ዘፍጥረት 15:1-21

  • አምላክ ከአብራም ጋር የገባው ቃል ኪዳን (1-21)

    • ለ400 ዓመት እንደሚጨቆኑ ትንቢት ተነገረ (13)

    • አምላክ ለአብራም ዳግመኛ ቃል ገባለት (18-21)

15  ከዚህ በኋላ የይሖዋ ቃል በራእይ ወደ አብራም መጥቶ “አብራም አትፍራ።+ እኔ ጋሻ እሆንሃለሁ።+ የምታገኘውም ሽልማት እጅግ ታላቅ ይሆናል”+ አለው። 2  አብራምም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ያለልጅ እንደቀረሁና ቤቴን የሚወርሰው የደማስቆ ሰው የሆነው ኤሊዔዘር+ እንደሆነ ታያለህ፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?” 3  በተጨማሪም አብራም “እንግዲህ ዘር አልሰጠኸኝም፤+ ደግሞም ወራሼ የሚሆነው በቤቴ ያለው አገልጋይ* ነው” አለ። 4  ሆኖም እንዲህ የሚል የይሖዋ ቃል ወደ እሱ መጣ፦ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ልጅህ* ወራሽህ ይሆናል።”+ 5  ወደ ውጭም ካወጣው በኋላ “እባክህ ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቁጠር ከቻልክ ከዋክብቱን ቁጠራቸው” አለው። ከዚያም “የአንተም ዘር እንዲሁ ይሆናል”+ አለው። 6  አብራምም በይሖዋ አመነ፤+ አምላክም ይህን ጽድቅ አድርጎ ቆጠረለት።+ 7  ደግሞም እንዲህ አለው፦ “ይህችን ምድር ርስት አድርጌ ልሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እኔ ይሖዋ ነኝ።”+ 8  አብራምም “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ ይህችን ምድር ርስት አድርጌ እንደምወርስ እንዴት አውቃለሁ?” አለ። 9  እሱም መልሶ “አንዲት የሦስት ዓመት ጊደር፣ አንዲት የሦስት ዓመት ፍየል፣ አንድ የሦስት ዓመት አውራ በግ እንዲሁም አንድ ዋኖስና አንድ የርግብ ጫጩት ውሰድ” አለው። 10  እሱም እነዚህን እንስሳት ሁሉ ወስዶ ለሁለት ሰነጠቃቸው፤ ከዚያም አንዱን ግማሽ ከሌላኛው ግማሽ ትይዩ አድርጎ አስቀመጠ። ወፎቹን ግን አልሰነጠቃቸውም። 11  አሞሮችም በበድኖቹ ላይ መውረድ ጀመሩ፤ አብራም ግን ያባርራቸው ነበር። 12  ፀሐይ ልትጠልቅ ስትቃረብም አብራም ከባድ እንቅልፍ ወሰደው፤ ታላቅና የሚያስፈራ ጨለማም ወረደበት። 13  አምላክም አብራምን እንዲህ አለው፦ “ዘሮችህ በባዕድ አገር ባዕዳን ሆነው እንደሚኖሩ እንዲሁም በዚያ ያሉት ሰዎች ለ400 ዓመት በባርነት እንደሚገዟቸውና እንደሚያጎሳቁሏቸው በእርግጥ እወቅ።+ 14  ይሁንና በባርነት በሚገዛቸው ብሔር ላይ እፈርዳለሁ፤+ እነሱም ብዙ ንብረት ይዘው ይወጣሉ።+ 15  አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜ ጠግበህም ወደ መቃብር ትወርዳለህ።+ 16  ሆኖም በአራተኛው ትውልድ ወደዚህ ይመለሳሉ፤+ ምክንያቱም የአሞራውያን በደል ጽዋው ገና አልሞላም።”+ 17  ፀሐይዋ ከጠለቀችና ድቅድቅ ጨለማ አካባቢውን ከዋጠው በኋላ የሚጨስ ምድጃ ታየ፤ ለሁለት በተከፈለውም ሥጋ መካከል የሚንቦገቦግ ችቦ አለፈ። 18  በዚያ ቀን ይሖዋ እንዲህ ሲል ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገባ፦+ “ከግብፅ ወንዝ አንስቶ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ+ ድረስ ያለውን ይህን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤+ 19  የቄናውያንን፣+ የቀኒዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣ 20  የሂታውያንን፣+ የፈሪዛውያንን፣+ የረፋይምን፣+ 21  የአሞራውያንን፣ የከነአናውያንን፣ የገርጌሻውያንንና የኢያቡሳውያንን+ ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ወንድ ልጅ።”
ቃል በቃል “የአብራክህ ክፋይ።”