የሐዋርያት ሥራ 3:1-26

  • ጴጥሮስ ሽባ የሆነን ለማኝ ፈወሰ (1-10)

  • ጴጥሮስ ‘በሰለሞን መተላለፊያ’ ያቀረበው ንግግር (11-26)

    • “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” (21)

    • እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ (22)

3  አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ሰዓት ይኸውም ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደሱ እየወጡ ነበር፤ 2  ሰዎችም ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ተሸክመው በማምጣት ወደ ቤተ መቅደሱ ከሚገባው ሰው ምጽዋት* እንዲለምን “ውብ” በተባለው የቤተ መቅደሱ በር አጠገብ በየዕለቱ ያስቀምጡት ነበር። 3  ይህ ሰው ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሊገቡ ሲሉ አያቸውና ምጽዋት እንዲሰጡት ይለምናቸው ጀመር። 4  ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን ትኩር ብለው አዩት፤ ከዚያም ጴጥሮስ “ወደ እኛ ተመልከት” አለው። 5  ሰውየውም የሆነ ነገር ሊሰጡኝ ነው ብሎ በማሰብ ትኩር ብሎ ተመለከታቸው። 6  ይሁንና ጴጥሮስ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ። በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነስና ተራመድ!” አለው።+ 7  ከዚያም ቀኝ እጁን ይዞ አስነሳው።+ ወዲያውም እግሩና ቁርጭምጭሚቱ ጠነከረ፤+ 8  ዘሎም ተነሳ፤+ መራመድም ጀመረ፤ ደግሞም እየተራመደና እየዘለለ እንዲሁም አምላክን እያወደሰ ከእነሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ። 9  ሰዎቹም ሁሉ ሲራመድና አምላክን ሲያወድስ አዩት። 10  ይህ ሰው “ውብ በር” በተባለው የቤተ መቅደሱ መግቢያ አጠገብ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው ሰው መሆኑን ስላወቁ በእሱ ላይ በተፈጸመው ሁኔታ እጅግ ተገረሙ፤+ በአድናቆትም ተዋጡ። 11  ሰውየው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዟቸው ሳለ በዚያ የነበሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ ተደንቀው እነሱ ወዳሉበት “የሰለሞን መተላለፊያ”+ ወደሚባለው ስፍራ ግር ብለው እየሮጡ መጡ። 12  ጴጥሮስ ይህን ባየ ጊዜ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? ደግሞስ በእኛ ኃይል ወይም እኛ ለአምላክ ያደርን በመሆናችን የተነሳ ይህን ሰው እንዲራመድ ያስቻልነው ይመስል ለምን ትኩር ብላችሁ ታዩናላችሁ? 13  የአባቶቻችን አምላክ ይኸውም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ+ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና+ ጲላጦስ ሊፈታው ወስኖ የነበረ ቢሆንም በእሱ ፊት የካዳችሁትን አገልጋዩን ኢየሱስን አከበረው።+ 14  አዎ፣ እናንተ ይህን ቅዱስና ጻድቅ ሰው ክዳችሁ ነፍሰ ገዳይ የሆነን ሰው እንዲፈታላችሁ ጠየቃችሁ፤+ 15  በአንጻሩ ግን የሕይወትን “ዋና ወኪል”*+ ገደላችሁት። አምላክ ግን ከሞት አስነሳው፤ እኛም ለዚህ ነገር ምሥክሮች ነን።+ 16  የኢየሱስ ስምና እኛ በስሙ ላይ ያለን እምነት ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን ሰው አጠነከረው። በኢየሱስ አማካኝነት ያገኘነው እምነት ይህ ሰው በሁላችሁም ፊት ፍጹም ጤናማ እንዲሆን አደረገው። 17  አሁንም ወንድሞች፣ ገዢዎቻችሁ እንዳደረጉት ሁሉ እናንተም ይህን ያደረጋችሁት ባለማወቅ እንደሆነ አውቃለሁ።+ 18  ይሁንና አምላክ፣ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ አስቀድሞ ያሳወቀው ነገር በዚህ መንገድ እንዲፈጸም አድርጓል።+ 19  “ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ+ ንስሐ ግቡ፣+ ተመለሱም፤+ ከይሖዋም ዘንድ* የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤ 20  እንዲሁም ለእናንተ የሾመውን ክርስቶስን ይኸውም ኢየሱስን ይልክላችኋል። 21  እሱም አምላክ በጥንቶቹ ቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገራቸው ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ በሰማይ መቆየት* ይገባዋል። 22  ደግሞም ሙሴ እንዲህ ብሏል፦ ‘አምላካችሁ ይሖዋ* ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳላችኋል።+ እሱ የሚነግራችሁንም ነገር ሁሉ ስሙ።+ 23  ያንን ነቢይ የማይሰማ ሰው ሁሉ* ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል።’+ 24  ከሳሙኤል ጀምሮ በተከታታይ የተነሱት ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ቀናት በግልጽ ተናግረዋል።+ 25  እናንተ የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ እንዲሁም አምላክ ለአብርሃም ‘የምድር ቤተሰቦች ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ይባረካሉ’+ ብሎ ከአባቶቻችሁ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ወራሾች ናችሁ።+ 26  አምላክ አገልጋዩን ካስነሳ በኋላ እያንዳንዳችሁን ከክፉ ሥራችሁ በመመለስ ይባርካችሁ ዘንድ በመጀመሪያ ወደ እናንተ ላከው።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የምሕረት ስጦታ።” ወይም “ለድሆች የሚሰጥ ስጦታ።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ሕይወት እንዲሰጥ የተሾመውን መሪ።”
ቃል በቃል “ከይሖዋም ፊት።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ሰማይ በውስጡ ሊይዘው።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ነፍስ ሁሉ።”