ዳንኤል 7:1-28
7 የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛር+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በአልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልምና ራእዮች አየ።+ ከዚያም ያየውን ሕልም ጻፈ፤+ ጉዳዩንም በዝርዝር አሰፈረ።
2 ዳንኤልም እንዲህ ሲል ገለጸ፦
“በሌሊት ባየኋቸው ራእዮች ላይ አራቱ የሰማያት ነፋሳት የተንጣለለውን ባሕር ሲያናውጡት ተመለከትኩ።+
3 አራት ግዙፍ አራዊትም+ ከባሕር ውስጥ ወጡ፤ እያንዳንዳቸውም አንዱ ከሌላው የተለዩ ነበሩ።
4 “የመጀመሪያው አንበሳ ይመስል ነበር፤+ የንስር ክንፎችም ነበሩት።+ እኔም እየተመለከትኩ ሳለ ክንፎቹ ተነቃቀሉ፤ ከምድር እንዲነሳና ልክ እንደ ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆም ተደረገ፤ የሰውም ልብ ተሰጠው።
5 “እነሆ፣ ሁለተኛው አውሬ ድብ ይመስል ነበር።+ በአንድ ጎኑም ተነስቶ ነበር፤ በአፉም ውስጥ በጥርሶቹ መካከል ሦስት የጎድን አጥንቶች ይዞ ነበር፤ ‘ተነስተህ ብዙ ሥጋ ብላ’ ተባለ።+
6 “ከዚህም በኋላ አየሁ፤ እነሆ ነብር የሚመስል ሌላ አውሬ ነበር፤+ ሆኖም ጀርባው ላይ አራት የወፍ ክንፎች ነበሩት። አውሬውም አራት ራሶች ነበሩት፤+ የመግዛት ሥልጣንም ተሰጠው።
7 “ከዚህ በኋላ በሌሊት ባየኋቸው ራእዮች ላይ የሚያስፈራ፣ የሚያስደነግጥና ለየት ያለ ጥንካሬ ያለው አራተኛ አውሬ ተመለከትኩ፤ ትላልቅ የብረት ጥርሶችም ነበሩት። ይበላና ያደቅ እንዲሁም የቀረውን በእግሮቹ ይረጋግጥ ነበር።+ ከእሱ በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየ ሲሆን አሥር ቀንዶች ነበሩት።
8 ቀንዶቹን እየተመለከትኩ ሳለ፣ እነሆ ሌላ ትንሽ ቀንድ በመካከላቸው ወጣ፤+ ከመጀመሪያዎቹ ቀንዶች መካከል ሦስቱ በፊቱ ተነቃቀሉ። እነሆ፣ በዚህ ቀንድ ላይ የሰው ዓይኖች የሚመስሉ ዓይኖች ነበሩ፤ በእብሪት* የሚናገርም አፍ ነበረው።+
9 “እኔም እየተመለከትኩ ሳለ ዙፋኖች ተዘጋጁ፤ ከዘመናት በፊት የነበረውም+ ተቀመጠ።+ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ፣+ የራሱም ፀጉር እንደጠራ ሱፍ ነበር። ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣ መንኮራኩሮቹም የሚነድ እሳት ነበሩ።+
10 ከፊቱ የእሳት ጅረት ይፈልቅና ይፈስ ነበር።+ ሺህ ጊዜ ሺዎች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍም* በፊቱ ቆመው ነበር።+ ችሎቱ+ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ።
11 “በዚህ ጊዜ ቀንዱ ከሚናገረው የእብሪት* ቃል የተነሳ መመልከቴን ቀጠልኩ፤+ እኔም እየተመለከትኩ ሳለ አውሬው ተገደለ፤ አካሉም ወደሚንበለበል እሳት ተጥሎ እንዲጠፋ ተደረገ።
12 የቀሩት አራዊት+ ግን የገዢነት ሥልጣናቸውን ተቀሙ፤ ሆኖም ለተወሰነ ጊዜና ወቅት ዕድሜያቸው ተራዘመ።
13 “በሌሊት የተገለጡልኝን ራእዮች ማየቴን ቀጠልኩ፤ እነሆ የሰው ልጅ+ የሚመስል ከሰማያት ደመና ጋር መጣ፤ ከዘመናት በፊት ወደነበረውም+ እንዲገባ ተፈቀደለት፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።
14 ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያገለግሉት የገዢነት ሥልጣን፣+ ክብርና+ መንግሥት ተሰጠው።+ የገዢነት ሥልጣኑ የማያልፍና ዘላለማዊ፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።+
15 “እኔ ዳንኤል ያየኋቸው ራእዮች ፍርሃት ስላሳደሩብኝ በውስጤ መንፈሴ ታወከ።+
16 ከቆሙት መካከል ወደ አንዱ ቀርቤ የዚህ ሁሉ ትክክለኛ ትርጉም ምን እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም መለሰልኝ፤ ደግሞም የእነዚህን ነገሮች ትርጉም ገለጸልኝ።
17 “‘እነዚህ አራት ግዙፍ አራዊት+ ከምድር የሚነሱ አራት ነገሥታት ናቸው።+
18 ይሁንና ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን፣+ መንግሥቱን ይቀበላሉ፤+ መንግሥቱን ለዘላለም፣ አዎ ለዘላለም ዓለም ይወርሳሉ።’+
19 “ከዚያም ከሌሎቹ ሁሉ የተለየ ስለሆነው ስለ አራተኛው አውሬ ይበልጥ ማወቅ ፈለግኩ፤ የብረት ጥርሶችና የመዳብ ጥፍሮች ያሉት እጅግ አስፈሪ አውሬ ነበር፤ ይበላና ያደቅ እንዲሁም የቀረውን በእግሩ ይረጋግጥ ነበር፤+
20 ደግሞም በራሱ ላይ ስለነበሩት አሥር ቀንዶች+ እንዲሁም በኋላ ስለወጣውና ሦስቱ በፊቱ እንዲወድቁ ስላደረገው ስለ ሌላኛው ቀንድ+ ይኸውም ዓይኖችና በእብሪት* የሚናገር አፍ ስላሉት እንዲሁም ከሌሎቹ ስለበለጠው ቀንድ ማወቅ ፈለግኩ።
21 “እየተመለከትኩ ሳለ ይህ ቀንድ በቅዱሳኑ ላይ ጦርነት ከፈተ፤ በእነሱም ላይ አየለባቸው፤+
22 ይህም የሆነው ከዘመናት በፊት የነበረው+ እስኪመጣና ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን አገልጋዮች+ እስኪፈረድላቸው ድረስ ነበር፤ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወርሱበት የተወሰነው ዘመን መጣ።+
23 “እሱም እንዲህ አለ፦ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሳ አራተኛ መንግሥት ነው። ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፤ መላዋን ምድር ያወድማል፣ ይረግጣል እንዲሁም ያደቃል።+
24 አሥሩ ቀንዶች ከዚህ መንግሥት የሚነሱ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነሱም በኋላ ሌላ ይነሳል፤ እሱም ከመጀመሪያዎቹ የተለየ ይሆናል፤ ሦስት ነገሥታትንም ያዋርዳል።+
25 በልዑሉ አምላክ ላይ የተቃውሞ ቃል ይናገራል፤+ ከሁሉ በላቀው አምላክ ቅዱሳንም ላይ ያለማቋረጥ ችግር ያደርስባቸዋል። ዘመናትንና ሕግን ለመለወጥ ያስባል፤ እነሱም ለዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ* በእጁ አልፈው ይሰጣሉ።+
26 ይሁንና ችሎቱ ተሰየመ፤ የገዢነት ሥልጣኑንም ቀሙት፤ ከዚያም አስወገዱት፤ ፈጽሞም አጠፉት።+
27 “‘ከሰማያት በታች ያለ መንግሥት፣ የገዢነት ሥልጣንና የመንግሥታት ግርማ በሙሉ ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን ለሆኑት ሰዎች ተሰጠ።+ መንግሥታቸው ዘላለማዊ መንግሥት ነው፤+ መንግሥታትም ሁሉ ያገለግሏቸዋል፤ ደግሞም ይታዘዟቸዋል።’
28 “የነገሩ ፍጻሜ ይህ ነው። እኔም ዳንኤል ሳስበው የነበረው ነገር በጣም አስፈራኝ፤ ፊቴም ገረጣ፤* ነገሩን ግን በልቤ ያዝኩት።”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በጉራ።”
^ ወይም “አንድ መቶ ሚሊዮን።”
^ ወይም “የጉራ።”
^ ወይም “በጉራ።”
^ ሦስት ዘመን ተኩልን ያመለክታል።
^ ወይም “ፊቴም ተለዋወጠ።”