ዮናስ 1:1-17
1 የይሖዋ ቃል ወደ አሚታይ ልጅ ወደ ዮናስ*+ እንዲህ ሲል መጣ፦
2 “ተነስተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ+ ሂድና በእሷ ላይ የፍርድ መልእክት አውጅ፤ ክፋታቸውን አስተውያለሁና።”
3 ዮናስ ግን ከይሖዋ ፊት ኮብልሎ ወደ ተርሴስ ለመሄድ ተነሳ፤ ወደ ኢዮጴም ወረደ፤ ከዚያም ወደ ተርሴስ የምትሄድ መርከብ አገኘ። ከይሖዋም ፊት ሸሽቶ፣ በመርከቡ ውስጥ ከነበሩት ጋር ወደ ተርሴስ ለመሄድ የጉዞውን ዋጋ ከፍሎ ተሳፈረ።
4 ከዚያም ይሖዋ በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ነፋስ አመጣ፤ ከባድ ማዕበል ስለተነሳ መርከቧ ልትሰበር ተቃረበች።
5 መርከበኞቹ እጅግ ከመፍራታቸው የተነሳ እርዳታ ለማግኘት እያንዳንዳቸው ወደየአምላካቸው ይጮኹ ጀመር። የመርከቧንም ክብደት ለመቀነስ በውስጧ የነበሩትን ዕቃዎች ወደ ባሕሩ መጣል ጀመሩ።+ ዮናስ ግን ወደ መርከቧ* ውስጠኛ ክፍል ወርዶ ተኝቶ ነበር፤ ጭልጥ ያለ እንቅልፍም ወስዶት ነበር።
6 የመርከቧ አዛዥ ወደ እሱ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ “እንዴት ትተኛለህ? ተነስተህ ወደ አምላክህ ጩኽ! ምናልባት እውነተኛው አምላክ ለእኛ አስቦ ከጥፋት ያድነን ይሆናል።”+
7 ከዚያም እርስ በርሳቸው “ይህ መከራ የደረሰብን በማን ምክንያት እንደሆነ ማወቅ እንድንችል፣ ኑ ዕጣ እንጣጣል”+ ተባባሉ። በመሆኑም ዕጣ ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ።+
8 እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ይህ መከራ የደረሰብን በማን ምክንያት እንደሆነ እባክህ ንገረን። ሥራህ ምንድን ነው? የመጣኸው ከየት ነው? አገርህስ የት ነው? ከየትኛውስ ሕዝብ ነህ?”
9 እሱም መልሶ “እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማያትን አምላክ ይሖዋን የምፈራ* ሰው ነኝ” አላቸው።
10 በዚህ ጊዜ ሰዎቹ የባሰ ፈሩ፤ “ያደረግከው ነገር ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። (ሰዎቹ ዮናስ ነግሯቸው ስለነበር ከይሖዋ ፊት እየሸሸ እንዳለ አወቁ።)
11 የባሕሩ ማዕበል እያየለ በመሄዱ “ባሕሩ ጸጥ እንዲልልን በአንተ ላይ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉት።
12 እሱም “አንስታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል፤ ይህ ከባድ ማዕበል የመጣባችሁ በእኔ የተነሳ መሆኑን አውቃለሁና” በማለት መለሰላቸው።
13 ሰዎቹ ግን መርከቧን ወደ የብስ ለመመለስ በኃይል ቀዘፉ፤* ይሁንና ማዕበሉ ይበልጥ እያየለባቸው ስለሄደ ሊሳካላቸው አልቻለም።
14 ከዚያም ወደ ይሖዋ በመጮኽ እንዲህ አሉ፦ “እንግዲህ ይሖዋ ሆይ፣ በዚህ ሰው ምክንያት* እንዳንጠፋ እንለምንሃለን! ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ደስ እንዳሰኘህ ስላደረግክ ለንጹሕ ሰው ደም ተጠያቂ አታድርገን!”
15 ከዚያም ዮናስን አንስተው ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም መናወጡን አቆመ።
16 በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ይሖዋን እጅግ ፈሩ፤+ ለይሖዋም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ስእለትም ተሳሉ።
17 ይሖዋም ዮናስን እንዲውጠው አንድ ትልቅ ዓሣ ላከ፤ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣው ሆድ ውስጥ ቆየ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ስሙ “ርግብ” የሚል ትርጉም አለው።
^ ወይም “ከመርከቧ ወለል በታች ወደሚገኘው።”
^ ወይም “የማመልክ።”
^ ወይም “ማዕበሉን ሰንጥቀው ወደ የብስ ለመመለስ ጥረት አደረጉ።”
^ ወይም “በዚህ ሰው ነፍስ ምክንያት።”