የሐዋርያት ሥራ 26:1-32
26 አግሪጳ+ ጳውሎስን “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል የመከላከያ መልሱን ይሰጥ ጀመር፦
2 “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ አይሁዳውያን በእኔ ላይ ያቀረቡትን ክስ+ ሁሉ በተመለከተ ዛሬ በአንተ ፊት የመከላከያ መልስ መስጠት በመቻሌ እጅግ ደስተኛ ነኝ፤
3 በተለይ ደግሞ አንተ የአይሁዳውያንን ልማዶችና በመካከላቸው ያሉትን ክርክሮች ሁሉ ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ስለዚህ በትዕግሥት እንድታዳምጠኝ እለምንሃለሁ።
4 “ገና ከልጅነቴ በሕዝቤ መካከልም ሆነ በኢየሩሳሌም እንዴት እንደኖርኩ አይሁዳውያን ሁሉ በሚገባ ያውቃሉ፤+
5 ከድሮ ጀምሮ የሚያውቁኝ ሰዎች ሊመሠክሩ ፈቃደኞች ቢሆኑ ኖሮ በሃይማኖታችን ውስጥ ወግ አጥባቂ የሆነውን ቡድን በመከተል+ ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርኩ ያውቃሉ።+
6 አሁን ግን እዚህ ለፍርድ የቀረብኩት አምላክ ለአባቶቻችን የገባውን ቃል ተስፋ በማድረጌ ነው፤+
7 ደግሞም 12ቱ ነገዶቻችን ለአምላክ ቀንና ሌሊት በትጋት ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ እየተጠባበቁ ያሉት የዚህኑ ተስፋ ፍጻሜ ነው። ንጉሥ ሆይ፣ አይሁዶች የከሰሱኝ በዚህ ተስፋ ምክንያት ነው።+
8 “አምላክ ሙታንን የሚያስነሳ መሆኑ ሊታመን የማይችል ነገር እንደሆነ አድርጋችሁ የምታስቡት* ለምንድን ነው?
9 እኔ ራሴ የናዝሬቱ ኢየሱስን ስም በተቻለኝ መጠን መቃወም እንዳለብኝ አምን ነበር።
10 ደግሞም በኢየሩሳሌም ያደረግኩት ይህንኑ ነው፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ+ ብዙ ቅዱሳንን ወህኒ ቤት አስገብቻለሁ፤+ እንዲገደሉም የድጋፍ ድምፅ ሰጥቻለሁ።
11 ብዙ ጊዜም በየምኩራቡ እነሱን እየቀጣሁ እምነታቸውን በይፋ እንዲክዱ ለማስገደድ ሞክሬአለሁ፤ በእነሱ ላይ እጅግ ተቆጥቼ በሌሎች ከተሞች ያሉትን እንኳ ሳይቀር እስከ ማሳደድ ደርሻለሁ።
12 “ይህን እያከናወንኩ በነበረበት ወቅት ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ተልእኮ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ እየተጓዝኩ ሳለ
13 ንጉሥ ሆይ፣ እኩለ ቀን ሲሆን በመንገድ ላይ ከፀሐይ ብርሃን የበለጠ ድምቀት ያለው ከሰማይ የመጣ ብርሃን በእኔና አብረውኝ በሚጓዙት ሰዎች ዙሪያ ሲያበራ አየሁ።+
14 ሁላችንም መሬት ላይ በወደቅን ጊዜ አንድ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ‘ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን* መቃወምህን ከቀጠልክ ለአንተው የባሰ ይሆንብሃል’ ሲለኝ ሰማሁ።
15 እኔም ‘ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?’ አልኩ። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ።
16 ይሁንና አሁን ተነስተህ በእግርህ ቁም። የተገለጥኩልህ እኔን በተመለከተ ስላየኸው ነገርና ወደፊት ስለማሳይህ ነገር አገልጋይና ምሥክር እንድትሆን አንተን ለመምረጥ ነው።+
17 ወደ እነሱ ከምልክህ ከዚህ ሕዝብና ከአሕዛብ እታደግሃለሁ፤+
18 የምልክህም የኃጢአት ይቅርታ ያገኙና+ በእኔ ላይ ባላቸው እምነት አማካኝነት በተቀደሱት መካከል ርስት ይቀበሉ ዘንድ ዓይናቸውን እንድትገልጥ+ እንዲሁም ከጨለማ+ ወደ ብርሃን፣+ ከሰይጣን ሥልጣንም+ ወደ አምላክ እንድትመልሳቸው ነው።’
19 “በመሆኑም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ ከሰማይ ለተገለጠልኝ ራእይ አልታዘዝም አላልኩም፤
20 ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ በደማስቆ+ ላሉ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና+ በመላው የይሁዳ አገር ሁሉ ለሚገኙ ከዚያም ለአሕዛብ ንስሐ እንዲገቡና ለንስሐ የሚገባ ሥራ+ በመሥራት ወደ አምላክ እንዲመለሱ የሚያሳስበውን መልእክት ማዳረሴን ቀጠልኩ።
21 አይሁዳውያኑ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የያዙኝና ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚህ የተነሳ ነው።+
22 ይሁን እንጂ ከአምላክ እርዳታ በማግኘቴ እስከዚህ ቀን ድረስ ለትንሹም ሆነ ለትልቁ መመሥከሬን ቀጥያለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይፈጸማል ብለው ከተናገሩት በስተቀር ምንም የተናገርኩት ነገር የለም፤+
23 እነሱም የተናገሩት ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና+ ከሙታን የመጀመሪያ ሆኖ በመነሳት+ ለዚህ ሕዝብም ሆነ ለአሕዛብ ስለ ብርሃን እንደሚያውጅ ነው።”+
24 ጳውሎስ የመከላከያ መልሱን እየሰጠ ሳለ ፊስጦስ ጮክ ብሎ “ጳውሎስ አሁንስ አእምሮህን ልትስት ነው! ብዙ መማር አእምሮህን እያሳተህ ነው!” አለ።
25 ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፣ አእምሮዬን እየሳትኩ አይደለም፤ እኔ እየተናገርኩ ያለሁት እውነተኛ እንዲሁም ከጤናማ አእምሮ የሚመነጭ ቃል ነው።
26 እንደ እውነቱ ከሆነ በነፃነት እያናገርኩት ያለሁት ንጉሥ ስለ እነዚህ ነገሮች በሚገባ ያውቃል፤ እነዚህ ነገሮች በድብቅ የተፈጸሙ ባለመሆናቸው አንዳቸውም ቢሆኑ ከእሱ የተሰወሩ እንዳልሆኑ እርግጠኛ ነኝ።+
27 ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ በነቢያት ታምናለህ? እንደምታምን አውቃለሁ።”
28 አግሪጳም ጳውሎስን “በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳምነህ ክርስቲያን ልታደርገኝ እኮ ምንም አልቀረህም” አለው።
29 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ እየሰሙኝ ያሉት ሁሉ ከእስራቴ በስተቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ አምላክን እለምናለሁ” አለ።
30 ከዚያም ንጉሡ ተነሳ፤ አገረ ገዢው፣ በርኒቄና አብረዋቸው ተቀምጠው የነበሩት ሰዎችም ተነሱ።
31 እየወጡ ሳሉም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ ምንም ነገር አላደረገም” ተባባሉ።+
32 ከዚያም አግሪጳ ፊስጦስን “ይህ ሰው ወደ ቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ ሊፈታ ይችል ነበር” አለው።+