አንደኛ ሳሙኤል 7:1-17

  • ታቦቱ በቂርያትየአሪም (1)

  • ሳሙኤል እስራኤላውያን ‘ይሖዋን ብቻ እንዲያገለግሉ’ አጥብቆ አሳሰበ (2-6)

  • እስራኤላውያን ምጽጳ ላይ ድል ተቀዳጁ (7-14)

  • ሳሙኤል በእስራኤላውያን ላይ ፈራጅ ሆኖ አገለገለ (15-17)

7  በመሆኑም የቂርያትየአሪም ሰዎች መጥተው የይሖዋን ታቦት በኮረብታው ላይ ወደሚገኘው ወደ አቢናዳብ ቤት+ ወሰዱት፤ የይሖዋን ታቦት እንዲጠብቅም ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት። 2  ታቦቱም ወደ ቂርያትየአሪም ከመጣ ረጅም ጊዜ ይኸውም በአጠቃላይ 20 ዓመት አለፈው፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ይሖዋን መፈለግ* ጀመረ።+ 3  ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ “በሙሉ ልባችሁ+ ወደ ይሖዋ የምትመለሱ ከሆነ ባዕዳን አማልክትንና+ የአስታሮትን ምስሎች+ ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ልባችሁንም ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ስጡ፤ እሱን ብቻ አገልግሉ፤+ እሱም ከፍልስጤማውያን እጅ ይታደጋችኋል”+ አላቸው። 4  በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን የባአልንና የአስታሮትን ምስሎች አስወግደው ይሖዋን ብቻ አገለገሉ።+ 5  ከዚያም ሳሙኤል “እስራኤልን ሁሉ በምጽጳ+ ሰብስቡ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ”+ አለ። 6  እነሱም በምጽጳ ተሰበሰቡ፤ ከዚያም ውኃ ቀድተው በይሖዋ ፊት አፈሰሱ፤ ያን ዕለትም ሲጾሙ ዋሉ።+ በዚያም “በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርተናል” አሉ።+ ሳሙኤልም በምጽጳ በእስራኤላውያን ላይ ፈራጅ ሆኖ ማገልገል ጀመረ።+ 7  ፍልስጤማውያንም እስራኤላውያን በምጽጳ አንድ ላይ መሰብሰባቸውን በሰሙ ጊዜ የፍልስጤም ገዢዎች+ እስራኤልን ለመውጋት ወጡ። እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ ፍልስጤማውያንን ፈሩ። 8  ስለሆነም እስራኤላውያን ሳሙኤልን “አምላካችን ይሖዋ እንዲረዳንና ከፍልስጤማውያን እጅ እንዲያድነን ወደ እሱ መጮኽህን አታቁም” አሉት።+ 9  ከዚያም ሳሙኤል አንድ የሚጠባ ግልገል ወስዶ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ+ አድርጎ አቀረበው፤ ሳሙኤልም ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲረዳቸው ተማጸነ፤ ይሖዋም መለሰለት።+ 10  ሳሙኤል የሚቃጠለውን መባ እያቀረበ ሳለ ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንን ለመውጋት ቀረቡ። ይሖዋም በዚያን ዕለት በፍልስጤማውያን ላይ ኃይለኛ የነጎድጓድ ድምፅ ለቀቀባቸው፤+ ግራ እንዲጋቡም አደረጋቸው፤+ እነሱም በእስራኤላውያን ፊት ድል ተመቱ።+ 11  በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች ከምጽጳ ወጥተው ፍልስጤማውያንን ማሳደዳቸውን ተያያዙት፤ ከቤትካር በስተ ደቡብ እስከሚገኘው አካባቢም ድረስ መቷቸው። 12  ከዚያም ሳሙኤል አንድ ድንጋይ+ ወስዶ በምጽጳ እና በየሻና መካከል አስቀመጠው፤ ስሙንም ኤቤንዔዘር* አለው፤ ይህን ያለው “ይሖዋ እስካሁን ድረስ ረድቶናል”+ ሲል ነው። 13  በዚህ ሁኔታ ፍልስጤማውያን ድል ተመቱ፤ ዳግመኛም ወደ እስራኤላውያን ክልል መጥተው አያውቁም፤+ በሳሙኤል ዘመን ሁሉ የይሖዋ እጅ በፍልስጤማውያን ላይ ነበር።+ 14  በተጨማሪም ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ላይ የወሰዷቸው ከኤቅሮን እስከ ጌት ያሉት ከተሞች ለእስራኤላውያን ተመለሱላቸው፤ እንዲሁም እስራኤላውያን በእነዚህ ከተሞች ሥር ያሉትን ክልሎች ከፍልስጤማውያን እጅ አስለቀቁ። በእስራኤላውያንና በአሞራውያን መካከልም ሰላም ወረደ።+ 15  ሳሙኤልም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።+ 16  በየዓመቱም በቤቴል፣+ በጊልጋል+ እና በምጽጳ+ በመዘዋወር በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉ ለሚገኙ እስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 17  ሆኖም ቤቱ የሚገኘው በራማ+ ስለነበር ወደዚያ ይመለስ ነበር፤ በዚያም ለእስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ወደ ይሖዋ ማልቀስ።”
“የእርዳታ ድንጋይ” የሚል ትርጉም አለው።