ዘፀአት 40:1-38
40 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦
2 “በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የማደሪያ ድንኳኑን ይኸውም የመገናኛ ድንኳኑን ትከል።+
3 የምሥክሩን ታቦት በውስጡ ካስቀመጥክ+ በኋላ ታቦቱን በመጋረጃው ከልለው።+
4 ጠረጴዛውንም+ ካስገባህ በኋላ በላዩ ላይ የሚቀመጡትን ነገሮች አስተካክለህ አስቀምጥ፤ መቅረዙንም+ አስገብተህ መብራቶቹን+ አብራቸው።
5 ከዚያም ለዕጣን የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ+ ከምሥክሩ ታቦት በፊት አስቀምጠው፤ ለማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ የሚሆነውን መከለያም* በቦታው አድርገው።+
6 “የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያም+ በማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ፊት አድርገው፤
7 ገንዳውንም በመገናኛ ድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አድርገህ ውኃ ጨምርበት።+
8 በመገናኛ ድንኳኑም ዙሪያ ግቢ ከልልለት፤+ ለግቢውም መግቢያ መከለያ*+ አድርግለት።
9 የማደሪያ ድንኳኑም የተቀደሰ እንዲሆን የቅብዓት ዘይቱን+ ወስደህ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ትቀባቸዋለህ፤+ ድንኳኑንም ሆነ ዕቃዎቹን በሙሉ ትቀድሳለህ።
10 የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትም መሠዊያ እጅግ ቅዱስ እንዲሆን መሠዊያውንና ዕቃዎቹን በሙሉ ትቀባቸዋለህ፤ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ።+
11 ገንዳውንና ማስቀመጫውንም ቀባ፤ ቀድሰውም።
12 “ከዚያም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ አቅርባቸው፤ በውኃም እጠባቸው።+
13 አሮንንም ቅዱስ የሆኑትን ልብሶች ካለበስከው+ በኋላ ቀባው፤+ እንዲሁም ቀድሰው፤ እሱም ካህን ሆኖ ያገለግለኛል።
14 ከዚያም ወንዶች ልጆቹን አቅርበህ ረጃጅሞቹን ቀሚሶች አልብሳቸው።+
15 ካህናት ሆነውም እንዲያገለግሉኝ አባታቸውን እንደቀባኸው ሁሉ እነሱንም ቀባቸው፤+ መቀባታቸውም ክህነታቸው ለትውልዶቻቸው ሁሉ በዘላቂነት እንዲቀጥል ያስችላል።”+
16 ሙሴም ይሖዋ ባዘዘው መሠረት አደረገ።+ ልክ እንደዚሁ አደረገ።
17 በሁለተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የማደሪያ ድንኳኑ ተተከለ።+
18 ሙሴም የማደሪያ ድንኳኑን ሲተክል መሰኪያዎቹን+ ከሥር በማስቀመጥ አራት ማዕዘን ቋሚዎቹን+ አደረገባቸው፤ አግዳሚ እንጨቶቹንም+ አስገባቸው፤ ዓምዶቹንም አቆማቸው።
19 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የማደሪያ ድንኳኑን በድንኳኑ ጨርቅ አለበሰው፤+ በላዩም ላይ የድንኳኑን መደረቢያ ደረበበት።+
20 ቀጥሎም የምሥክሩን ጽላቶች+ ወስዶ በታቦቱ+ ውስጥ አስቀመጣቸው፤ የታቦቱንም መሎጊያዎች+ አስገባቸው፤ መክደኛውንም+ በታቦቱ ላይ አደረገው።+
21 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ታቦቱን ወደ ማደሪያ ድንኳኑ አስገባው፤ የመግቢያው መከለያ የሆነውን መጋረጃ+ በቦታው በማድረግ የምሥክሩን ታቦት ከለለው።+
22 በመቀጠልም ጠረጴዛውን+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ በስተ ሰሜን በኩል ባለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን ከመጋረጃው ውጭ አደረገው፤
23 በላዩም ላይ ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የተነባበረውን ኅብስት በይሖዋ ፊት አስቀመጠ።+
24 መቅረዙንም+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ከጠረጴዛው ትይዩ፣ በስተ ደቡብ በኩል ባለው የማደሪያ ድንኳኑ ጎን አስቀመጠው።
25 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት መብራቶቹን+ በይሖዋ ፊት አበራቸው።
26 የወርቅ መሠዊያውንም+ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ከመጋረጃው በፊት አስቀመጠው፤
27 ይህን ያደረገውም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን+ እንዲጨስበት+ ነው።
28 ቀጥሎም የማደሪያ ድንኳኑን መግቢያ መከለያ*+ በቦታው አደረገው።
29 ከዚያም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት የሚቃጠለውን መባና የእህሉን መባ በላዩ ላይ እንዲያቀርብበት የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ+ በማደሪያ ድንኳኑ ይኸውም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ አደረገው።
30 በመቀጠልም ገንዳውን በመገናኛ ድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አደረገው፤ ለመታጠቢያ የሚሆን ውኃም ጨመረበት።+
31 ሙሴ እንዲሁም አሮንና ወንዶች ልጆቹ እጃቸውንና እግራቸውን ታጠቡበት።
32 ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገቡበትና ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ ሁሉ ይታጠቡ ነበር።+
33 በመጨረሻም በማደሪያ ድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ ግቢውን ከለለ፤+ ለግቢውም መግቢያ መከለያ* አደረገለት።+
በዚህ መንገድ ሙሴ ሥራውን አጠናቀቀ።
34 ደመናውም የመገናኛ ድንኳኑን ሸፈነው፤ የይሖዋም ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ሞላው።+
35 ደመናው በመገናኛ ድንኳኑ ላይ አርፎ ስለነበርና የይሖዋም ክብር የማደሪያ ድንኳኑን ስለሞላው ሙሴ ወደ መገናኛ ድንኳኑ መግባት አልቻለም ነበር።+
36 እስራኤላውያንም በጉዟቸው ወቅት ሁሉ ደመናው ከማደሪያ ድንኳኑ ላይ በሚነሳበት ጊዜ ድንኳናቸውን ነቅለው ይንቀሳቀሱ ነበር።+
37 ሆኖም ደመናው ካልተነሳ፣ ደመናው እስከሚነሳበት ቀን ድረስ ድንኳናቸውን ነቅለው አይንቀሳቀሱም ነበር።+
38 መላው የእስራኤል ቤት በሚጓዝበት ወቅት ሁሉ ቀን ቀን የይሖዋ ደመና፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ እሳት በማደሪያ ድንኳኑ ላይ ሆኖ ያይ ነበር።+