የዮሐንስ ወንጌል 6:1-71
6 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የገሊላን ማለትም የጥብርያዶስን ባሕር* አቋርጦ ወደ ማዶ ተሻገረ።+
2 ብዙ ሰዎችም ኢየሱስ የታመሙትን በመፈወስ+ የፈጸማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች ስላዩ ተከተሉት።+
3 ስለዚህ ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ተቀመጠ።
4 በዚያን ጊዜ የአይሁዳውያን በዓል የሆነው ፋሲካ+ ተቃርቦ ነበር።
5 ኢየሱስም ቀና ብሎ ብዙ ሕዝብ ወደ እሱ እየመጣ እንዳለ ሲመለከት ፊልጶስን “እነዚህ ሰዎች የሚበሉት ዳቦ ከየት ብንገዛ ይሻላል?” አለው።+
6 ሆኖም ይህን ያለው ሊፈትነው ብሎ እንጂ ለማድረግ ያሰበውን ያውቅ ነበር።
7 ፊልጶስም “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ እንዲደርሰው ለማድረግ እንኳ የ200 ዲናር* ዳቦ አይበቃም” ሲል መለሰለት።
8 ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለው፦
9 “አምስት የገብስ ዳቦና ሁለት ትናንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ትንሽ ልጅ እዚህ አለ። ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይበቃል?”+
10 ኢየሱስም “ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ” አለ። በስፍራው ብዙ ሣር ስለነበር ሰዎቹ በዚያ ተቀመጡ፤ ወንዶቹም 5,000 ያህል ነበሩ።+
11 ኢየሱስ ዳቦዎቹን ወስዶ ካመሰገነ በኋላ በዚያ ለተቀመጡት ሰዎች አከፋፈለ፤ ትናንሾቹን ዓሣዎችም ልክ እንደዚሁ አደለ፤ እነሱም የሚፈልጉትን ያህል ወሰዱ።
12 በልተው ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ምንም እንዳይባክን የተረፈውን ቁርስራሽ ሁሉ ሰብስቡ” አላቸው።
13 ስለዚህ ከአምስቱ የገብስ ዳቦ ሰዎቹ በልተው የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ።
14 ሰዎቹም ኢየሱስ የፈጸመውን ተአምራዊ ምልክት ባዩ ጊዜ “ወደ ዓለም እንደሚመጣ ትንቢት የተነገረለት ነቢይ በእርግጥ ይህ ነው” አሉ።+
15 ከዚያም ኢየሱስ ሰዎቹ መጥተው ሊይዙትና ሊያነግሡት እንዳሰቡ ስላወቀ ብቻውን ዳግመኛ ወደ ተራራ ገለል አለ።+
16 በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ወረዱ፤+
17 በጀልባም ተሳፍረው ባሕሩን በማቋረጥ ወደ ቅፍርናሆም ለመሻገር ተነሱ። በዚያን ሰዓት ጨልሞ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ገና ወደ እነሱ አልመጣም ነበር።+
18 በተጨማሪም ኃይለኛ ነፋስ ይነፍስ ስለነበረ ባሕሩ ይናወጥ ጀመር።+
19 ይሁን እንጂ አምስት ወይም ስድስት ኪሎ ሜትር ገደማ* እንደቀዘፉ ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ ጀልባዋ ሲቃረብ ተመልክተው ፈሩ።
20 እሱ ግን “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው።+
21 ከዚያም ወዲያው ጀልባዋ ላይ አሳፈሩት፤ ጀልባዋም ሊሄዱ ወዳሰቡበት ቦታ በፍጥነት ደረሰች።+
22 በማግስቱም፣ በባሕሩ ማዶ የቀሩት ሰዎች በዚያ ምንም ጀልባ እንዳልነበረ አስተዋሉ። አንዲት ትንሽ ጀልባ በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስ ግን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚህች ጀልባ አልተሳፈረም። ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ሄደው ነበር።
23 ሆኖም ከጥብርያዶስ የተነሱ ጀልባዎች፣ ሕዝቡ ጌታ የባረከውን ዳቦ ወደበሉበት አካባቢ መጡ።
24 ሕዝቡ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አለመኖራቸውን ባወቁ ጊዜ በጀልባዎቻቸው ተሳፍረው ኢየሱስን ፍለጋ ወደ ቅፍርናሆም መጡ።
25 ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ “ረቢ፣+ መቼ ወደዚህ መጣህ?” አሉት።
26 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የምትፈልጉኝ ተአምራዊ ምልክት ስላያችሁ ሳይሆን ዳቦ ስለበላችሁና ስለጠገባችሁ ነው።+
27 ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት+ ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ፤ ምክንያቱም አብ ይኸውም አምላክ ራሱ እሱን እንደተቀበለው አሳይቷል።”*+
28 እነሱም “ታዲያ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ሥራ ለመሥራት ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉት።
29 ኢየሱስም መልሶ “አምላክ የሚቀበለው ሥራማ እሱ በላከው ሰው ማመን ነው” አላቸው።+
30 በዚህ ጊዜ እንዲህ አሉት፦ “ታዲያ አይተን እንድናምንብህ ምን ተአምራዊ ምልክት ትፈጽማለህ?+ ምን ነገርስ ትሠራለህ?
31 ‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ ምግብ ሰጣቸው’+ ተብሎ በተጻፈው መሠረት አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ።”+
32 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ከሰማይ የወረደውን ምግብ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ አባቴ ግን እውነተኛውን ምግብ ከሰማይ ይሰጣችኋል።
33 ምክንያቱም አምላክ የሚሰጠው ምግብ ከሰማይ የሚወርድና ለዓለም ሕይወት የሚያስገኝ ነው።”
34 እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ይህን ምግብ ሁልጊዜ ስጠን” አሉት።
35 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ። ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ፈጽሞ አይራብም፤ እንዲሁም በእኔ የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አይጠማም።+
36 ነገር ግን “አይታችሁኝም እንኳ አታምኑም” ብያችሁ ነበር።+
37 አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ፈጽሞ አላባርረውም፤+
38 ከሰማይ የመጣሁት+ የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነውና።+
39 የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንዱም እንኳ እንዳይጠፋብኝና በመጨረሻው ቀን ሁሉንም ከሞት እንዳስነሳቸው+ ነው።
40 ምክንያቱም የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያውቅና በእሱ የሚያምን* ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤+ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ።”+
41 ከዚያም አይሁዳውያን “ከሰማይ የወረደው ምግብ እኔ ነኝ”+ በማለቱ በኢየሱስ ላይ ያጉረመርሙ ጀመር።
42 ደግሞም “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለም? አባቱንና እናቱንስ እናውቃቸው የለም እንዴ?+ ታዲያ እንዴት ‘ከሰማይ ወረድኩ’ ይላል?” አሉ።
43 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ።
44 የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም፤+ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ።+
45 ነቢያት በጻፏቸው ጽሑፎች ላይ ‘ሁሉም ከይሖዋ* የተማሩ ይሆናሉ’+ ተብሎ ተጽፏል። ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።
46 ከአምላክ ዘንድ ከመጣው በስተቀር አብን ያየ አንድም ሰው የለም፤+ እሱ አብን አይቶታል።+
47 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው።+
48 “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ።+
49 አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ።+
50 ከሰማይ የወረደውን ምግብ የሚበላ ሁሉ ግን አይሞትም።
51 ከሰማይ የወረደው ሕያው ምግብ እኔ ነኝ። ከዚህ ምግብ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል፤ ምግቡ ደግሞ ለዓለም ሕይወት ስል የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”+
52 አይሁዳውያንም “ይህ ሰው እንዴት ሥጋውን እንድንበላ ሊሰጠን ይችላል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር።
53 በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።+
54 ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በመጨረሻውም ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ፤+
55 ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።
56 ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ ከእኔ ጋር አንድነት ይኖረዋል፤ እኔም ከእሱ ጋር አንድነት ይኖረኛል።+
57 ሕያው የሆነው አብ እንደላከኝና እኔም ከእሱ የተነሳ በሕይወት እንደምኖር ሁሉ የእኔን ሥጋ የሚበላም ከእኔ የተነሳ በሕይወት ይኖራል።+
58 ከሰማይ የወረደው ምግብ ይህ ነው። ይህም አባቶቻችሁ በበሉበት ጊዜ እንደነበረው አይደለም፤ እነሱ ቢበሉም እንኳ ሞተዋል። ይህን ምግብ የሚበላ ሁሉ ግን ለዘላለም ይኖራል።”+
59 ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም በምኩራብ* እያስተማረ ሳለ ነበር።
60 ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ይህን ሲሰሙ “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ።
61 ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ እያጉረመረሙ እንዳሉ ስለገባው እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ያሰናክላችኋል?
62 ታዲያ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው?+
63 ሕይወትን የሚሰጠው መንፈስ ነው፤+ ሥጋ ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው።+
64 ነገር ግን ከእናንተ መካከል የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ያለው የማያምኑት እነማን እንደሆኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ከመጀመሪያው ያውቅ ስለነበረ ነው።+
65 ከዚያም “አብ ካልፈቀደለት በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም ያልኳችሁ ለዚህ ነው” አላቸው።+
66 ከዚህም የተነሳ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ትተውት ወደነበረው ነገር ተመለሱ፤+ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እሱን መከተላቸውን አቆሙ።
67 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን “እናንተም መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
68 ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን?+ አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ።+
69 አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ እንደሆንክ አምነናል፤ ደግሞም አውቀናል።”+
70 ኢየሱስም መልሶ “አሥራ ሁለታችሁንም የመረጥኳችሁ እኔ አይደለሁም?+ ይሁንና ከመካከላችሁ አንዱ ስም አጥፊ* ነው” አላቸው።+
71 ይህን ሲል የአስቆሮቱ ስምዖን ልጅ ስለሆነው ስለ ይሁዳ መናገሩ ነበር፤ ምክንያቱም ይሁዳ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆንም አሳልፎ የሚሰጠው እሱ ነበር።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “የማረጋገጫ ማኅተሙን አትሟል።”
^ ወይም “በእሱ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ።”
^ “ሕዝብ በተሰበሰበበት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “ዲያብሎስ።”