም እባክህ ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንድንጓዝ ፍቀድልን።’+ 19  ይሁንና የግብፁ ንጉሥ ኃያል የሆነ ክንድ ካላስገደደው በስተቀር እንድትሄዱ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ ራሴ በሚገባ አውቃለሁ።+ 20  በመሆኑም እጄን እዘረጋለሁ፤ ግብፅንም በመካከሏ በምፈጽማቸው ድንቅ ነገሮች ሁሉ እመታለሁ፤ ከዚያ በኋላ ይለቃችኋል።+ 21  እኔም ለዚህ ሕዝብ በግብፃውያን ፊት ሞገስ እሰጠዋለሁ፤ በምትወጡበትም ጊዜ በምንም ዓይነት ባዶ እጃችሁን አትሄዱም።+ 22  እያንዳንዷ ሴት ከጎረቤቷና ቤቷ ካረፈችው ሴት የብርና የወርቅ ዕቃዎችን እንዲሁም ልብሶችን ትጠይቅ፤ እነዚህንም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻችሁ ታደርጉላቸዋላችሁ፤ ግብፃውያኑንም ትበዘብዛላችሁ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ታመልካላችሁ።”
ወይም “የምሆነውን እሆናለሁ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ4ን ተመልከት።