አንደኛ ነገሥት 1:1-53

  • አቢሻግ የዳዊት ሞግዚት ሆነች (1-4)

  • አዶንያስ መንገሥ ፈለገ (5-10)

  • ናታንና ቤርሳቤህ እርምጃ ወሰዱ (11-27)

  • ዳዊት ሰለሞንን እንዲቀቡት አዘዘ (28-40)

  • አዶንያስ የመሠዊያውን ቀንዶች ያዘ (41-53)

1  ንጉሥ ዳዊት አረጀ፤+ ዕድሜውም እየገፋ ሄደ፤ ልብስ ቢደራርቡለትም እንኳ ሊሞቀው አልቻለም።  በመሆኑም አገልጋዮቹ “ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ልጃገረድ ትፈለግለት፤ እሷም ንጉሡን እንደ ሞግዚት ሆና ትንከባከበው። ጌታዬ ንጉሡ እንዲሞቀው በእቅፉ ትተኛለች” አሉት።  ስለዚህ በመላው የእስራኤል ግዛት በመዘዋወር ቆንጆ ልጃገረድ ፈለጉ፤ ሹነማዊቷን+ አቢሻግንም+ አገኙ፤ ወደ ንጉሡም አመጧት።  እሷም እጅግ ውብ ነበረች፤ የንጉሡም ሞግዚት ሆነች፤ ትንከባከበውም ጀመር፤ ሆኖም ንጉሡ ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት አልፈጸመም።  በዚህ ጊዜ የሃጊት ልጅ አዶንያስ+ “ንጉሥ እሆናለሁ!” በማለት ራሱን ከፍ ከፍ ያደርግ ጀመር። ለራሱም ሠረገላ ከነፈረሰኞቹ እንዲሁም ከፊት ከፊቱ የሚሮጡ 50 ሰዎች እንዲዘጋጁለት አደረገ።+  አባቱ ግን አንድም ቀን “ይህን ያደረግከው ለምንድን ነው?” በማለት ተቃውሞት* አያውቅም ነበር። በተጨማሪም አዶንያስ እጅግ መልከ መልካም ነበር፤ እናቱ እሱን የወለደችው ከአቢሴሎም በኋላ ነበር።  እሱም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮዓብና ከካህኑ ከአብያታር+ ጋር ተመካከረ፤ እነሱም እርዳታና ድጋፍ አደረጉለት።+  ሆኖም ካህኑ ሳዶቅ፣+ የዮዳሄ ልጅ በናያህ፣+ ነቢዩ ናታን፣+ ሺምአይ፣+ ረአይና የዳዊት ኃያላን ተዋጊዎች+ አዶንያስን አልደገፉትም።  በኋላም አዶንያስ በኤንሮጌል አቅራቢያ በሚገኘው በጾሃለት ድንጋይ አጠገብ በጎችን፣ ከብቶችንና የሰቡ እንስሳትን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤+ የንጉሡ ልጆች የሆኑትን ወንድሞቹን በሙሉ እንዲሁም የንጉሡ አገልጋዮች የሆኑትን የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ። 10  ይሁን እንጂ ነቢዩ ናታንን፣ በናያህን፣ የዳዊትን ኃያላን ተዋጊዎች ወይም ወንድሙን ሰለሞንን አልጠራም። 11  ከዚያም ናታን+ የሰለሞንን እናት+ ቤርሳቤህን+ እንዲህ አላት፦ “የሃጊት ልጅ አዶንያስ+ ንጉሥ እንደሆነና ጌታችን ዳዊት ደግሞ ስለ ጉዳዩ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አልሰማሽም? 12  ስለዚህ አሁን ነይ፣ የራስሽንም ሆነ የልጅሽን የሰለሞንን ሕይወት* ማዳን እንድትችይ አንድ ነገር ልምከርሽ።+ 13  ወደ ንጉሥ ዳዊት ገብተሽ እንዲህ በዪው፦ ‘“ልጅሽ ሰለሞን ከእኔ በኋላ ንጉሥ ይሆናል፤ በዙፋኔም ላይ የሚቀመጠው እሱ ነው”+ በማለት ለአገልጋይህ የማልክላት አንተ ንጉሡ ጌታዬ አልነበርክም? ታዲያ አዶንያስ ንጉሥ የሆነው ለምንድን ነው?’ 14  አንቺም እዚያው ገና ከንጉሡ ጋር እየተነጋገርሽ ሳለ እኔ ተከትዬሽ እገባና ያልሽው ትክክል መሆኑን እናገራለሁ።” 15  በመሆኑም ቤርሳቤህ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ውስጠኛው ክፍል ገባች። ንጉሡ በጣም አርጅቶ ነበር፤ ሹነማዊቷ አቢሻግም+ ንጉሡን እየተንከባከበች ነበር። 16  ከዚያም ቤርሳቤህ በንጉሡ ፊት ተደፍታ ሰገደች፤ ንጉሡም “ጥያቄሽ ምንድን ነው?” አላት። 17  እሷም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ጌታዬ ሆይ፣ ‘ልጅሽ ሰለሞን ከእኔ በኋላ ንጉሥ ይሆናል፤ በዙፋኔም ላይ የሚቀመጠው እሱ ነው’ በማለት ለአገልጋይህ በአምላክህ በይሖዋ የማልክላት አንተ ነበርክ።+ 18  ይኸው አሁን ግን አዶንያስ ንጉሥ ሆኗል፤ ጌታዬ ንጉሡም ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።+ 19  እሱም በጣም ብዙ በሬዎችን፣ የሰቡ እንስሳትንና በጎችን መሥዋዕት አድርጓል፤ የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ ካህኑን አብያታርንና የሠራዊቱን አለቃ ኢዮዓብን ጠርቷል፤+ አገልጋይህን ሰለሞንን ግን አልጠራውም።+ 20  አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እስራኤላውያን በሙሉ ከጌታዬ ከንጉሡ በኋላ በዙፋኑ ላይ የሚቀመጠው ማን እንደሆነ እንድታሳውቃቸው ዓይኖቻቸው አንተ ላይ ናቸው። 21  አለዚያ ግን ጌታዬ ንጉሡ ከአባቶቹ ጋር በሚያንቀላፋበት ጊዜ እኔና ልጄ ሰለሞን እንደ ከዳተኞች ተደርገን እንቆጠራለን።” 22  እሷም ገና ከንጉሡ ጋር እየተነጋገረች ሳለ ነቢዩ ናታን ገባ።+ 23  ወዲያውም ለንጉሡ “ነቢዩ ናታን መጥቷል!” ብለው ነገሩት። ናታንም ንጉሡ ፊት ቀርቦ በግንባሩ መሬት ላይ በመደፋት ሰገደ። 24  ከዚያም ናታን እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ‘አዶንያስ ከእኔ በኋላ ንጉሥ ይሆናል፤ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውም እሱ ነው’ ብለህ ተናግረሃል እንዴ?+ 25  ይኸው ዛሬ በጣም ብዙ በሬዎችን፣ የሰቡ እንስሳትንና በጎችን ለመሠዋት ወርዷል፤+ እንዲሁም የንጉሡን ልጆች በሙሉ፣ የሠራዊቱን አለቆችና ካህኑን አብያታርን ጠርቷል።+ እነሱም በዚያ ከእሱ ጋር እየበሉና እየጠጡ ‘ንጉሥ አዶንያስ ለዘላለም ይኑር!’ እያሉ ነው። 26  ሆኖም እኔን አገልጋይህን ወይም ካህኑን ሳዶቅን አሊያም የዮዳሄን ልጅ በናያህን+ ወይም አገልጋይህን ሰለሞንን አልጠራም። 27  ጌታዬ ንጉሡ ከእሱ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠው ማን እንደሆነ ለአገልጋዩ ሳይነግረው ይህ እንዲደረግ ፈቅዷል?” 28  በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ” አለ። እሷም ገብታ ንጉሡ ፊት ቆመች። 29  ንጉሡም እንዲህ ሲል ማለ፦ “ከመከራ ሁሉ ባዳነኝ*+ ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ 30  ‘ልጅሽ ሰለሞን ከእኔ በኋላ ንጉሥ ይሆናል፤ በእኔ ምትክ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውም እሱ ነው!’ በማለት በእስራኤል አምላክ በይሖዋ በማልኩልሽ መሠረት ዛሬም ይህ እንዲፈጸም አደርጋለሁ።” 31  ከዚያም ቤርሳቤህ በግንባሯ መሬት ላይ ተደፍታ ለንጉሡ በመስገድ “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም ይኑር!” አለች። 32  ንጉሥ ዳዊትም ወዲያውኑ “በሉ አሁን ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንንና የዮዳሄን+ ልጅ በናያህን+ ጥሩልኝ” አለ። እነሱም ገብተው ንጉሡ ፊት ቀረቡ። 33  ንጉሡም እንዲህ አላቸው፦ “የጌታችሁን አገልጋዮች ውሰዱና ልጄን ሰለሞንን በበቅሎዬ*+ ላይ አስቀምጣችሁ ወደ ግዮን+ ይዛችሁት ውረዱ። 34  በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቀቡታል፤+ ከዚያም ቀንደ መለከት እየነፋችሁ ‘ንጉሥ ሰለሞን ለዘላለም ይኑር!’+ በሉ። 35  አጅባችሁትም ተመለሱ፤ እሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል፤ በእኔም ምትክ ንጉሥ ይሆናል፤ እኔም በእስራኤልና በይሁዳ ላይ መሪ አድርጌ እሾመዋለሁ።” 36  የዮዳሄ ልጅ በናያህም ወዲያውኑ ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “አሜን! የጌታዬ የንጉሡ አምላክ ይሖዋ ይህን ያጽናው። 37  ይሖዋ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር እንደነበረ ሁሉ ከሰለሞንም ጋር ይሁን፤+ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሥ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርገው።”+ 38  ከዚያም ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያህ፣+ ከሪታውያንና ጴሌታውያን+ ወርደው ሰለሞንን በንጉሥ ዳዊት በቅሎ ላይ አስቀመጡት፤+ ወደ ግዮንም+ አመጡት። 39  ካህኑ ሳዶቅም ከድንኳኑ+ ውስጥ የዘይቱን ቀንድ+ ወስዶ ሰለሞንን ቀባው፤+ እነሱም ቀንደ መለከት መንፋት ጀመሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ “ንጉሥ ሰለሞን ለዘላለም ይኑር!” እያለ ይጮኽ ጀመር። 40  ከዚያም ሕዝቡ በሙሉ ዋሽንት እየነፋና በደስታ እየፈነደቀ ተከትሎት ወጣ፤ ከጩኸታቸውም የተነሳ ምድሪቱ ተሰነጠቀች።+ 41  አዶንያስና የጋበዛቸው ሰዎች ሁሉ በልተው ሲጨርሱ ይህን ድምፅ ሰሙ።+ ኢዮዓብ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ሲሰማ “በከተማዋ ውስጥ የሚሰማው ይህ ሁሉ ሁካታ ምንድን ነው?” አለ። 42  እሱም ገና እየተናገረ ሳለ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን+ መጣ። ከዚያም አዶንያስ “መቼም አንተ ጥሩ* ሰው ስለሆንክ ምሥራች ሳትይዝ አትመጣምና ግባ” አለው። 43  ዮናታን ግን ለአዶንያስ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ምሥራች ይዤስ አልመጣሁም! ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰለሞንን አንግሦታል። 44  ንጉሡም ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያህ፣ ከሪታውያንና ጴሌታውያን አብረውት እንዲሄዱ አደረገ፤ እነሱም በንጉሡ በቅሎ ላይ አስቀመጡት።+ 45  ከዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት። እነሱም ከዚያ እየተደሰቱ መጡ፤ ከተማዋ በጩኸት እየተናወጠች ነው። እናንተም የሰማችሁት ይህን ድምፅ ነው። 46  ከዚህም በላይ ሰለሞን በነገሥታቱ ዙፋን ላይ ተቀምጧል። 47  የንጉሡ አገልጋዮችም ‘አምላክህ የሰለሞንን ስም ከአንተ ስም በላይ ታላቅ ያድርገው፤ ዙፋኑንም ከአንተ ዙፋን የበለጠ ያድርገው’ በማለት ለጌታችን ለንጉሥ ዳዊት ደስታቸውን ለመግለጽ መጥተዋል። በዚህ ጊዜ ንጉሡ አልጋው ላይ ሰገደ። 48  ከዚያም ንጉሡ ‘ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጥ ሰው የሰጠኝና ዓይኖቼም ይህን እንዲያዩ ያደረገው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ!’ አለ።” 49  አዶንያስ የጋበዛቸው ሰዎችም ሁሉ ተሸበሩ፤ እያንዳንዳቸውም ተነስተው በየፊናቸው ሄዱ። 50  አዶንያስም ሰለሞንን ስለፈራው ተነስቶ በመሄድ የመሠዊያውን ቀንዶች ያዘ።+ 51  በኋላም ሰለሞን “አዶንያስ ንጉሥ ሰለሞንን ፈርቶታል፤ ‘በመጀመሪያ ንጉሥ ሰለሞን አገልጋዩን በሰይፍ እንደማይገድል ይማልልኝ’ በማለት የመሠዊያውን ቀንዶች ይዟል” ተብሎ ተነገረው። 52  በዚህ ጊዜ ሰለሞን “ጸባዩን ካሳመረ ከራስ ፀጉሩ አንዲቷም እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም፤ መጥፎ ነገር ከተገኘበት+ ግን ይሞታል” አለ። 53   በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን አዶንያስን ከመሠዊያው ላይ እንዲያወርዱት ሰዎች ላከ። ከዚያም አዶንያስ መጥቶ ለንጉሥ ሰለሞን ሰገደ፤ ሰለሞንም “ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ስሜቱን ጎድቶት፤ ገሥጾት።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍሴን በዋጃት።”
ወይም “በእንስት በቅሎዬ።”
ወይም “የተከበርክ።”