የዮሐንስ ወንጌል 15:1-27

  • የእውነተኛው የወይን ተክል ምሳሌ (1-10)

  • የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር እንድናሳይ የተሰጠ ትእዛዝ (11-17)

    • ‘ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም’ (13)

  • ዓለም የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ይጠላል (18-27)

15  “እኔ እውነተኛው የወይን ተክል ነኝ፤ አትክልተኛው ደግሞ አባቴ ነው። 2  በእኔ ላይ ያለውን፣ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቆርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ደግሞ ይበልጥ እንዲያፈራ ያጠራዋል።*+ 3  እናንተ ከነገርኳችሁ ቃል የተነሳ አሁን ንጹሐን ናችሁ።+ 4  ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ኑሩ፤ እኔም ከእናንተ ጋር ያለኝን አንድነት ጠብቄ እኖራለሁ። ቅርንጫፉ ከወይኑ ተክል ጋር ተጣብቆ ካልኖረ በራሱ ፍሬ ማፍራት አይችልም፤ እናንተም ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ካልኖራችሁ+ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም። 5  እኔ የወይኑ ተክል ነኝ፤ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎቹ ናችሁ። ማንኛውም ሰው ከእኔ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ከኖረና እኔም ከእሱ ጋር አንድ ሆኜ ከኖርኩ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤+ እናንተ ከእኔ ተለይታችሁ ምንም ነገር ልታደርጉ አትችሉምና። 6  አንድ ሰው ከእኔ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ካልኖረ እንደ ቅርንጫፍ ይጣልና ይደርቃል። ሰዎችም እንዲህ ያሉትን ቅርንጫፎች ሰብስበው እሳት ውስጥ በመጣል ያቃጥሏቸዋል። 7  እናንተ ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ከጠበቃችሁና ቃሌ በልባችሁ ከኖረ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ብትጠይቁ ይፈጸምላችኋል።+ 8  ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ መሆናችሁን ብታሳዩ በዚህ አባቴ ይከበራል።+ 9  አብ እኔን እንደወደደኝ፣+ እኔም እናንተን እንዲሁ ወድጃችኋለሁ። እናንተም በፍቅሬ ኑሩ። 10  እኔ የአብን ትእዛዛት ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር እናንተም ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። 11  “እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ እኔ ያገኘሁትን ደስታ እንድታገኙና የእናንተም ደስታ የተሟላ እንዲሆን ነው።+ 12  ትእዛዜ ይህ ነው፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።+ 13  ሕይወቱን* ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።+ 14  የማዛችሁን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ።+ 15  ከእንግዲህ ባሪያዎች ብዬ አልጠራችሁም፤ ምክንያቱም ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን ነገር አያውቅም። እኔ ግን ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ። 16  እኔ መረጥኳችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ ሄዳችሁ ፍሬ እንድታፈሩና ፍሬያችሁ ጸንቶ እንዲኖር ሾሜያችኋለሁ፤ የመረጥኳችሁ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ ነው።+ 17  “እነዚህን ነገሮች የማዛችሁ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው።+ 18  ዓለም ቢጠላችሁ፣ እናንተን ከመጥላቱ በፊት እኔን እንደጠላኝ ታውቃላችሁ።+ 19  የዓለም ክፍል ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን በወደደ ነበር። አሁን ግን እኔ ከዓለም መረጥኳችሁ እንጂ የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ+ ከዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላችኋል።+ 20  ባሪያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኳችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል፤+ ቃሌን ጠብቀው ከሆነ ደግሞ የእናንተንም ቃል ይጠብቃሉ። 21  ሆኖም የላከኝን ስለማያውቁት በስሜ ምክንያት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደርጉባችኋል።+ 22  መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር።+ አሁን ግን ለኃጢአታቸው የሚያቀርቡት ሰበብ የለም።+ 23  እኔን የሚጠላ ሁሉ አባቴንም ይጠላል።+ 24  ሌላ ማንም ያላደረገውን ነገር በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤+ አሁን ግን እኔን አይተዋል እንዲሁም እኔንም ሆነ አባቴን ጠልተዋል። 25  ይሁን እንጂ ይህ የሆነው ‘ያለምክንያት ጠሉኝ’+ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው። 26  ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ከአብ የሚወጣው ረዳት* ይኸውም የእውነት መንፈስ+ ሲመጣ እሱ ስለ እኔ ይመሠክራል፤+ 27  እናንተም ደግሞ ትመሠክራላችሁ፤+ ምክንያቱም ከመጀመሪያ አንስቶ ከእኔ ጋር ነበራችሁ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ይገርዘዋል።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “አጽናኝ።”