ዘፍጥረት 28:1-22

  • ይስሐቅ ያዕቆብን ወደ ጳዳንአራም ላከው (1-9)

  • ያዕቆብ በቤቴል ያለመው ሕልም (10-22)

    • አምላክ የሰጠውን ተስፋ በድጋሚ ለያዕቆብ አረጋገጠለት (13-15)

28  በመሆኑም ይስሐቅ ያዕቆብን ጠርቶ ባረከውና እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ከከነአን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳታገባ።+  በጳዳንአራም ወደሚገኘው ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድና ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች+ መካከል አንዷን አግባ።  ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይባርክሃል፤ ፍሬያማም ያደርግሃል፤ እንዲሁም ያበዛሃል፤ አንተም በእርግጥ ብዙ ሕዝብ ያቀፈ ጉባኤ ትሆናለህ።+  አምላክ ለአብርሃም የሰጠውን፣+ አንተም እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነህ የምትኖርበትን ምድር እንድትወርስ የአብርሃምን በረከት+ ለአንተና ከአንተ ጋር ላለው ዘርህ ይሰጣል።”  ስለሆነም ይስሐቅ ያዕቆብን አሰናበተው፤ እሱም የያዕቆብና የኤሳው እናት የርብቃ ወንድም+ እንዲሁም የአራማዊው የባቱኤል ልጅ ወደሆነው ወደ ላባ+ ለመሄድ ወደ ጳዳንአራም ጉዞ ጀመረ።  ኤሳው፣ ይስሐቅ ያዕቆብን እንደባረከውና ሚስት እንዲያገባ ወደ ጳዳንአራም እንደላከው እንዲሁም በባረከው ጊዜ “ከከነአን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳታገባ”+ ብሎ እንዳዘዘውና  ያዕቆብም አባቱንና እናቱን በመታዘዝ ወደ ጳዳንአራም እንደሄደ አወቀ።+  በዚህ ጊዜ ኤሳው የከነአን ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ዘንድ የተጠሉ መሆናቸውን ተገነዘበ፤+  ስለዚህ ኤሳው ወደ እስማኤል ሄደ፤ ካሉትም ሚስቶች በተጨማሪ የአብርሃም ልጅ እስማኤል የወለዳትን የነባዮትን እህት ማሃላትን አገባ።+ 10  ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነስቶ ወደ ካራን አቀና።+ 11  ከዚያም ወደ አንድ ስፍራ ደረሰ፤ ፀሐይ ጠልቃ ስለነበረም እዚያ ለማደር አሰበ። በመሆኑም በአካባቢው ካሉት ድንጋዮች አንዱን አንስቶ በመንተራስ እዚያው ተኛ።+ 12  እሱም ሕልም አለመ፤ በሕልሙም በምድር ላይ የተተከለ ደረጃ* አየ፤ የደረጃውም ጫፍ እስከ ሰማያት ይደርስ ነበር፤ በላዩም ላይ የአምላክ መላእክት ይወጡና ይወርዱ ነበር።+ 13  ከደረጃውም በላይ ይሖዋ ነበር፤ እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክና የይስሐቅ አምላክ ይሖዋ ነኝ።+ የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ።+ 14  ዘርህም በእርግጥ እንደ ምድር አፈር ብዙ ይሆናል፤+ ወደ ምዕራብ፣ ወደ ምሥራቅ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ትስፋፋለህ። የምድር ቤተሰቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካኝነት በእርግጥ ይባረካሉ።*+ 15  እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበት ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልስሃለሁ።+ የገባሁልህን ቃል እስክፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።”+ 16  ከዚያም ያዕቆብ ከእንቅልፉ ነቅቶ “በእርግጥም በዚህ ስፍራ ይሖዋ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅኩም ነበር” አለ። 17  እሱም በፍርሃት ተዋጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ይህ ስፍራ እንዴት የሚያስፈራ ነው! ይህ የአምላክ ቤት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፤+ ይህ የሰማያት በር ነው።”+ 18  በመሆኑም ያዕቆብ በማለዳ ተነሳ፤ ተንተርሶት የነበረውን ድንጋይ ወስዶ እንደ ዓምድ አቆመው፤ በአናቱም ላይ ዘይት አፈሰሰበት።+ 19  ስለዚህ ያን ቦታ ቤቴል* አለው፤ የከተማዋ የቀድሞ ስም ግን ሎዛ+ ነበር። 20  ከዚያም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ስእለት ተሳለ፦ “አምላክ ከእኔ ባይለይና በመንገዴ ቢጠብቀኝ እንዲሁም የምበላው ምግብና የምለብሰው ልብስ ቢሰጠኝ፣ 21  ወደ አባቴም ቤት በሰላም ብመለስ ይሖዋ አምላኬ መሆኑን አስመሠከረ ማለት ነው። 22  እንደ ዓምድ ያቆምኩት ይህ ድንጋይም የአምላክ ቤት ይሆናል፤+ አምላክ ሆይ፣ እኔም ከምትሰጠኝ ከማንኛውም ነገር አንድ አሥረኛውን ለአንተ እሰጣለሁ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መሰላል።”
ወይም “ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።”
“የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም አለው።