አንደኛ ሳሙኤል 23:1-29

  • ዳዊት የቀኢላን ከተማ ታደጋት (1-12)

  • ሳኦል ዳዊትን አሳደደው (13-15)

  • ዮናታን ዳዊትን አበረታታው (16-18)

  • ዳዊት ከሳኦል ለጥቂት አመለጠ (19-29)

23  ከጊዜ በኋላም ዳዊት “ፍልስጤማውያን በቀኢላ+ ላይ ውጊያ ከፍተው በየአውድማው ያለውን እህል እየዘረፉ ነው” ተብሎ ተነገረው። 2  ስለሆነም ዳዊት “ሄጄ እነዚህን ፍልስጤማውያን ልምታ?” በማለት ይሖዋን ጠየቀ።+ ይሖዋም ዳዊትን “ሂድ፣ ፍልስጤማውያንን ምታ፤ ቀኢላንም አድናት” አለው። 3  የዳዊት ሰዎች ግን “እዚህ በይሁዳ እያለን እንኳ ፈርተናል፤+ የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ለመውጋት ወደ ቀኢላ ከሄድንማ ምን ያህል እንፈራ!”+ አሉት። 4  በመሆኑም ዳዊት እንደገና ይሖዋን ጠየቀ።+ ይሖዋም “ፍልስጤማውያንን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥህ+ ተነስተህ ወደ ቀኢላ ውረድ” ሲል መለሰለት። 5  ስለዚህ ዳዊት ከሰዎቹ ጋር በመሆን ወደ ቀኢላ ሄዶ ከፍልስጤማውያን ጋር ተዋጋ፤ ከብቶቻቸውን እየነዳ ወሰደ፤ ብዙ ሰውም ገደለባቸው፤ በዚህ መንገድ ዳዊት የቀኢላን ነዋሪዎች ታደጋቸው።+ 6  የአሂሜሌክ ልጅ አብያታር+ በቀኢላ ወደነበረው ወደ ዳዊት በሸሸ ጊዜ ኤፉድ ይዞ ነበር። 7  ሳኦል “ዳዊት ወደ ቀኢላ መጥቷል” የሚል ወሬ ደረሰው። ሳኦልም “ዳዊት በሮችና መቀርቀሪያዎች ወዳሏት ከተማ በመግባት ራሱን ወጥመድ ውስጥ ከቷል፤ ስለሆነም አምላክ እሱን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶታል”*+ አለ። 8  በመሆኑም ሳኦል ወደ ቀኢላ በመውረድ ዳዊትንና ሰዎቹን ከቦ ለመያዝ ሕዝቡን ሁሉ ለጦርነት አሰባሰበ። 9  ዳዊትም ሳኦል ሴራ እየጠነሰሰበት መሆኑን ሲያውቅ ካህኑን አብያታርን “ኤፉዱን ወደዚህ አምጣው” አለው።+ 10  ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ሳኦል ወደ ቀኢላ መጥቶ በእኔ የተነሳ ከተማዋን ለማጥፋት+ ማሰቡን አገልጋይህ በእርግጥ ሰምቷል። 11  ታዲያ የቀኢላ መሪዎች* ለእሱ አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን? አገልጋይህ እንደሰማውስ ሳኦል ወደዚህ ይወርድ ይሆን? የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ ለአገልጋይህ አሳውቀው።” በዚህ ጊዜ ይሖዋ “አዎ፣ ይወርዳል” አለው። 12  ዳዊትም “የቀኢላ መሪዎች እኔንና ሰዎቼን ለሳኦል አሳልፈው ይሰጡን ይሆን?” በማለት ጠየቀ። ይሖዋም “አዎ፣ አሳልፈው ይሰጧችኋል” ሲል መለሰለት። 13  ዳዊትም 600 ገደማ+ ከሚሆኑት የራሱ ሰዎች ጋር ወዲያውኑ ተነሳ፤ ከቀኢላም ወጥተው መሄድ ወደሚችሉበት ቦታ ሁሉ ሄዱ። ሳኦልም ዳዊት ከቀኢላ መሸሹ ሲነገረው እሱን ለማሳደድ መውጣቱን ተወው። 14  ዳዊትም በምድረ በዳው ውስጥ በሚገኙ በቀላሉ በማይደረስባቸው ቦታዎች፣ በዚፍ+ ምድረ በዳ ባለው ተራራማ አካባቢ ተቀመጠ። ሳኦል ሁልጊዜ ይፈልገው ነበር፤+ ይሖዋ ግን በእጁ አሳልፎ አልሰጠውም። 15  ዳዊት በሆሬሽ በሚገኘው በዚፍ ምድረ በዳ ሳለ ሳኦል የእሱን ሕይወት* ለመፈለግ መውጣቱን አውቆ* ነበር። 16  የሳኦል ልጅ ዮናታንም በሆሬሽ ወደሚገኘው ወደ ዳዊት ሄደ፤ እሱም በይሖዋ ላይ ያለው ትምክህት እንዲጠናከር ረዳው።*+ 17  እንዲህም አለው፦ “አባቴ ሳኦል ስለማያገኝህ አትፍራ፤ አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፤+ እኔ ደግሞ ከአንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ፤ አባቴ ሳኦልም ቢሆን ይህን ያውቃል።”+ 18  ከዚያም ሁለቱም በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ተጋቡ፤+ ዳዊትም በሆሬሽ ተቀመጠ፤ ዮናታን ደግሞ ወደ ቤቱ ተመለሰ። 19  በኋላም የዚፍ ሰዎች በጊብዓ+ ወደነበረው ወደ ሳኦል ወጥተው እንዲህ አሉት፦ “ዳዊት እዚሁ አጠገባችን ከየሺሞን*+ በስተ ደቡብ፣* በሃኪላ ኮረብታ+ ላይ በሆሬሽ+ በሚገኙት በቀላሉ የማይደረስባቸው ስፍራዎች ተደብቆ የለም?+ 20  አሁንም ንጉሥ ሆይ፣ ወደዚህ ለመውረድ* በምትፈልግበት በማንኛውም ጊዜ ወደዚህ ና፤ እኛም እሱን ለንጉሡ አሳልፈን እንሰጣለን።”+ 21  በዚህ ጊዜ ሳኦል እንዲህ አላቸው፦ “ለእኔ ስለተቆረቆራችሁ ይሖዋ ይባርካችሁ። 22  አሁንም እባካችሁ ሂዱና ያለበትን ትክክለኛ ቦታም ሆነ በዚያ ያየውን ሰው ማንነት ለይታችሁ ለማወቅ ጥረት አድርጉ፤ ምክንያቱም እሱ በጣም ተንኮለኛ ሰው እንደሆነ ሰምቻለሁ። 23  የሚደበቅባቸውን ቦታዎች በሙሉ በደንብ አጣሩ፤ ከዚያም ተጨባጭ ማስረጃ ይዛችሁልኝ ኑ። እኔም አብሬያችሁ እሄዳለሁ፤ በዚያ አገር የሚገኝ ከሆነ ከይሁዳ ሺዎች* ሁሉ መካከል የገባበት ገብቼ አወጣዋለሁ።” 24  በመሆኑም ሰዎቹ ተነሱ፤ ከሳኦልም ቀድመው ወደ ዚፍ+ ሄዱ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ከየሺሞን በስተ ደቡብ በሚገኘው በአረባ፣+ በማኦን+ ምድረ በዳ ነበሩ። 25  ሳኦልም ዳዊትን ለመፈለግ ከሰዎቹ ጋር መጣ።+ ዳዊትም ይህ በተነገረው ጊዜ ወዲያውኑ ወደ ዓለቱ+ ወርዶ በማኦን ምድረ በዳ ተቀመጠ። ሳኦል ይህን ሲሰማ ዳዊትን እያሳደደ ወደ ማኦን ምድረ በዳ ሄደ። 26  ከዚያም ሳኦል ከተራራው በአንደኛው በኩል ሲሆን ዳዊትና ሰዎቹ ደግሞ ከተራራው በሌላኛው በኩል ሆኑ። ዳዊት ከሳኦል ለማምለጥ እየተጣደፈ ነበር፤+ ይሁን እንጂ ሳኦልና አብረውት የነበሩት ሰዎች ዳዊትንና ሰዎቹን ለመያዝ ተቃርበው ነበር።+ 27  ሆኖም አንድ መልእክተኛ ወደ ሳኦል መጥቶ “ፍልስጤማውያን ምድሪቱን ስለወረሯት ቶሎ ድረስ!” አለው። 28  በዚህ ጊዜ ሳኦል ዳዊትን ማሳደዱን ትቶ+ ፍልስጤማውያንን ለመግጠም ሄደ። ያ ቦታ ‘የመለያያ ዓለት’ የተባለው በዚህ የተነሳ ነው። 29  ዳዊትም ከዚያ ወጥቶ በኤንገዲ+ በሚገኙ በቀላሉ በማይደረስባቸው ስፍራዎች ተቀመጠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ለእጄ አሳልፎ ሸጦታል።”
“ባለርስቶች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍስ።”
“በመውጣቱ ፈርቶ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በይሖዋ እጁን አበረታለት።”
“ከበረሃው፤ ከምድረ በዳው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በስተ ቀኝ በኩል።”
ወይም “ነፍስህ ወደዚህ ለመውረድ።”
ወይም “ጎሳዎች።”