የዮሐንስ ወንጌል 2:1-25
2 በሦስተኛውም ቀን በገሊላ በምትገኘው በቃና የሠርግ ድግስ ነበር፤ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች።
2 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ ተጠርተው ነበር።
3 የወይን ጠጁ እያለቀ ሲሄድ የኢየሱስ እናት “የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” አለችው።
4 ኢየሱስ ግን “አንቺ ሴት፣ ይህ ጉዳይ እኔንና አንቺን ምን ይመለከተናል?* ሰዓቴ ገና አልደረሰም” አላት።
5 እናቱም በዚያ የሚያገለግሉትን ሰዎች “የሚላችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው።
6 የአይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት በሚያዘው መሠረት+ እያንዳንዳቸው ሁለት ወይም ሦስት የፈሳሽ መለኪያዎች* የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት የውኃ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር።
7 ኢየሱስም “ጋኖቹን ውኃ ሙሏቸው” አላቸው። እነሱም እስከ አፋቸው ድረስ ሞሏቸው።
8 ከዚያም “አሁን ቀድታችሁ ለድግሱ አሳዳሪ ስጡት” አላቸው። እነሱም ወስደው ሰጡት።
9 የድግሱ አሳዳሪም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውኃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደመጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ
10 እንዲህ አለው፦ “ሰው ሁሉ በቅድሚያ ጥሩውን የወይን ጠጅ ያቀርብና ሰዎቹ ከሰከሩ በኋላ መናኛውን ያቀርባል። አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስካሁን ድረስ አስቀምጠሃል።”
11 ኢየሱስ ከምልክቶቹ የመጀመሪያ የሆነውን ይህን ተአምር በገሊላ በምትገኘው በቃና ፈጸመ፤ ክብሩንም ገለጠ፤+ ደቀ መዛሙርቱም በእሱ አመኑ።
12 ከዚህ በኋላ እሱና እናቱ እንዲሁም ወንድሞቹና+ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም+ ወረዱ፤ ሆኖም በዚያ ብዙ ቀን አልቆዩም።
13 በዚህ ጊዜ የአይሁዳውያን ፋሲካ*+ ቀርቦ ነበር፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
14 በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከብት፣ በግና ርግብ+ የሚሸጡ ሰዎችን እንዲሁም በዚያ የተቀመጡ ገንዘብ መንዛሪዎችን አገኘ።
15 በዚህ ጊዜ የገመድ ጅራፍ ሠርቶ ሁሉንም ከበጎቻቸውና ከከብቶቻቸው ጋር አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ሳንቲሞች በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ።+
16 ርግብ ሻጮቹንም “እነዚህን ከዚህ አስወጡ! የአባቴን ቤት የንግድ ቤት* ማድረጋችሁ ይብቃ!” አላቸው።+
17 ደቀ መዛሙርቱም “ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት ይበላኛል”+ ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው።
18 በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን መልሰው “እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት።+
19 ኢየሱስም መልሶ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን ውስጥ አነሳዋለሁ” አላቸው።+
20 አይሁዳውያኑም “ቤተ መቅደሱን ለመገንባት 46 ዓመት ፈጅቷል፤ ታዲያ አንተ በሦስት ቀን ታነሳዋለህ?” አሉት።
21 እሱ ግን ቤተ መቅደስ ሲል ስለ ራሱ ሰውነት መናገሩ ነበር።+
22 ከሙታን በተነሳ ጊዜም፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ደጋግሞ ይናገር እንደነበር አስታወሱ፤+ ቅዱሳን መጻሕፍትንና ኢየሱስ የተናገረውንም ቃል አመኑ።
23 ይሁንና በፋሲካ በዓል፣ በኢየሩሳሌም በነበረበት ጊዜ ብዙ ሰዎች የሚያከናውናቸውን ተአምራዊ ምልክቶች ሲያዩ በስሙ አመኑ።
24 ኢየሱስ ግን ሁሉንም ያውቃቸው ስለነበር አይተማመንባቸውም ነበር፤
25 እንዲሁም በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለነበር ማንም ስለ ሰው እንዲመሠክርለት አላስፈለገውም።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “አንቺ ሴት፣ ለእኔና ለአንቺ ምንድን ነው?” ይህ በአንድ ጉዳይ አለመስማማትን የሚያሳይ ፈሊጣዊ አነጋገር ነው። “አንቺ ሴት” የሚለው አገላለጽ አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ አይደለም።
^ ወይም “የማለፍ በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ገበያ።”