የሐዋርያት ሥራ 12:1-25
12 በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሄሮድስ በአንዳንድ የጉባኤው አባላት ላይ ስደት ማድረስ ጀመረ።+
2 የዮሐንስን ወንድም ያዕቆብን+ በሰይፍ ገደለው።+
3 ይህ ድርጊቱ አይሁዳውያንን እንዳስደሰተ ባየ ጊዜ ጴጥሮስን ደግሞ በቁጥጥር ሥር አዋለው። (ይህም የሆነው በቂጣ* በዓል ሰሞን ነበር።)+
4 ከያዘውና እስር ቤት ካስገባው+ በኋላ በአራት ፈረቃ፣ አራት አራት ሆነው እንዲጠብቁት ለተመደቡ ወታደሮች አስረከበው፤ ይህን ያደረገው ከፋሲካ* በኋላ ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው* አስቦ ነው።
5 ስለዚህ ጴጥሮስ እስር ቤት እንዲቆይ ተደረገ፤ ሆኖም ጉባኤው ስለ እሱ ወደ አምላክ አጥብቆ ይጸልይ ነበር።+
6 ሄሮድስ ጴጥሮስን ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው ካሰበበት ቀን በፊት በነበረው ሌሊት፣ ጴጥሮስ በሁለት ወታደሮች መካከል በሁለት ሰንሰለቶች ታስሮ ተኝቶ ነበር፤ በር ላይ ያሉ ጠባቂዎችም እስር ቤቱን እየጠበቁ ነበር።
7 ይሁንና የይሖዋ* መልአክ ድንገት መጥቶ ቆመ፤+ በክፍሉም ውስጥ ብርሃን በራ። ጴጥሮስን ጎኑን መታ አድርጎ ከእንቅልፉ ቀሰቀሰውና “ቶሎ ብለህ ተነሳ!” አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ላይ ወደቁ።+
8 መልአኩም “በል ልብስህን ልበስ፤* ጫማህንም አድርግ” አለው። እሱም እንደተባለው አደረገ። ከዚያም “መደረቢያህን ልበስና ተከተለኝ” አለው።
9 እሱም ወጥቶ ይከተለው ጀመር፤ ይሁንና መልአኩ እያደረገ ያለው ነገር በእውን እየተከናወነ ያለ አልመሰለውም። እንዲያውም ራእይ የሚያይ መስሎት ነበር።
10 የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ከእስር ቤቱ ወደ ከተማዋ ወደሚያስወጣው የብረት መዝጊያ ደረሱ፤ መዝጊያውም በራሱ ተከፈተላቸው። ከወጡ በኋላ በአንድ ጎዳና አብረው ተጓዙ፤ ወዲያውም መልአኩ ተለይቶት ሄደ።
11 ጴጥሮስም የሆነውን ነገር ሲረዳ “ይሖዋ* መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና አይሁዳውያን በእኔ ላይ ይደርሳል ብለው ካሰቡት ነገር ሁሉ እንደታደገኝ አሁን በእርግጥ አወቅኩ” አለ።+
12 ይህን ከተገነዘበ በኋላ ማርቆስ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ዮሐንስ+ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ በዚያም በርከት ያሉ ሰዎች ተሰብስበው ይጸልዩ ነበር።
13 የውጭውን በር ሲያንኳኳ ሮዳ የተባለች አንዲት አገልጋይ በሩን ለመክፈት መጣች።
14 የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑን ባወቀች ጊዜ በጣም ከመደሰቷ የተነሳ በሩን ሳትከፍት ሮጣ ወደ ውስጥ በመግባት ጴጥሮስ በር ላይ መቆሙን ተናገረች።
15 እነሱም “አብደሻል እንዴ!” አሏት። እሷ ግን ያንኑ አስረግጣ መናገሯን ቀጠለች። እነሱም “ከሆነም የእሱ መልአክ ይሆናል” አሉ።
16 ጴጥሮስ ግን እዚያው ቆሞ ማንኳኳቱን ቀጠለ። በሩን ከከፈቱም በኋላ ሲያዩት በጣም ተገረሙ።
17 እሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ምልክት ከሰጣቸው በኋላ ይሖዋ* ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው በዝርዝር ነገራቸው፤ ከዚያም “ይህን ነገር ለያዕቆብና+ ለወንድሞች ንገሯቸው” አላቸው። ይህን ካለም በኋላ ወጥቶ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ።
18 በነጋም ጊዜ ወታደሮቹ ጴጥሮስ የት እንደደረሰ ግራ ስለተጋቡ በመካከላቸው ከፍተኛ ትርምስ ተፈጠረ።
19 ሄሮድስም ፈልጎ አፈላልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎቹን ከመረመረ በኋላ እርምጃ እንዲወሰድባቸው አዘዘ፤+ ከዚያም ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ በዚያ የተወሰነ ጊዜ ተቀመጠ።
20 ሄሮድስ በጢሮስና በሲዶና ሰዎች ላይ በጣም ተቆጥቶ* ነበር። እነሱም በአንድ ልብ ሆነው ወደ እሱ በመምጣት የንጉሡ ባለሟል* የሆነውን ብላስጦስን ካግባቡ በኋላ ንጉሡን እርቅ ጠየቁ፤ ይህን ያደረጉት አገራቸው ምግብ የምታገኘው ከንጉሡ ግዛት ስለነበረ ነው።
21 አንድ ልዩ ዝግጅት በተደረገበት ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ፤ ከዚያም ለሕዝቡ ንግግር መስጠት ጀመረ።
22 የተሰበሰበውም ሕዝብ “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው አይደለም!” እያለ ይጮኽ ጀመር።
23 በዚህ ጊዜ፣ ለአምላክ ክብር ባለመስጠቱ ወዲያውኑ የይሖዋ* መልአክ ቀሰፈው፤ በትል ተበልቶም ሞተ።
24 የይሖዋ* ቃል ግን እየተስፋፋ ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም አማኞች ሆኑ።+
25 በርናባስና+ ሳኦልም በኢየሩሳሌም እርዳታ ከሰጡ በኋላ ተመለሱ፤+ ማርቆስ ተብሎ የሚጠራውን ዮሐንስንም ይዘውት መጡ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ከማለፍ በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ሊያስፈርድበት።”
^ ወይም “ታጠቅ።”
^ ወይም “ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎች ጋር ተጣልቶ።”
^ ቃል በቃል “የንጉሡ መኝታ ቤት ሹም።”